18 የካቲት 2022, 15:09 EAT

በአካባቢው ያሉ ቁሳቁሶችን ተጠቅሞ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በተሳካ ሁኔታ የገጣጠመው ኢትዮጵያዊው የዩንቨርስቲ መምህር ትልቅ ራዕይ እንዳለው ለቢቢሲ ተናግሯል።
አማኑኤል ባልቻ ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገለ ሲሆን ከዚያ በፊት ግን ሃገር በቀል ኩባንያ በሆነው ደጀን አቪየሽን በመካኒካል መሃንዲስነት ሰርቷል።
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ዩኒቨርስቲው የፈጠራ ቀንን ሲያከብር አማኑኤልም የገጣጠመውን ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በተሳካ ሁኔታ እንዲበር አድርጓል።
ሌሎች ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖች) እና በሙከራ ደረጃ ላይ ያለ አንድ አይሮፕላን መገጣጠሙን ለቢቢሲ ተናግሯል።
- ምርጫ ቦርድ ብልፅግናን ጨምሮ በርካታ ፓርቲዎችን አሳሰበ
- ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ምርት አቋርጦ የነበረው የፊንጫአ ስኳር ፋብሪካ ወደ ሥራ ተመለሰ
- ከአምስት ወራት በኋላ የሕክምና መገልገያዎች ዛሬ ትግራይ መድረሳቸውን ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል አስታወቀ
“ከዚህም የሚበልጡ ነገሮችን ማሳካት ስለምችል ይህ የመጨረሻ ፍላጎቴ አይደለም… ይህ ለራዕዬ መንገድ መጥረጊያ ነው” ብሏል።
የመጨረሻ አላማው “ሁለት መንገደኞችን የመያዝ አቅም ያለው የራሴን አውሮፕላን መስራት ነው” ይላል።
“ህልሜን እውን አደርገዋለሁ እና ዩኒቨርሲቲዬን በቅርቡ አኮራለሁ” ሲል አክሎ ተናግሯል።
አማኑኤል በአገር ውስጥ የሚገጣጥማቸውን ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ለቪዲዮ ቀረጻ፣ ለአደጋ ወቅት እርዳታ እና ለአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት ሊጠቀምባቸው አቅዷል።
ማክሰኞ እለት የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ካደረገ በኋላ ለቀናት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ በበርካቶች ዘንድ ምስጋና እና አድናቆት እየተቸረው ነው።
የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ፀረ-መንግሥት ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ይገኛል።