18 የካቲት 2022, 10:48 EAT

ክትባት

በዚህ ሳምንት የዓለም ሃገራት አንድ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። 1 ቢሊዮን የክትባት ብልቃጦች መግዛት ለማይችሉ ሃገራት ለመለገስ። ነገር ግን 40 በመቶ የዓለም ሕዝብ አንድም ክትባት አላገኘም።

እስከዛሬ 11 ቢሊዮን ክትባቶች ተመርተዋል። ይህ ለአቅመ ክትባት የደረሱ የምድራችን ሰዎችን ሁለት ጊዜ ለመከተብ የሚያስችል ነው። እና ለምን አሁንም በርካታ ሰው ክትባት ሊደርሰው አልቻለም?

“ከ70 በመቶ በላይ ክትባቶች አሁንም ወደ ቡድን 20 ሃገራት ነው የሚሄዱት። ይህ ማለት ከ175 በላይ ሃገራት በቂ ክትባት አላገኙም ማለት ነው” ይላሉ አሁን የዓለም ጤና ድርጅት አምባሳደር የሆኑት የቀድሞው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን።

አደጉ የሚባሉ ሃገራት በአማካይ ከ60 በመቶ በላይ ዜጎቻቸውን ከትበዋል። አላደጉም የሚባሉ ሃገራት ደግሞ 10 በመቶ።

በፈረንጆቹ 2020 የተቋቋመው ኮቫክስ የተሰኘው ማዕቀፍ አቅም ለሌላቸው ሃገራት የኮቪድ ክትባት ማድረስ ነበር ዓላማው።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት የምጣኔ ሃብታቸው የዳበረ ሃገራት የመጀመሪያውን ዙር ክትባት የራሳቸው አደረጉት።

ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ዩኬ አምስት ሚሊዮን አስትራዜኔካ የተሰኘ ክትባት ከሕንዱ ክትባት አምራች ገዛች። ወርሃ ግንቦት ላይ ሕንድ ውስጥ በቀን በኮቪድ ምክንያት 4 ሺህ ሰው እየሞተ ነበር።

ይሄኔ ነው ሕንድ የኮቪድ ክትባት ወደ ውጭ እንዳይላክ ማዕቀብ የጣለችው።

ይሄ ሁሉ ሲሆን ኮቫክስ የተሰኘው ማዕቀፍ ሰልፍ ከመያዝ ውጭ ምንም አማራጭ አልነበረውም። ሃብታም ሃገራት ክትባት ገዝተው የተረፋቸውን ለኮቫክስ መስጠት ጀመሩ።

“ኬንያ በመጀመሪያው ዙር 3 ሚሊዮን ክትባት ብትጠብቅም የደረሳት 1.1 ሚሊዮን ነው። ከዚያ በኋላ ለሶስት ወራት ምንም አልደረሳትም” ይላሉ የአፍሪካ ሕዝብና ጤና ጥናት ማዕከል ባልደረባ ዶክተር ካትሪን ኪዮቡቱንጊ።

የፈለገችው ክትባት በጊዜ ያልደረሳት ኬንያ የክትባት ዕቅዷን በየጊዜው መቀያየር ነበረባት። ይህ ደግሞ የክትባት ሂደቱ ላይ ተፅዕኖ አድርሷል ይላሉ ዶክተር ካትሪን።

“ሰዎች ለመውሰድ ዝግጁ በነበሩት ወቅት ክትባቱን ፍለጋ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ ነበር። ማነው ለመከተብ ሶስት ቦታዎች ለመሄድ ጊዜ ያለው?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

ባለፈው ጥቅምትና ኅዳር በርካታ ክትባት ወደ ኬንያ ገባ፤ ነገር ግን ዋና ከተማዋ ናይሮቢ ከሚኖሩ ሰዎች 40 በመቶ ብቻ ናቸው ክትባቱን ያገኙት። በርካታ ገጠራማ ሥፍራዎች ደግሞ 5 በመቶ ብቻ።

“አሁን ጥያቄው እነዚህ ክትባቶች በሚቀጥለው ወር ከጥቅም ውጭ ሲሆኑ ምን ይሆናል የሚለው ነው። ወደነበርንበት ልንመለስ ነው ማለት ነው።” ይላሉ ዶክተር ካትሪን።

ኡጋንዳ ግማሽ ሚሊዮን ገደማ የሞደርና ክትባት ባለፈው ጥር ከጥቅም ውጭ በመሆኑ ምክንያት አስወግዳለች። ናይጄሪያ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ከጥቅም ውጭ የሆነ ክትባት በታኅሣሥ ወር ለማስወገድ ተገዳለች።

ከአንድ ቢሊዮን ክትባት አንድ ሶስተኛው እስካሁን ጥቅም ላይ አልዋለም። ምን ያክሉ ከጥቅም ውጭ እንደሆነ ግልፅ አይደለም።

አንዳንድ የአህጉረ አፍሪካ ሃገራት ክትባት ለመግዛት ሞክረው አልተሳካላቸውም። ልክ እንደ ኮቫክስ በትዕዛዝ መምጣት የነበረባቸው ክትባቶች ውሃ በልቷቸዋል።

በዚህ ውጥንቅጥ መካከል ቫይረሱ እንዲዛመት እና አዳዲስ ዝርያ እንዲያበቅል ሆኗል።

ዶክተር ካትሪን በፍጥነት መንቀሳቀስ የሚያዋጣ ነው ይላሉ። “ሁሉንም ሰው ለመከተብ እስከ ሚቀጥለው ዓመት ድረስ መጠበቅ መፍትሄ አይሆንም” ባይ ናቸው።

ክትባት የሚቋቋሙ አዳዲስ የኮቪድ ዝርያዎች ከመጡ ቀድሞ ወደነበርንበት ማጥ ውስጥ ተመልሰን ልንገባ ነው ሲሉ በርካታ ሙያተኞ ስጋታቸውን ይገልጣሉ።

በዓለም ዙሪያ ክትባቱ በፍጥነት እንዲሰራጭ ከተፈለገ እንዴት እንደሚመረት መረጃውን በማጋራት አቅም ያላቸው ሃገራት ክትባቱን እንዲያመርቱ ማድረግ ብቸኛው አማራጭ ነው ይላሉ።

በዚህ ሐሳብ የዓለም ጤና ድርጅት ይስማማል። የድርጅቱ ኃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም ባለፈው ሳምንት ደቡብ አፍሪካ ነበሩ።

ዶ/ር ቴዎድሮስ ወደሥፍራው ያቀኑት በድርጅታቸው የሚደገፍ አንድ ፕሮጀክት ሞደርና የተሰኘውን ክትባት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለማምረት የሚያደርገውን ጥረት ለመጎብኘት ነው።

የፕሮጀክቱ ሳይንቲስቶች ሞደርናን ለመቅዳት ያደረጉት ሙከራ ተሳክቶላቸዋል።

ፋይዘር የተሰኘው ክትባት አምራች ግን ክትባቱ እንደሚመረት አልናገርም ሲል አሻፈረኝ ብሏል። ይህ የድርጅቱ እምቢተኝነት በርካታ የዘርፉ ሰዎችን አስቆጥቷል።

ነገር ግን ድርጅቱ አፍሪካ ውስጥ የሚደረገውን ክትባት የማምረት ሙከራ “እደግፋለሁ” ብሏል።

ምንም እንኳ ፋይዘር የተሰኘው ክትባት በጣም ውዱ ቢሆንም ለበርካታ የዓለም ሃገራት ድጋፍ በመደረግ ቅድሚያውን ይዟል።

በርካታ ድጋፍ በማድረግ ቅድሚያ የያዙት ደግሞ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ናቸው።

ኤይርፊኒቲ የተሰኘው ተቋም ፋይዘር እስካሁን ከክትባት ያገኘው ገቢ ከ2.4 ቢሊዮን በላይ ዶላር ይገመታል ይላል። ሞደርና ደግሞ 2.1 ቢሊዮን ዶላር። በተነፃፃሪ አስትራዜኔካ ክትባቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ነው ለገበያ ያቀረበው።

ሞደርና ይህን ያህል ትርፍ ከክትባት አጋብሶ እንደሆን በቢቢሲ ቢጠየቅም ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል። ፋይዘር ደግሞ መረጃው የተዛባ ነው ብሎ አንድ ቢሊዮን ክትባቶችን ትርፍ በሌለው ዋጋ ለመሸጥ ከአሜሪካ መንግሥት መስማማቱን ገልጧል።