ኢዜማ ብልፅግና መራሹ መንግሥት የአገር ሰላም ማስከበር ተስኖታል አለ
የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋና ዋና ጸሐፊው አቶ አበበ አካሉ መግለጫ ሲሰጡ

ፖለቲካ

6 March 2022

ዮናስ አማረ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፖርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ባወጣው መግለጫ፣ ብልፅግና መራሹ መንግሥት የአገሪቱን ሰላም ማስጠበቅም ሆነ የዜጎችን በሕይወት የመኖር ዋስትና ለማስከበር አቅቶታል አለ፡፡

የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ዓርብ በፓርቲው ጽሕፈት ቤት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፓርቲያቸው ለአገር ሲባል ብዙ ችግሮችን ማለፉን አመልክተዋል፡፡ በአማራ ክልል፣ በደቡብ፣ እንዲሁም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ፓርቲው ማጥናቱን አስታውቀዋል፡፡

በፓርቲ አባሎችና በአመራሮቹ ላይ በመንግሥት በኩል ጫና እንደሚያደረግ ያስታወቀ ሲሆን፣ በተለይ በአማራ ክልል ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተከሰቱ ችግሮችን በጥናት መለየቱን ነው የተናገረው፡፡

ኢዜማ በዚሁ መግለጫው በዋናነት ከሕወሓት ወረራና ከህልውና ዘመቻው ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮችን፣ እንዲሁም የኦነግ ሸኔን ጥቃት የሚያስቆመው አካል ሊገኝ አለመቻሉን አስመልክቶ የደረሰበትን ድምዳሜ ለጋዜጠኞች ገልጿል፡፡ በአምስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላያ ያተኮረው የኢዜማ መግለጫ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የደረሰውን ድርቅ፣ በአፋር ክልል ሕወሓት እየፈጸመ ያለውን ዳግም ወረራና በደቡብ ክልል የተወሰኑ ወረዳዎች የማንነት ጥያቄን የተንተራሱ ግጭቶችን በዝርዝር መመልከቱን ነው፣ የፓርቲው አመራሮች በንባብ እንዲሁም በጥያቄና መልስ ለጋዜጠኞች ያብራሩት፡፡

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ መንግሥት በአገሪቱ የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ እያቃተው እንደመጣ የተናገሩ ሲሆን፣ የዜጎች በሕይወት የመኖር ዋስትና አደጋ ላይ መውደቅ ጉዳይን ፓርቲያቸው ከዚህ በላይ የሚታገስበት ዕድል አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የምንጠይቀው ጥያቄ የቅንጦት አይደለም፣ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት መሠረታዊ ጉዳይ እንጂ፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ የሺዋስ፣ የመንግሥት ግዴታ በመሠረታዊነት የዜጎችን ሕይወት መጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በብዙ ቦታዎች የመንግሥት ወይም የብልፅግና ሰዎች በኢዜማ አባላትና አመራሮች ላይ እንቅፋት እንደፈጠሩም አቶ የሺዋስ ዘርዝረዋል፡፡

‹‹በሰሜንና በደቡብ ወሎ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለአገር ህልውና መጠበቅ ዘመቻ በተሠለፉ አባሎቻችን ላይ ጭምር ችግር ተፈጥሮባቸዋል፡፡ ጉዳያችን ከመንግሥት እንጂ ከፓርቲ ጋር አይደለም፡፡ የሕወሓትና የኦነግ ሸኔ ጋብቻ የተግባር ነው፡፡ እንዲሁም መንግሥት ችግር ከመፈጠሩ በፊት ቢያጠራ ይሻላል፤›› የሚሉ ሐሳቦችን ያነሳሱት አቶ የሺዋስ፣ በአገሪቱ ላሉ ቀውሶች መንግሥትን በምክንያትነት አቅርበዋል፡፡

‹‹እዚህ አገር በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የፀጥታ ኃይሎችን ሊገዳደር የሚችል ፀረ ሰላም አካል የለም፡፡ ችግሩ የአሠራር፣ የፖሊሲ፣ የንዝህላልነት፣ ወይም ሥልጣንን የማስቀደም ሊሆን እንደሚችል ነው የምንረዳው፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ የሺዋስ፣ መንግሥት ራሱ ውስጥ ያሉትን ሕገወጦች ያፅዳ ብለዋል፡፡ ‹‹በጎንደር፣ በጅግጅጋም ሆነ በደቡብ ዞረናል፡፡ የሕዝቡን መሠረታዊ በሕይወት የመኖር ጥያቄ ስናነሳ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ አልገባንም የሚሉ መንግሥትነታቸውን የረሱ አመራሮች ጭምር አግኝተናል፤›› ሲሉ አገሪቱ የምትገኝበት የቀውስ ሁኔታን ዳሰዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ስለድርቁ አስተያየት የሰጡት የኢዜማው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ፣ ‹‹ድርቅ ተፈጥሮ ነው፣ ረሃብ ግን ስንፍና ነው ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የቀረበውን አስተያየት ኢዜማ አይቀበለውም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይህን ሁሉ ለም መሬትና ለልማት መሥራት የሚችል ብዙ ወጣት ሕዝብ ይዞ ረሃብ ስንፍና ነው ማለት አያስኬድም፡፡ ችግሩ የፖሊሲ መሆኑን ነው የምንረዳው፤›› ብለዋል፡፡  

በዚሁ ዕለት የፓርቲውን መግለጫ በንባብ ያሰሙትና ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የኢዜማ ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ‹‹ኢዜማ ለጭብጨባ የሚሮጥ ፓርቲ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገሮችን በተረጋጋ ሁኔታ ለመመልከት ብለን ብዙ ታግሰናል፤›› ያሉት አቶ አበበ፣ ‹‹አገር ትሻገር ብለን ብልፅግናን ጀርባችን እስኪጎብጥ ተሸክመነዋል፤›› ሲሉ ጠንከር ባለ ቃል መንግሥት መራሹን ፓርቲ ተችተዋል፡፡

በአማራ ክልል በቅድመ ጦርነት፣ በጦርነትና በድኅረ ጦርነት ወቅት ያሉ ሁነቶችን በጥልቀት አጥንተናል ያሉት አቶ አበበ፣ ‹‹አምበር በተባለ ቦታ ለህልውና ዘመቻው ሲዋደቅ የሞተ አመራራችንን መሬት ፆም አሳድረው የራሳቸውን ሰዎች እርሻ የሚያሳርሱ አሻጥረኛ አመራሮች ናቸው በአማራ ክልል የሞሉት፤›› ብለዋል፡፡ ክልሉ በጦርነቱ ከባድ ፈተና ባጋጠመውና ሕዝቡ ፈተና ላይ በወደቀ ወቅት አካባቢያቸውን ጥለውና የአገር ሀብት ተከፋፍለው የጠፉ አመራሮች፣ ዛሬ የድል አጥቢያ አርበኛ ሆነው የኢዜማ ሰዎችን እያሰቃዩ ናቸው በማለት ኮንነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ መከራ መሸከሙን ያወሱት አቶ አበበ በደቡብ ክልል በደራሼ፣ በአሌ፣ በጉማይዴና በኮንሶ በመሳሰሉ አካበቢዎች ግጭት እየደረሰ ያለውና ሰው የሚሞተው ራሱ የአካባቢው አመራር በሚፈጥረው ችግር መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በመግለጫው ወቅት በተለይ የኢዜማን ትይዩ ካቢኔ የተመለከቱ ጉዳዮችን በተመለከተ የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ትዕግሥት ወርቅነህ በበኩላቸው፣ የኢዜማ ትይዩ ካቢኔ ብዙ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን አውስተዋል፡፡ ‹‹ትይዩ ሚኒስትሮቻችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ሥራዎችን እንዲሠሩ ለማድረግ በሥራቸው ቡድን ተዋቅሯል፤›› ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ፣ የተለያዩ ዶክመንቶችንም በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በአገራዊ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች ላይ ግምገማዎች በማድረግ የማሻሻያ ሐሳቦችና ሂሶችን ያካተቱ ዶክመንቶችን ኢዜማ አዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ በመሬት ወረራ ላይ አዲስ ዶክመንት መዘጋጀቱን፣ እንዲሁም በፋይናንስ ዘርፍ የውጭ ድርጅቶች መሰማራት ጉዳይ ዙሪያ ዶክመንቶች መዘጋጀታቸውን ያመለከቱት ትዕግሥት፣ ፓርቲያቸው ከሰባት ያላነሱ ጥናቶችና ዶክመንቶችን አዘጋጅቶ ማጠናቀቁንና በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡