19 የካቲት 2022

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት ከትግራይ ጋር በሚዋሰነው የአፋር ክልል ነዋሪ የሆኑት አቶ ሁሞ ኢብራሂም ከቀናት በፊት በተፈጸመ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሚስታቸውንና አምስት ልጆቻቸውን አጥተው እጅግ ከባድ ሐዘን ውስጥ ናቸው።
ባለፈው ማክሰኞ የካቲት 08/2014 ዓ.ም ምሽት ላይ ተፈፀመ በተባለው የከባድ መሳሪያ ጥቃት አስር የአንድ ቤተሰብ አባላት መገደላቸውንና ሌሎች 13 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን ከአካባቢው የወጡ ሰዎችና የበጎ ፈቃደኛ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በጥቃቱ አስር የቤተሰብ አባሎቻቸው የተገደሉባቸው አቶ ሁሞ እና ቤተሰባቸው ይኖሩ የነበረው በአፋር ክልል ውስጥ በምትገኘው አዳ የምትባል ትንሽ ከተማ ነበር።
ከተማዋ ከበርሃሌ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ እንደሆነች በሰመራ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የአቶ ሁሞ የቅርብ ዘመድ አቶ ያሲን ከድር ለቢቢሲ ገልጸው፤ አጠቃላይ ዘመድ በከባድ ሐዘን ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በጥቃቱ ልጆቻቸውን ይዘው በመሸሽ ላይ ከነበሩት የቤተሰብ አባላት መካከል አምስት ህጻናት፣ እናት፣ የእናት እናት [አያት]፣ የእናት ወንድም እና የአባት እህት ሁለት ልጆች መሆናቸው ተገልጿል።
አባወራው አቶ ሁሞ ቀድመው ከአካባቢው ተፈናቅለው ወጥተው ስለነበር በቤተሰባቸው ላይ ከደረሰው አደጋ ሊተርፉ ችለዋል። ሙሉ ቤተሰባቸውን ያጡት አባት ሐዘኑን ሊቋቋሙ በማይችሉት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
“ምግብ አይበሉም። እንደ ድንገት የወረደባቸውን መዓት መቋቋም አልቻሉም። የሃይማኖት አባቶች እያጽናኑዋቸው ነው” ሲሉም ከባድ የሃዘን ስሜት ላይ መሆናቸውን አቶ ያሲን ተናግረዋል።
ቢቢሲ አቶ ሁሞ ኢብራሂምን ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም በደረሰባቸው መሪር ሐዘን ምክንያት ከማንም ጋር እንደማይነጋገሩ ዘመዶቻቸው ገልጸዋል።
አሁንም ድረስ በአካባቢው ከባድ ጦርነት እየተካሄደ በመሆኑና የስልክም ሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ በጥቃቱ ስለተገደሉት ሰዎች ታውቆ መርዶው የተሰማው በማግስቱ ነው።
ስለሞቱት ሰዎች መረጃ የተገኘው ከጥቃቱ ከተረፉ ቁስለኞችና ከተፈናቃዮች መሆኑን የሚናገሩት አቶ ያሲን፣ በጥቃቱ ሌሎች 13 ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የከፋ ጉዳት ያጋጠማቸው በዱብቲ ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል።
- የጂቡቲ መስመርን ዒላማ ያደረገ ጥቃት በህወሓት እንደተከፈተበት የአፋር ክልል ገለጸ
- አምነስቲ የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ከጦር ወንጀል ጋር የሚስተካከል ድርጊት ፈጽመዋል አለ
- ዩኒሴፍ አፋር ውስጥ የተፈፀመው ጥቃት ‘እንዳስደነገጠው’ ገለፀ
አካባቢው የጦርነት ቀጠና እንደሆነ የተናገሩት አቶ ያሲን ጥቃቱ የደረሰው “እነዚህ ቤተሰቦችን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ጦርነቱን ሽሽት ከበርሃሌ ዶዶም ወደ ተባለው በረሃ እየሸሹ ነበር” ብለዋል።
ጥቃቱ ያጋጠመው ይኖሩበት ከነበረው አዳ ከተባለው ከተማ 5 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዘው አላ ከሚባል ወንዝ ጥቂት ወጣ ብሎ ባለ ቦታ ላይ ነው ተብሏል።
በወንዙ ጎዳያ የሚባል ታዋቂ ፍልውሃ ያለ ሲሆን ከትግራይም ከአፋርም ሰዎች እየመጡ ፈውስ ለማግኘት ይጠቀሙበታል የሚሉት አቶ ያሲን “በጉዟቸው ላይ ምናልባትም አረፍ ባሉበት ይሆናል ጥቃቱ የደረሰው” ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል።
“ጥቃቱ በከባድ መሣሪያ የተፈጸመ ስለሆነ በአንድ ጊዜ ነው ያለቁት፤ ከቆሰሉት ሰዎችም መካከል እግርና እጃቸው ያጡ አሉ” በማለት ሟቾቹ እዚያው በጥቃቱ ከተገደሉበት ስፍራ መቀበራቸውንም ገልጸዋል።
ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች የተዛመተው ጦርነት ለተወሰነ ጊዜ ጋብ ያለ መስሎ ከአንድ ወር በፊት አንስቶ አፋርና ትግራይ በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች መቀጠሉ ይታወቃል።
ይህ ጦርነት በህወሓት ኃይሎች ጥቃት ተሰንዝሮብናል በሚል በከባድ መሳሪያ በመታገዝ በአፋር ክልል ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፣ ውጊያው አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የህወሓት ጥቃት ሰርዶን በመያዝ የኢትዮ ጂቡቲ መተላለፊያ መስመርን ለመቆጣጠር ዒላማ ያደረገ መሆኑን የአፋር ክልል ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በዚህ መግለጫው የህወሓት አማጺያን የአብአላ ወረዳን፣ የመጋሌ ወረዳን፣ የኤረብቲ፣ የኮነባ እና የበራህሌ ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን መግለጹ ይታወሳል።
የአፋር ክልል ባለሥልጣናት እንደሚሉት በክልሉ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ ቤት ንብረታቸውን ትተው የተፈናቀሉ ሰዎች ከ350 ሺ በላይ መሆኑን ከሳምንት በፊት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ነዋሪዎችና ከጦርነት ቀጠናዎች ተፈናቅለው ያሉ ዜጎችን በመርዳትና በማስተባባር ላይ የሚገኝ በጎ ፈቃደኛ ሳድቅ በድሩ አሁንም ጦርነቱ ተባብሶ መቀጠሉንና የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል።
“አፍዴራ እና ኩሪ ወረዳ ያሉት መውጣት የቻሉ ናቸው፤ መውጣት ያልቻሉ ግን በዚያው በጦርነት ቀጠና ውስጥ ነው ያሉት” ብሏል በጎ ፈቃደኛው ለቢቢሲ።
ጦርነቱን ሽሽት ሲወጡም በረሃ ላይ ያለምንም እርዳታ የወለዱ እናቶች መኖራቸውንና ጨቅላ ሕጻናትን ጨምሮ ሴቶች የከፋ ችግር ላይ መሆናቸውን በጎ ፈቃደኛው ለቢቢሲ ተናግሯል።
ህወሓት ቀደም ሲል በአፋር ኃይሎች በተደጋጋሚ በተፈፀመበት ጥቃት ምክንያት ጠንካራ እርምጃ መውሰዱንና የተወሰኑ ቦታዎችን መቆጣጠሩን ገልጾ ነበር።
በአፋር ክልል የሚካሄደው ውጊያ ላይ የፌደራል ሠራዊት አለመሰማራቱንና ውጊያው በአፋር ልዩ ኃይል እና በህወሓት አማጺያን መካከል እተካሄደ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ የኃይል መመጣጠን ባለመኖሩ “በሕዝቡ ላይ” ከባድ ጥቃት እየተፈፀመ ነው ብለዋል።
የፌደራል መንግሥቱ በአፋር ክልል ስላለው ጦርነት እስካሁን ያለው ነገር ባይኖርም፤ ከዚህ ቀደም የአገሪቱ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት በህወሓት በኩል ለሚፈጸሙ ጥቃቶች አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ መግለጹ ይታወሳል።