የደቡብ አፍሪካ አዲሱ ሕግና የኢትዮጵያዊያን ሥጋት
በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባትና የሚሠሩባት የደቡብ አፍሪካ ጆሐንስበርግ ከተማ አንደኛው ክፍል

ፖለቲካ

20 February 2022

ዮናስ አማረ

ከማኅበራዊ የትስስር ገጾች ባለፈ በአንዳንድ ዋና ዋና በሚባሉ የዜና አውታሮች ጉዳዩ ለኢትዮጵያዊያን ሥጋት ተብሎ ሲቀርብ ከርሟል፡፡ በተለይ አንዳንድ የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኞች በጥቂት የውጭ ሠራተኞች ቀጣሪ ተቋማት ተዟዙረው ፍተሻ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ የተነሱ ግርግሮች ነገሩን ጎልቶ እንዲነሳ አድርገውታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በውጭ ሠራተኞች ላይ አወጣችው የተባለው አዲሱ ሕግ በብዙዎች ዘንድ ሥጋት አሳድሯል፡፡

በውጭ ዜጎች ላይ ዒላማ ባደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች፣ ‹‹በመጤ ጠል›› ተቃውሞዎችና ስደተኞችን በተመለከቱ የፖለቲካ ውዝግቦች ስሟ ሲጠቀስ የቆየችው አገር፣ የሰሞኑን ሕግ ተከትሎ ዳግም የዜና ርዕስ ሆናለች፡፡ በዚያው በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ብቻ ሳይሆን በአገር ቤት ካሉ ወገኖች እንደሚደመጠው፣ በ‹‹መጤ ጠል›› የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚታሙ የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኞች ‹‹የዜኖ ፎቢያ›› መንፈስ ያለው ሕግ በውጭ አገር ሠራተኞች ላይ ለመደንገግ እየተንቀሳቀሱ ነው የሚለው ዜና ጎልቶ ሲያስተጋባ ነው የከረመው፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን፣ በራሳቸው ደቡብ አፍሪካዊያን ዘንድም የሚቃረን ሐሳብ እየቀረበበበት ያለ ጉዳይ ሆኖ ነው የከረመው፡፡

ብሉምበርግ፣ ቢዝነስቴክና ሌሎችም ዋና ዋና መገናኛ ብዙኃን ከሳምንት በፊት፣ ‹‹ደቡብ አፍሪካ የውጭ ሠራተኞችን በኮታ ልትገድብ ነው፤›› የሚል ዘገባ ይፋ አድርገዋል፡፡ አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ይህንኑ ጉዳይ ሲዘግቡም የደቡብ አፍሪካ ዜጎች በመጤ (ስደተኛ) ሠራተኞች የሥራ ዕድል እያጡ ነው ያሉ የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኞች፣ የውጭ ዜጎችን ቁጥር በኮታ የሚገድብ ሕግ ለመተግበር እየተንቀሳቀሱ ነው የሚል አንድምታ ባለው መንገድ ነበር መረጃውን ያሠራጩት፡፡

የደቡብ አፍሪካው ዕውቁ የቴሌቪዥን ጣቢያ ‹‹ኢ ኒውስ ቻናል አፍሪካ›› (eNCA) እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 26 ቀን ይህንኑ የውጭ ሠራተኞችን አዲስ ሕግ በተመለከተ የውይይት ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በውይይቱ ከተሳተፉት አንዱ በሠራተኞችና በስደተኞች ጉዳይ ባለሙያ ተብለው የቀረቡት ቲኦ ስፓራቡም፣ ደቡብ አፍሪካ ሕጉን ለማውጣት የተገደደችባቸውን ምክንያቶች ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

‹‹ደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ሕግ ፈራሚ አገር ናት፡፡ አገሪቱ የደቡብዊ አፍሪካ አገሮች የልማት ማኅበረሰብ (SADC) አባል በመሆኗ፣ የቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሠራተኞች ስምምነቶችን ተቀብላ ተግባራዊ ታደርጋለች፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከዓለም አቀፉ አሠራር ጋር የሚጣጣም የውጭ ሠራተኞች አያያዝ እንዲኖራት ታስቦ ነው ሕጉ የተዘጋጀው፤›› በማለት ነበር ባለሙያው ያብራሩት፡፡

በባለሙያው ማብራሪያ እንደተመለከተው ሕጉ ሰነድ አልባ ስደተኞችን/ሠራተኞችን ከመጉዳት ይልቅ፣ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ አገሪቱ የውጭ ዜጎች የሥራ ሥምሪትን ለመቆጣጠር፣ እንዲሁም የሠራተኞች የሥራ ደኅንነትና ሕጋዊ መብቶች ለማስከበር ሲባል ሕጎቿን ከቀጣናዊና ከዓለም አቀፋዊ አሠራሮች ጋር ትይዩ በሆነ መንገድ ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘችው ነው ሕጉን ያዘጋጀችው በማለት ቲኦ ስፓራቡም አብራርተዋል፡፡  

በዚሁ የውይይት ዝግጅት ላይ አስተያየታቸውን ያጋሩት የአፍሪካን ሴንተር ፎር ማይግሬሽንና ሶሳይቲ (ASFMS) ተቋም ባልደረባው ሎረን ላንደው በበኩላቸው፣ በደቡብ አፍሪካ የሠራተኞች ሥምሪት ሕግ ችግር የለም ይላሉ፡፡ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ‹‹ሕግ ከማርቀቅ ይልቅ ሥራ ለዜጎች በመፍጠር ላይ ያተኩሩ፤›› ሲሉ ሎረን ይተቻሉ፡፡ ሎረን ሕጉን የሚገልጹት፣ ‹‹ሥራ ለዜጎች መፍጠር ያቃታቸው ሕዝበኛ (Populist) ፖለቲከኞች ያዘጋጁት ሕግ ነው፤›› በማለት ነው፡፡ በእሳቸው እምነት በደቡብ አፍሪካ አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በአገሪቱ የተሻለ የሥራ ዕድል ማግኘት፣ እንዲሁም ምቹ የሥራ አያያዝ ለዜጎች ሊመቻች ይገባል ሲሉም ባለሙያው ተከራክረዋል፡፡

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ያወጣው የውጭ ዜጎችን የሥራ ሥምሪት የተመለከተው አዲስ ሕግ፣ የተለያዩ ፅንፎች ባለው ዕይታ እየቀረበ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኞች ለደቡብ አፍሪካ ዜጎች መሠረታዊ የሥራ ዕድል ለማመቻቸት ብለው ሳይሆን፣ የውጭ ዜጎች ላይ ባሳደሩት ጥላቻና የተዛባ አመለካከት የተነሳ ነው ይህንን ሕግ ያወጡት የሚል ትችት በአንድ በኩል ይቀርባል፡፡ የደቡብ አፍሪካ የሥራ ሚኒስትር ቱላስ ዜሲ ግን ይህንን ያስተባብላሉ፡፡

‹‹ሠራተኛ የውጭ ዜጋ ወይም ዜጋ ተብሎ አይለይም፡፡ ሁሉም ሰው ሠራተኛ እስከተባለ ድረስ የሥራ ደኅንነቱ፣ መብቱና ጥቅማ ጥቅሙ እኩል እንዲከበርለት ሕጋችን ያስገድዳል፤›› ሲሉ ይናገራሉ የሥራ ሚኒስትሩ ቱላስ ዜሲ፡፡ ደቡብ አፍሪካ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፉ ሕጎችና ስምምነቶች ተፈጻሚ የማድረግ ግዴታ አለባት የሚሉት ሚኒስትሩ፣ ይህ ማለት ግን የዜጎቿን መሠረታዊ የሥራ ዋስትናና ጥቅማ ጥቅሞች አሳልፋ ትሰጣለች ማለት እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በአንዳንድ ዘርፎች ለአብነት በሬስቶራንቶች 90 በመቶ ድረስ የውጭ ዜጎች ይቀጠራሉ፡፡ በአንዳንድ መስኮች ደግሞ 30፣ 50 እና 70 በመቶ የሥራ ዕድሎችን ይይዛሉ፡፡ አንዳንድ ቀጣሪዎች ይህንን ክፍተት ተጠቅመው በርካሽ ደመወዝ መሥፈርት የማያሟሉ ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ የሌላቸው የውጭ ዜጎችን ወደ መቅጠር ይገባሉ፡፡ በየዘርፉ ያለውን ዜጎችና የውጭ ሠራተኞችን ቁጥር ለማመጣጠን ሲባል ነው አዲሱን ሕግ ማርቀቅ ያስፈለገው፤›› በማለት ነው ሚኒስትሩ ቱላስ ዜሲ የሕጉን አስፈላጊነት ለማስረዳት የሞከሩት፡፡

ደቡብ አፍሪካዊያውን እንደሚሉት ሕጉ የውጭ ዜጎችን ዒላማ አድርጎ የተዘጋጀ ካልሆነ፣ አፍሪካውያን ዜጎች የ‹‹ዜኖ ፎቢያ›› ጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው የሚለው ሥጋት እንዴት ሊከሰት ቻለ የሚለው ጥያቄ ያጋግላል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ የዘገቡ ሚዲያዎች በደቡብ አፍሪካ አዲስ የመጤ ጠል ጥቃት የተነሳ አስመስለው ጉዳዩን አቅርበውታል፡፡ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ ዓምደኞች የደቡብ አፍሪካ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያውያንን ከየሥራ ቦታዎች እየመነጠሩ ማስወጣት እንደጀመሩ አድርገው ጉዳዩን አቅርበውታል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ስደተኞች በተለይ አፍሪካውያን ሠርተው መኖር አልቻሉም የሚሉ ጩኸቶችም ከሰሞኑ በርትተዋል፡፡ ይህ ከሰሞኑ የተነሳ ሥጋት ደግሞ በተጨባጭ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ መኖር አለመኖሩን በሚመለከት፣ ጉዳዩን በቅርብ ያውቃሉ ከሚባሉ ወገኖች ለማጣራት ተሞክሯል፡፡

ስለዚህ ሰሞነኛ ውዝግብ ተከታታይ መረጃዎችን የሚያሠራጨውና በደቡብ አፍሪካ ስለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ የሚዘግበው የዩናይትድ ሚዲያ ሐውስ (United Media House) የፌስቡክ የዜና ገጽ መሥራች በኃይሉ መሐመድ፣ ኢትዮጵያውያንን ዒላማ ያደረገ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴም ሆነ ዕርምጃ በደቡብ አፍሪካ አለመወሰዱን ይናገራል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ለ21 ዓመታት የኖረችው የሕግና የማማከር ሥራ ባለሙያ ትዕግሥት ደሱ (ዶ/ር)፣ የደቡብ አፍሪካዊያኑ የሥራ ዕድል የማግኘት ጥያቄ ሥር የሰደደ ችግር መሆኑን ታስረዳለች፡፡ በዚያው በደቡብ አፍሪካ የኩባንያ ባለቤት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያዊያን ኮሙዩኒቲ አባል የሆኑና ስሜ አይጠቀስ የሚሉ ኢትዮጵያዊ ደግሞ የሰሞኑ ግርግር የተለየ ገጽታ ተሰጥቶትና ተዛብቶ ቀርቧል ነው የሚሉት፡፡

የደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሮን ሞትሶሌዲ እንደተናገሩት፣ ደቡብ አፍሪካ የውጭና የአገር ውስጥ ሠራተኞችን ድርጅቶች አመጣጥነው እንዲቀጥሩ የሚያደርግ ሕግ ነው ያረቀቀችው፡፡ ይህ ሕግ በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ሞትሶሌዲ፣ አገሪቱ ስደተኞችንና ከለላ ጠያቂዎችን የተመለከቱ ሦስት ተጨማሪ ሕጎችን ለማርቀቅ በሒደት ላይ መሆኗን አምነዋል፡፡

ሚኒስትሩ አሮን ሞትሶሌዲ እንደሚሉት፣ አገሪቱ እነዚህን ሕጎች የምታረቀው ዜጎቿን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንጂ የውጭ ዜጎችን ሰለባ ለማድረግ አይደለም፡፡ ‹‹በደቡብ አፍሪካ ድርጅት ያለው ሰው ፋብሪካም ይክፈት ምግብ ቤት ማንን መቅጠር እንዳለበት የሚደነግግ ሕግ አልነበረንም፡፡ አንድ ሰው መቶ በመቶ ከውጭ አገር ሠራተኞችን አምጥቶ ቢቀጥር የሚያግደው ነገር አልነበረም፡፡ ይህ ዓይነቱ አሠራር መቀየር አለበት፡፡ ደቡብ አፍሪካዊያን በኮታ መሠረት ሊቀጠሩ ይገባል ነው እያልን ያለነው፤›› ሲሉ ሞቶሶሌዲ ይናገራሉ፡፡

ይህ የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ማብራሪያ ግን ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ብዙ የውጭ ዜጎችን ያሳመነ አይመስልም፡፡ አገሪቱ ‹‹መጤ ጠል›› ሕግ ደነገገች በሚል ጉዳዩ ሲብጠለጠል የከረመው በዚህ ሥጋት የተነሳ ነው ይላሉ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ ወገኖች፡፡

በኃይሉ መሐመድ እንደሚለው ኢትዮጵያውያንን ለይቶ ያዋከበም ሆነ ስደተኞች ከአገር ካልወጡ ብሎ ዘመቻ የከፈተ አካል በደቡብ አፍሪካ የለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥትም ሆነ በሕግ የተደገፈ ስደተኞችን ዒላማ ያደረገ እንቅስቃሴም የለም፡፡

‹‹ከሰሞኑ የተነሳው ግርግር የውጭ ዜጎች ወንጀል ይፈጽማሉ፣ ሥራችንን ያቆማሉ፣ እንዲሁም ንብረታችንን ነጥቀውናል የሚሉ ጥቂት ፖለቲከኞችና ግለሰቦች የፈጠሩት ነው፤›› ሲል ይናገራል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ኮሽ ባለ ቁጥር ግርግር መፈጠሩ የተለመደ ነው የሚለው በኃይሉ፣ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ከተዛባ መረጃ እንዲጠብቁና ራሳቸውን ለአደጋ እንዳያጋልጡ ነው የሚመክረው፡፡

በኃይሉ ይህንን ሲልም ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች አስፈላጊውን ፈቃድ የማግኘት ጥረታቸውን ማፋጠን አለባችው ይላል፡፡ ከዚህ ውጪ ኢትዮጵያዊያኑ በሚንቀሳቀሱበትና በሚሠሩበት ሁሉ ፈቃድ ወይም ዶክመንቶቻቸውን ይዘው እንዲንቀሳቀሱም በኃይሉ ያሳስባል፡፡

‹‹ከ30 በመቶ በላይ ሥራ አጥ ዜጋ ያለው አገር ዜጎቹ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው የሚያደርግ የኮታ ሕግ ቢያዘጋጅ አይገርምም፤›› የምትለው ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ትዕግሥት (ዶ/ር) በበኩሏ፣ የደቡበ አፍሪካዊያኑ ጥያቄ ኢትጵያዊያን ላይ የሚያስከትለው ጎጂ ተፅዕኖ አለመኖሩን ታስረዳለች፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በእሷ እምነት 95 በመቶ የሚሆኑት የራሳቸውን ንግድና ቢዝነስ ፈጥረው የሚሠሩ እንጂ፣ የደቡብ አፍሪካዊያኑን የሥራ ዕድል የሚሻሙ ተቀጣሪዎች አይደሉም፡፡

‹‹ከዛምቢያ፣ ከታንዛኒያ፣ ከዚምባብዌና ከማላዊ የሚፈልሱ ዜጎች ብዙኃኑ በደቡብ አፍሪካዊያን ዜጎች ሊሸፈኑ የሚችሉ አነስተኛ የሥራ ቅጥሮችን በስፋት ይይዙታል፤›› ስትል የምትገልጸው ትዕግሥት (ዶ/ር)፣ ደቡብ አፍሪካዊያን በእነዚህ ቅጥሮች በኮታ የሥራ ዕድል ያግኙ መባሉ በውጭ ዜጎች ጠልነት ሊፈረጅ የማይችል መሆኑን ነው የምታስረዳው፡፡

ስሜ አይጠቀስ ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ ደቡብ አፍሪካዊያኑ የሥራ ቅጥር ምጣኔው 60 በመቶ ለአገሬው፣ 40 በመቶ ደግሞ ለውጭ ዜጋ እንዲሆን በሕግ ከመደልደል ውጪ ያደረጉት ሌላ አዲስ ነገር አለመኖሩን ነው ያስረዱት፡፡ ከዚህ ውጪ ጉዳዩ የፖለቲከኞች ፍጆታ እንዲሆን ታስቦ እየተራገበ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ ‹‹በደቡብ አፍሪካ ምርጫ ደርሷል፡፡ ምርጫ በደረሰ ቁጥርም የፖለቲካኞቹ የሥራ ዕድል እንፈጥራለን፣ መጤዎችን እናስወጣለን እያሉ ለፖለቲካ ትርፍ መራወጥ የተለመደ ነው፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ያክላሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው እምነት የሰሞኑ ግርግር በተዛባ መንገድ የቀረበ መረጃ እንጂ፣ በተጨባጭ ለኢትዮጵያውያን ሥጋት የሆነ ጉዳይ አይደለም፡፡

‹‹በቅርቡ ሑዋዌ በተባለ አንድ ኩባንያ 90 በመቶ የውጭ ሠራተኞች፣ አሥር በመቶ የአገሬው ዜጎች ሲሠሩ ተገኙ፡፡ ይህንን ተከትሎ የውጭ ዜጎች በደቡብ አፍሪካ በከፈቷቸው ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ቁጥርና ማንነት ካልተጣራ የሚል የፖለቲካ ውዝግብ ተነስቷል፤›› ሲሉ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው፣ ነገሩ ሲዘገብ ግን ‹‹ዜኖ ፎቢያ›› ተቀሰቀሰ ይላሉ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያውያን ሥጋት ላይ ወደቁ የሚል ገጽታን መያዙን ያስረዳሉ፡፡