17 የካቲት 2022, 12:11 EAT

በአካባቢው ባለው ጸጥታ ችግር ምክንያት የነዳጅ አቅርቦት በመስተጓጎሉ የስኳር ምርቱን አቋርጦ የነበረው የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ዳግም ወደ ሥራ መመለሱን የስኳር ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽን ተጠባባቂ ሥራ አስፈፃሚ ለቢቢሲ ገለጹ።
ፋብሪካው ለሰባት ቀናት ያህል ከየካቲት 02፣ 2014 ዓ.ም ሥራ አቁሞ የነበረ ሲሆን የካቲት 8 ዳግም ወደ ሥራ መግባቱን የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረታ ደመቀ ተናግረዋል።
በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የነዳጅ ጫኝ አሸከርካሪዎች ስጋት አድሮባቸው ወደ ቦታው ሊሄዱ ባለመቻላቸው ነበር የነዳጅ እጥረት ያጋጠመው።
“በአሁኑ ወቅት በያዝነው ሳምንት ሰኞ የነዳጅ አቅርቦት በመድረሱ ማክሰኞ ዕለት ፋብሪካው ዳግም ወደ ሥራ ተመልሷል” ብለዋል ሥራ አስፈጻሚው።
- የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሥራ ማቆሙ ተገለጸ
- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል በቄለም ወለጋ ሁለት አምቡላንሶቹ እንደተወሰዱበት ገለጸ
- ምርጫ ቦርድ ብልፅግናን ጨምሮ በርካታ ፓርቲዎችን አሳሰበ
ብሉምበርግ ፋብሪካው ሥራውን ለማቆም የተገደደው የኦሮሞ ነፃነት ጦር ወይም መንግሥት “ሸኔ” የሚለው ታጣቂ ቡድን በፋብሪካው ላይ ባደረሰው ጥቃት ምክንያት ነው በሚል አስነብቧል።
አቶ ረታ በበኩላቸው ፋብሪካው ሥራ አቋርጦ የነበረው በአካባቢው አልፎ አልፎ በሚፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የነዳጅ አቅርቦት በመስተጓጎሉና እጥረት በመፈጠሩ ነው ብለዋል።
ከሳምንታት በፊት አራት ያህል ትራክተሮች ተቃጥለው የነበረ ቢሆንም ይህ ግን ፋብሪካው ሥራ እንዲያቆም አላደረገውም ይላሉ።
“ፋብሪካው ብዙ ሺህ ሄክታር የአገዳ መሬት ያለው ሲሆን በዚያ ውስጥ ትራክተሮች ይንቀሳቀሳሉ። ትራክተሮቹ የተቃጠሉትም እዚያ መሃል ላይ ነው።” የሚሉት አቶ ረታ ማን እንዳቃጠላቸው የጸጥታ አካላት ምላሽ ሊሰጡበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ረታ ከሆነ ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የአሁኑን ሳይጨምር ፋብሪካው ከዚህ ቀደም ሥራ ያቆመበት ጊዜ የለም።
በዚያ አካባቢ አልፎ አልፎ የጸጥታ ችግር የሚያጋጥም ቢሆንም ፋብሪካው ላይ የተከሰተ ችግር አለመኖሩን አስረድተዋል።
“መስመሩ ላይ የጸጥታ ችግር አጋጠመ ማለት ፋብሪካው ላይ ሊያጋጥም ይችላል ማለት አይደለም። ፋብሪካው ከዋናው መስመር ወደ አምሳ ሜትር ተገንጥሎ ነው የሚገኘው። ለብቻው ወደ ውስጥ ገብቶ ነው ያለው።”ይላሉ።
በተጨማሪም ፋብሪካው የማኅበረሰቡ የጀርባ አጥንት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ረታ “የአካባቢው ኅብረተሰብ እስከ ልጆቹ የሚተዳደረው በፋብሪካው ነው።” ብለዋል።
አቶ ረታ አክለውም ፋብሪካው የቴክኒክ ችግር ሲያጋጥመው ለሰዓታት ሊያቆም እንደሚችልና አስፈላጊው ጥገና ተደርጎለት እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ይህ ግን ማቆም የሚባል ሳይሆን ውስብስብ ማሽኖች ባሉት ፋብሪካ ውስጥ የተለመደ ሁኔታ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በሰባት ቀናት ውስጥ ፋብሪካው ምን ያህል ገንዘብ ወይም ምርት አጣ? የሚል ጥያቄ ቢቢሲ ለአቶ ረታ ያቀረበላቸው ሲሆን ፋብሪካው በአማካኝ በጥሩ የማምረቻው ወቅት በቀን 10 ሺህ ኩንታል እንደሚያመርት ጠቅሰው ሆኖም ፋብሪካው ምን ያህል እንዳጣ የተገመገመ ጉዳይ አለመኖሩን ተናግረዋል።
በስኳር አቅርቦትስ ላይ መጉላላት ፈጥሮ ይሆን? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “አገሪቱ መተሃራ፣ ወንጂና ጥገናውን በቅርቡ ጨርሶ ወደ ሥራ የገባው በአካባቢው የሚገኘው አርጆ ዴዴሳ ፋብሪካን ጨምሮ ሌሎች ፋብሪካዎች በመኖራቸው የአንድ ፋብሪካ ሰባት ቀን ማቆም በስኳር ሥርጭት ላይ ምንም አይነት ተፅእኖ አይኖረውም ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አባይ ጮመን ወረዳ በፊንጫአ ሸለቆ ውስጥ ልዩ ስሙ አገምሳ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ ይገኛል።
ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ፋብሪካው በዓመት 270 ሺህ ቶን ስኳር የማምረት አቅም አለው። ፋብሪካው ከስኳር ምርቱ በተጨማሪ ኢታኖል በማምረት ከቤንዚል ጋር ተደባልቆ ለተሸከርካሪዎች በነዳጅነት እንዲውል ያደርጋል።