ከ 5 ሰአት በፊት

የኦታዋ ፖሊስ መንግሥት ላይ አምጸዋል በሚል በዋና ከተማዋ የሚገኙ ሁለት የጭነት መኪና ሹፌሮች መሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።
የጭነት መኪና ሹፌሮች የካናዳ መንግሥት ያወጣውን ጠንከር ያለ የኮቪድ ደንብ እየተቃወሙ ይገኛሉ።
ታማራ ሊችና ክሪስ ባርበር የተሰኙት ግለሰቦች ሐሙስ ምሽት ሲሆን በቁጥጥር ሥር የዋሉት በቅርቡ ክስ ሊመሠረትባቸው ይችላል።
የሃገሪቱ ባለሥልጣናት ድንበር አካባቢ ያሉ ተቃዋሚዎች እንዲሸሹ ማድረግ ችለዋል።
ካናዳ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ ሕጓን ተግባራዊ ለማድረግ ከወሰነች በኋላ ነው ግለሰቦቹ የታሰሩት።
ነገር ግን አሁንም በኦታዋ ተቃዋሚዎች ድምፃቸውን እያሰሙ ሲሆን የከተማዋ ፖሊስ ኃላፊ ስቲቭ ቤል “በሰላም ወደቤታቸው የማይገቡ ከሆነ መላ አዘጋጅተናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
- ቱርክ የምትታወቅበት ስሟ ላይ ለውጥ ልታደርግ ነው
- ዩናይትድ ኪንግደም ለውጭ አገር ባለሃብቶች የምትሰጠውን ወርቃማ ቪዛ ልትሰርዝ ነው
- ቴሌግራም ላይ በተጋሩ ፎቶዎች ምክንያት ሕይወታቸው የተመሳቀለ ሴቶች
ባለፈው ሰኞ የአስቸኳይ ጊዜ ሕጉ ተግባራዊ እንዲሆን ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፤ በአንዳንድ ቦታዎች ሰዎች ያለምክንያት እንዳይሰባሰቡ አዘዋል።
ሰልፈኞቹ 400 ያክል የጭነት ተሽከርካሪዎችን ኦታዋ በሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢያ ባሉ መንገዶች ላይ በማቆም ተቃውሟቸውን እየገለፁ ነው።
አሽከርካሪዎቹ ይህንን ድርጊታቸውን ካላቆሙ እስር እንደሚጠብቃቸው፣ መኪናቸውን ሊነጠቁ እንደሚችሉ አልፎም ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
ታማራ ሊች የተባለችው መሪ የባንክ አካውንቷ እግድ እንደተጣለበት ለካናዳ መገናኛ ብዙሃን ተናግራለች።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስትያ ፍሪላንድ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎቹ ባንክ አካውንት እግድ እየተጣለበት እንደሆነ ገልጸዋል።
“እየሆነ ነው ያለው። ከፈለጋችሁ ምን ያክል እንደሆነ የሚያሳይ መረጃ ፊት ለፊቴ አለ” ብለዋል።
ባለሥልጣናት ምጣኔ ሃብቱ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ባሏቸው ከተሞች ላይ ያሉ ተቃውሞዎችን መቆጣጠር ችለዋል።
በተለይ ዊንድሶር፣ ኦንታሪዮና የአሜሪካዋን ሚሺገን ግዛት የሚያገናኘው ድልድይ እንዲሁም አልበርታ፣ ኤመርሰን እና ማኒቶባ አሁን ከተቃውሞ ነፃ ሆነዋል።
የኦታዋ ፖሊስ በከተማዋ ባሉ ዋና ዋና በሚባሉ የንግድና የመኖሪያ ሥፍራዎች 100 ጊዜያዊና አነስተኛ የፖሊስ ጣቢያዎች አቁሟል።
ባለፈው ሐሙስ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ በታችኛው ምክር ቤት ቀርበው ለምን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈለገ ለሚለው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሣት ላይ ቤንዚን ነው ያርከፈከፉት ሲሉ ይወቅሳሉ።
የካናዳ ሲቪል ሊበርቲስ ማሕበር መንግሥትን ከባድ እርምጃ ወስዷል በማለት ፍርድ ቤት ሊያቆመው እንደሆነ አስታውቋል።
ተቃዋሚዎቹ መጀመሪያ ማመፅ የጀመሩት ድንበር የሚሻገሩ ሹፌሮች ሊከተቡ ይገባሉ የሚለውን መመሪያ በመቃወም ነበር።
ነገር ግን እያደር የጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ መንግሥት ያወጣቸው ጥብቅ የኮቪድ መመሪያዎችን ወደ መቃወም ገቡ።
‘ፍሪደም ኮንቮይ’ የተሰኘ ስያሜ የተሰጣቸው ተቃዋሚዎችን የሚደግፉ ሰዎች መንግሥት ለሰላማዊ ተቃውሞ አላስፈላጊ ምለሽ ሰጥቷል ሲሉ ይከሳሉ