17 የካቲት 2022

ዩናይትድ ኪንግደም ፈጣን የመኖሪያ ፈቃድ የሚያስገኘውን ቪዛ ለውጭ አገር ባለሃብቶች (ኢንቨስተሮች) መስጠት ልታቆም ነው።
አገሪቷ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከሩሲያ ጋር ባለው ግንኙነት ጫና ስለበረታበት ነው።
በአገሪቱ አሰራር መሰረት 2 ሚሊዮን ፓውንድ ወይም ከዚያ በላይ መዋዕለ ንዋይ ያላቸው ኢንቨስተሮች ደረጃ 1 የሚሰኘውን የኢንቨስተር ቪዛና መኖሪያ ፍቃድ ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን የመንግሥት ምንጭም ይህ እንደሚሰረዝ አረጋግጧል።
ይህ አሰራር በአውሮፓውያኑ 2008 ሲሆን የተዋወቀው ከአውሮፓ ህብረት ውጭ ያሉ ባለጸጎች በእንግሊዝ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለማበረታታት ያለመ ነው።
በአሰራሩ ላይ አንዳንድ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ተከትሎም ለተወሰነ ጊዜም በግምገማ ላይ ቆይቷል።
- በአለም የመጀመሪያዋ ሴት ከኤችአይቪ ተፈወሰች
- በዩክሬን ጦርነት እንዳይከሰት ያስችላሉ የተባሉ አምስት መንገዶች
- ቴሌግራም ላይ በተጋሩ ፎቶዎች ምክንያት ሕይወታቸው የተመሳቀለ ሴቶች
ነገር ግን ይህ ውሳኔ የተሰማው ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ትችላለች በሚለው ስጋት ምክንያት ዩናይትድ ኪንግደም ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥ የደረሰባትን ከፍተኛ ጫና ተከትሎ ነው።
ሩሲያ በዩክሬን ድንበር ከ100 ሺህ በላይ ወታደሮችን ያሰማራች ቢሆንም ወረራ ለመፈጸም አቅዳለች የሚለውን ግን አትቀበለውም።
ደረጃ አንድ (ኢንቨስተር) ቪዛ፣ ወርቃማ ቪዛ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም 2 ሚሊዮን ፓውንድ ወይም ከዚያ በላይ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የየትኛውም አገር ዜጎች የመኖሪያ ፈቃድ ይሰጣቸዋል፤ ቤተሰቦቻቸውም እንዲሁ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
ይህንን ቪዛ ያገኙ ግለሰቦች በአገሪቷ ምን ያህል ኢንቨስት ያደርጋሉ የሚለው ታይቶ በፍጥነት ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘትም ማመልከት ይችላሉ።
2 ሚሊዮን ፓውንድ ኢንቨስት ያደረጉ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ በአምስት አመት ውስጥ፣ አምስት ሚሊዮን በሶስት አመት ውስጥ፣ 10 ሚሊዮን ከሆነ ደግሞ በሁለት አመት ውስጥ ማመልከት ይችላሉ።
የአገር ውስጥ ጽሕፈት ቤት (ሆም ኦፊስ) እንዳስታወቀው ይህ አሰራር በሙስና የተገኘ ገንዘብ ጥቅም ላይ እንዳይውል ለማድረግ ቀደም ሲል ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል።
ማሻሻያና ለውጦች ከመደረጋቸው ከአውሮፓውያኑ 2015 በፊት የተሰጡ ቪዛዎችና መኖሪያ ፈቃዶችን በተመለከተው ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተገመገመ መሆኑንና በጊዜውም ሪፖርት እንደሚደረግ ቃለ አቀባዩ አክለዋል።
አሰራሩ በአውሮፓውያኑ 2008 ጀምሮ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ የአገር ውስጥ ጽሕፈት ቤት (ሆም ኦፊስ) 14 ሺህ 516 የኢንቨስትመንት ቪዛ ለሩሲያ ዜጎች ሰጥቷል።
አሰራሩ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ማሻሻያዎች የተደረጉ ሲሆን ከዚህም ውስጥ አመልካቾች ሃብታቸውን እንዴት እና መቼ እንዳገኙ ተጨማሪ ምርመራዎች መደረጉ አንዱ ነው።