17 የካቲት 2022, 10:49 EAT

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገዢው ፓርቲ ብልፅግናን ጨምሮ በርካታ ፓርቲዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን እንዲያደርጉ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዳር 23/ 2014 ዓ.ም ከፓርቲዎች ጋር ባደረገው ውይይት ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ ገልጦላቸው ነበር።
ነገር ግን ፓርቲዎቹ የሚጠበቅባቸውን አጠናቀው ባለማቅረባቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በአንድ ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ እና ለቦርዱ እንዲያስገቡ መወሰኑ ይታወሳል ሲል ቦርዱ ያወጣው መግለጫ ያትታል።
- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል በቄለም ወለጋ ሁለት አምቡላንሶቹ እንደተወሰዱበት ገለጸ
- ቴሌግራም ላይ በተጋሩ ፎቶዎች ምክንያት ሕይወታቸው የተመሳቀለ ሴቶች
- በዩክሬን ጦርነት እንዳይከሰት ያስችላሉ የተባሉ አምስት መንገዶች
አሁን የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማንሳቱ ፓርቲዎቹ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባዔያቸውን እንዲያደርጉ እንዲሁም የሰነድ ማሻሻያ እንዲከውኑ አሳስቧል።
ካለፈው ሃገራዊ ምርጫ በኋላ ጠቅላላ ጉባዔ አላደረጉም፤ አልፎም የሰነድ ማሻሻያ አላከናወኑም ተብሎ በቦርዱ የተጠቀሱት 26 ፓርቲዎች ናቸው።
ገዢው ብልፅግናን ጨምሮ 13 ሃገራዊና 13 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቦርዱ ባወጣው መግለጫ ላይ ስማቸው ተጠቅሷል።
ቦርዱ በማሕበራዊ ድር አምባ ገፆቹ በለጠፈው መግለጫ ስማቸው ከተጠቀሰ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ይገኙበታል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ የነበረው ሃገራዊው ምርጫ ባለፈው ዓመት ተካሂዶ ገዢው ፓርቲ አብዛኛውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘቱ ይታወሳል።