
ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በህወሓት ጥቃት ምክንያት አፋር ውስጥ የደረሰውን የሰብዓዊ ቀውስ በሚዛናዊነት እንዳላየው የአፋር ክልል መንግስት ገልጿል።
አሁንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየደረሰ ያለውን ጉዳት እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርቧል።
የአፋር ክልል ፤ ህወሓት አፋርን ከትግራይ ክልል ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ላይ በፈፀመው ወረራ መጋሌ፣ በራህሌ፣ ኤረብቲ፣ እንዲሁም አብአላ ከተማን በመያዝ ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች እንዲሰደዱ ፤ በሚወረውረው ከባድ መሳሪያም አቅመ ደካማ ወገኖች ለአካል ጉዳትና ለሞት መዳረጋቸውን ፣ ከዚህ ባለፈ ሆን ተብሎ ዝርፊያ እየተፈፀመ መሆኑን አስረድቷል።
የተፈናቀሉ ሰዎች በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን በተለያዩ ቦታዎች ተበትነው መጠለያ ጣቢያ ሊመጡ ያልቻሉ ወገኖች መኖራቸው ተገልጿል።
የአፋር ክልል ህዝብ ተገቢውን ትኩረት ያላገኘ ሲሆን ክልሉ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአርብቶ አደሩ ፣ እየሞተ ላለው ማህበረሰብ ተገቢውን ትኩረት እንዳልሰጠ በመግለፅ ወቅሷል።
ማህበረሰቡ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁን ላይ ድጋፍ የሚሻ መሆኑን አመልክቷል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰብዓዊነትን በእኩልነት እንዲያስተናግድ ፣ የደረሰውን ጉዳት በአካል ተገኝቶ ከመመልከት ጀምሮ ከህዝቡ ጎን እንዲቆም የአፋር ክልል ጥሪ አቅርቧል።
ክልሉ የጦርነቱ ሰለባዎችን ለመርዳት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከደረሰው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አንፃር በውስን አካላት ጥረት ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል አስገንዝቧል። መንግስት እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ፣ የተራድኦ ድርጅቶች እጃቸውን እንዲዘረጉ ጠይቋል።