11 መጋቢት 2022, 10:48 EAT

እስከ ዛሬ በኮቪድ-19 ተህዋሲ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሚባለው በሦስት እጥፍ አሃዝ እንዳለው ተመላከተ።
በዚህ አዲስ አሃዝ መሠረት በዓለም ዙርያ 18 ሚሊዮን ሰዎች በተህዋሲው ሕይወታቸውን አጥተዋል የሚል ግምት ተወስዷል።
ይህ አዲስ ጥናት ይፋ የሆነው የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19ን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ብሎ ከጠራው ከሁለት ዓመት በኋላ ነው።
በዋሺንግተን ዩኒቨርስቲ መሪነት በተደረገው በዚህ መጠነ ሰፊ ጥናት 191 አገራት የተካተቱ ሲሆን ዓላማውም በተህዋሲው በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሞቱ ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር ማፈላለግ ነበር።
ይህን ጥናት ማድረግ የተፈለገው በርካታ ሞቶች ቢከሰቱም ምን ያህል ከኮቪድ-19 ተህዋሲ ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ለማመቅ ሳይቻል በመቅረቱ ነው።
ይህም የሆነው ተህዋሲው ወደ ሰውነት ሲገባ ሌሎች ከዚያ ቀደም የነበሩ ጽኑ ደዌዎችን የማባባስ ሁኔታ ስላለው ነው።
ከዚያ በኋላ ሞት ሲከሰት ግን በተህዋሲው ስም ሳይመዘገብ የሚቀርበት ሁኔታ በመኖሩ ነው።
በተለይ የልብና የሳምባ በሽተኞች ተህዋሲው ከመጣ በኋላ በስፋት ሞታቸው ተፋጥኗል ተብሎ ይገመታል።
የጥናቱ ሥነ ዘዴ ምን ያህል ተጨማሪ ሰዎች ሞቱ በሚል የተመራ ሲሆን ይህም ማለት ኮቪድ ከመምጣቱ በፊት የሟች ቁጥርን በየአገሩ በአማካይ በመውሰድ ከኮቪድ በኋላ ከመጣው ቁጥር ጋር ማነጻጸር ነው።
ይህን ለማሳካትም አጥኚዎቹ ከኮቪድ በፊት የሞት ቁጥርን ፍለጋ በርካታ የድረ ገጽ ዶሴዎችን፣ የጤና ሚኒስትር መረጃዎችን በየአገሩ ፈትሸዋል።
በዚህ ጥናት መሠረት ታዲያ የሞት ምጣኔ ከአገር አገር ቢለያይም የዓለም የሞት ምጣኔ መጨመሩን ደርሰውበታል።
የመጨመሩ ምሥጢር ግን ቀጥታ ኮቪድ ያመጣው ወይም በተዘዋዋሪ የዳረገው መሆኑ ሳይሰነድ በመቆየቱ የኮቪድን ትክክለኛ ጉዳት ማወቅ ሳይቻል ቆይቷል።
በዚህ ስሌት መሠረት አጥኚዎቹ ከኮቪድ በፊት የነበረ የሞት ምጣኔን ከዚያ በኋላ ከተሰከሰተ የሞት ምጣኔ ጋር አነጻጽረው በዓለም ዙርያ በትንሹ 18 ሚሊዮን ተጨማሪ ሞቶች መመዝገባቸውን ደርሰውበታል።
በይፋ እስከ ዛሬ ሲነገር የነበረው በኮቪድ በዓለም ደረጃ የሟቾች ቁጥር 5.9 ሚሊዮን ሲሆን አሁን በዚህ ጥናት መሰረት ግን ቁጥሩ በሦስት እጥፍ አድጎ ወደ 18 ሚሊዮን አሻቅቧል።
ይህ ጥናት በላንሴት የጤና ጆርናል ላይ የታተመ ሲሆን ከፍተኛ ሞት የተመዘገበባቸው በዋናነት በድሃ አገራት ውስጥ መሆኑን አመላክቷል።
በተለይም በላቲን አሜሪካና ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ሞት ተንሰራፍቶ ነበር ይላል ጥናቱ።
ከኮቪድ መምጣት በኋላ በርካታ ሞት የተመዘገበባቸው አምስት አገራት ቦሊቪያ፣ ቡልጋሪያ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሰሜን መቄዶኒያና ሌሴቶ ናቸው።
ኮቪድን ተከትሎ ዝቅተኛ የሞት ምጣኔ የታየባቸው አገራት ደግሞ አይስላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ሲንጋፖር፣ ኒዊዝላንድ እና ታይዋን ናቸው።
የጥናቱ መሪ እንዳሉት በስዊድንና በኔዘርላንድስ በተደረጉ የመረጃ ትንታኔ ጥናቶች በርካታ ሰዎች ከኮቪድ በኋላ የመሞታቸው ምስጢር ተህዋሲው ቀደም ሲል የነበረ በሽታን አፋፍሞ ለሞት አፋፍ የሚዳርግ ስለሆነ ነው።
የጥናቱ መሪ ወደፊት ምን ያህል ሞቶች በትክክል በኮቪድ በቀጥታ የተከሰቱ ናቸው፤ ምን ያህሎቹስ ኮቪድ ተህዋሲ በተዘዋዋሪ ያመጣቸው ናቸው፣ የሚለው ይጠናል ብለዋል።
የዚህ ጥናት ተመራማሪዎች በሚቀጥሉት ዓመታት ክትባት ሥርጭት በስፋት በመኖሩ እና ሕክምና እየተሻሻለ በመምጣቱ በብዙ አገራት የሞት ቁጥር በአያሌው ይቀንሳል ብለው ያምናሉ።
ሆኖም ግን ተህዋሲው በአዲስ ዝርያ አይከሰትም ብሎ ለመደምደም ጊዜው ገና ነው ባይ ናቸው።