
ኢትዮጵያን የሚመስል የአገር መከላከያ ሰራዊት ለመገንባት ኢትዮጵያውያን የአብራካቸውን ክፋይ የአገር መከላከያ ሰራዊትን እንዲቀላቀሉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የአንደኛ ደረጃ የምርጥ አዋጊ እና ተዋጊ የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚ ኮለኔል ሁሴን አህመድ ገለፁ፡፡
ኮ/ል ሁሴን አህመድ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ለማጠናከር ወላጆች ልጆቻቸውን መርቀው ወደ አገር መከላከያ ሰራዊት መላክ አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያን የሚመስል ሰራዊት ለመገንባት ብሄር ብሄረሰቦች የአብራካቸውን ክፋይ ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ የማድረግ አገራዊ ግዴታ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ለኢትዮጵያ ህዝብ መልዕክት አለኝ ያሉት ኮሎኔሉ፤ ‹‹ውትድርና ቅብብሎሽ ሥራ ነው፡፡ እኔ በግሌ 31 ዓመት ለአገሬ ኢትዮጵያ በውትድርና አገልግዬ ቦርድ እየወጣሁ ነው፡፡ የእኛ ተተኪ ያስፈልጋል፡፡ ሰራዊታችን ተተኪ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ወደ አገር መከላከያ ሠራዊት እንዲገባ ህዝቡ ልጆቹን መርቆ መላክ አለበት›› ብለዋል፡፡
እንደ ኮሎኔሉ ገለፃ፤ ውትድርና በግዳጅ ሊሆን የማይሆንና ይልቁንም ለአገር ሠላምና አንድነት ሲባል የሚገባበት ክብር ያለው ሙያ ነው፡፡ በዚህ ክቡር ሙያ ላይ መሰማራት ደግሞ ለአገርም ለወገንም የሚያኮራ ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አገርና ወግንን የሚያኮራ ጠንካራ ሰራዊት እየገነባች ነው፡፡ እየተገነባ ያለው ሰራዊት ህዝቡ የሚተማመንበትና የሚኮራበት እንዲሆን ከጨቻፍ እስከጫፍ ያለው ኢተዮጵያዊ መከላከያ ሰራዊትን ሊቀላቀል ይገባል፡፡
ልማት የሚቀጥለው ሠላም ሲኖር ነው ያሉት ኮሎኔሉ፤ ‹‹ሠላም ባለመኖሩ የተፈጠረውን ክፍተት እየተመለከትን ነው፤ ከተሞችም ወድመዋል፤የልማት ሥራዎች ተቋርጠዋል፡፡ ስለዚህ የደፈረሰው ስላማችንን ለመመለስ ህዝቡ ሰራዊቱን በመደገፍ አና አካባቢውን በማልማት ንቁ ተሳፎ ሊያደርግ ይገባል›› ብለዋል።
ህወሃትን በመፋለም ላይ ሳሉ እጃቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ኮለኔል ሁሴን፤ ‹‹እጄ እንደተቆረጠ አላስብም፤ ሙሉ እንደሆንኩ ነው የማስበው፡፡ የሰው ልጅ እግሩ ወይንም እጁ አሊያም ዓይኑ ሊጠፋ ይችላል።
ነገር ግን ከእኛ መጥፋት የሌለበት ህሊናችን ነው፡፡ የምናስብበት አዕምሮ ነው መኖር ያለበት፡፡ አዕምሯችን እስከሠራ ድረስ ማንኛውንም ነገር መሥራት እንችላለን፡፡ በሕይወት መትረፌ በራሱ ዕድለኝነት ነው፡፡
ሊያቆስለኝ ሳይሆን ሊገለኝ የመጣ መሳሪያ ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ተረፍኩኝ፡፡ እጄ ስለተቆረጠ ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር አይሰማኝም፡፡ ውስጤ እጅግ ደስተኛ ነው፡፡ አዕምሮዬ የሚያስበውና ይከፋኝ የነበረው ለአገሬ አስተዋፅኦ ባላደርግ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ባልሳተፍ ኖሮ መኖር አልችልም፡፡ ያመኛል፡፡ አሁን ግን የምችለውን አድርጌ ስለሆነ ውስጤ ደስተኛ ነው›› ብለዋል፡፡
ኮ/ል ሁሴን አህመድ ለፈጸሙት ጀብድ፤ የደቡብ ዕዝ ‹‹ጥሩ አዋጊ እና ተዋጊ አንደኛ ደረጃ የወርቅ ሜዳሊያ›› እንዳበረከተላቸው ይታወቃል፡፡