ከ 4 ሰአት በፊት

ዩክሬን ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ጦሱ እዚያው የሚያበቃ አይደለም። የተለያዩ የዓለም ክፍሎችን መንካቱ ስለማይቀር የአፍሪካ አገራትንም በተለያየ ሁኔታ ይመለከታቸዋል።
የአፍሪካ አገራት ከሩሲያና ከዩክሬን ጋር ምጣኔ ሀብታዊና ወታደራዊ ግንኙነቶች ስላላቸው ጦርነቱ የሚያስከትላባቸው ጫና ይኖራል።
በተለይ ደግሞ ሩሲያና ምዕራባዊያን የእፍሪካ አገራት ከጎናቸው እንዲቆሙ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ማሳደራቸው አይቀርም።
አስካሁን ጦርነቱን በተመለከተ ከአፍሪካ አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ጋና እና ጋቦን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ዘመቻ አውግዘው በይፋ ተቃውመዋል።
አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ግን ዝምታን የመረጡ ሲሆን፣ በይፋ ወጥቶ ከሩሲያ ጎን በመቆም ድጋፉን የገለጸም የለም።
ነገር ግን የሱዳን ኃያሉ ወታደራዊ ጄነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጎሎ (ሔሜቲ) ጦርነቱ በተጀመረበት ዕለት ለጉብኝት ሞስኮ ገብተዋል።
የጄነራሉ ጉብኘት በሱዳን መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ በአገሪቱ የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር መቀልበሱን ተከትሎ ምዕራባውያን በሱዳን ወታደራዊ መሪዎች ላይ ፊታቸውን በማዞራቸው ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር መሆኑ ተገልጿል።

ጦርነቱ አፍሪካውያንን እንዴት ሊጎዳ ይችላል?
በዩክሬንና በሩሲያ መካከል ያለው ፍጥጫ መባባሱን ተከትሎ በበርሜል የነዳጅ ዋጋ ከ100 ዶላር በላይ ሆኗል። ይህም ከስድስት ዓመት ወዲህ ከፍተኛው ነው።
በነዳጅ ዋጋ መጨመር ናይጄሪያንና አንጎላን ጨምሮ ነዳጅ አምራች የሆኑ ጥቂት የአፍሪካ አገራት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ያደርጋል።
ነገር ግን በመላዋ አህጉሪቱ የትራንስፓርት ዋጋን እንዲጨምር ከማድረግ በተጨማሪ የሌሎች ምርቶችን ዋጋ በማናር የተራውን ሕዝብ ኑሮ የበለጠ ያስወድደዋል።
በተጨማሪም በዓለም ላይ ለገበያ ከሚቀርበው የስንዴ ምርት 30 በመቶውን የሚያቀርቡት ሩሲያና ዩክሬን በመሆናቸው በአቅርቦት ላይ በሚፈጠር መስተጓጎል በአፍሪካ ውስጥ የዳቦ ዋጋ ላይ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል።
ከዚህ በፊት እንደታየው ደግሞ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ለሚከሰቱ ተቃውሞውችና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የዳቦ ዋጋ መጨመር እንደምክንያት የሚቀርብ በመሆኑ፣ የስንዴ እጥረት የሚያስከትለው የዳቦ መወደድ በአፍሪካ አገራት ፖለቲካ ውስጥ አለመረጋጋት ሊያስከትል ይችላል ሲል የአፍሪካ ኮንፊደንሺያል አርታኢ ፓትሪክ ስሚዝ ይናገራል።
የኬንያ የሻይ ምርትን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን ከአፍሪካ የምትገዛው ሩሲያ የገንዘብ ዝውውር እቀባ ስለተጣለባት የአፍሪካ አምራችና ላኪዎች ገበያ ላይ እክልን ፈጥሮ ከፍተኛ ገቢን እንዲያጡ ሊያደርጋቸው ይችላል።
አፍሪካውያን በዩክሬን
በተለይ የሕክምና ትምህርትን ርካሽ በሆነ ክፍያ የከፍተኛ ትምህርት ፍለጋ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ዩክሬን ውስጥ ያሉ ሲሆን ሌሎች አፍሪካውያን ደግሞ ለሥራና ለኑሮ እዚያው ይገኛሉ።
ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ግን ደኅንነታቸው አሳሳቢ ሆኗል። የጋና የተማሪዎች ማኅበር መንግሥት ዜጎቹን እንዲያስወጣ ቢጠይቅም፣ የጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ዩክሬን ውስጥ የሚገኙ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎቹ በቤታቸውና በመንግሥት በተዘጋጁ መጠለያዎች ውስጥ እንዲቆዩ አሳስቧል።
ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለትምህርት ዩክሬን የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች አሉ። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪ ያላቸው አገራት ሞሮኮ (8,000)፣ ናይጄሪያ (4,000) እና ግብፅ (3,500) ሲሆኑ ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ዩክሬን ውስጥ እንደሚገኙ ቢቢሲ አረጋግጧል።https://www.bbc.com/ws/av-embeds/cps/amharic/news-60519864/p08k578f/amየተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,
ቭላድሚር ፑቲን ማን ናቸው- ሩሲያን በታሪክ ለረጅም ጊዜ የሚመሩ ሰው?