13 መጋቢት 2022, 08:16 EAT
የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባዔውን እያካሄደ የሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ በሰሜን ኢትዮጵያ ላለፉት አስራ ስድስት ወራት እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለመቋጨት ማንኛውንም የሰላም አማራጭ እንደሚጠቀም አስታወቀ።
ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ይህንን ያለው በትናንትናው ዕለት እያካሄደ ባለው አንደኛ ጉባዔ ላይ የተወያየባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው።
የፓርቲው የሕዝብና የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫቸው “አሉ የተባሉ የሰላም አማራጮችን በሙሉ አሟጦ በመጠቀም . . .ችግሩን ለመቅረፍ መስራት እንደሚጠበቅበት” ከስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።
ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ በዚሁ መግለጫቸው ላይ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ቡድን አቋም ምክንያት ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት ብልጽግና ፓርቲ በማንኛውም የሰላም አማራጭ ሁኔታውን ለመቋጨት እንደሚሰራ ከስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ከቢቢሲ ኒውስ አወር ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአፍሪካ ሕብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በኬንያ አማካኝነት በተዘዋዋሪ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ገልፀው ነበር።
- ከመንግሥት ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ተናገሩ
- የብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ ምን ይዞ ይመጣል?
- የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ፍጻሜ የት ሊሆን ይችላል?
እነዚህ ቀጥተኛ ያልሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች እየተካሄዱ መሆናቸው ከተነገረ ጥቂት ወራት የተቆጠሩ ቢሆንም አስካሁን ያመጡት ተጨባጭ ውጤት የለም።
አርብ ዕለት በተጀመረው የፓርቲው የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ ቅዳሜ ውይይት የተደረገባቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ የማዕከላዊ ኮሚቴ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበትና እንደጸደቀ የተገለፀ ሲሆን በዚህ ሪፖርት በዋናነት የአገሪቱ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ መካተቱን ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያካሄደውን ጠቅላላ ጉባዔ መጋቢት 02/2014 ዓ.ም፣ አርብ ዕለት በደማቅ ዝግጅት የጀመረ ሲሆን፣ ከ1500 በላይ አባላቱ እየተሳተፉበት ነው።
“የትግራይ ሕዝብ አካላችን፣ ወንድማችን፣ እህታችን” ነው ያሉት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ “በዚህም ምክንያት ከህወሓት ጋር በተያያዘ በተፈጠረው የፀብ አጫሪነት እና የአውዳሚነት ተግባሩ ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ እየከፈለ” መሆኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ሕዝብ የገባበትን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመቅረፍ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች እንደሚሰሩ የገለፁት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) “ኢትዮጵያ የሰላም አማራጮችን ተጠቅማ የትግራይ ሕዝብ እያጋጠመው ያለውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቅረፍ” እንደምትሰራ ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ እያካሄደ በሚገኘው በዚህ የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲውን ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዝደንቶች ምርጫም አካሄዷል።
የብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን በከፍተኛ ድምጽ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑትን አቶ ደመቀ መኮንን እና አቶ አደም ፋራህ ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት
16 ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት በትግራይ ክልል ውስጥ ለወራት ከተካሄደ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ሲያስወጣ የትግራይ ኃይሎች በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ጥቃት መክፈታቸው ይታወሳል።
በሁለቱ ክልሎች ውስጥ በርካታ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው የቆዩት የትግራይ ኃይሎች የፌደራሉ መንግሥት መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ከፍቶ ከአብዛኛው የአማራ እና የአፋር ክልል ክፍሎች ማስወጣት ችሏል።
ይህንንም ተከትሎም ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ የፌደራሉ መንግሥት ሲያካሂዳቸው ከቆየው የአየር ጥቃቶች ውጪ፤ ይህ ነው የሚባል የተጠናከረ ጦርነት ስለመካሄዱ ሳይዘገብ ቆይቷል።
ባለፉት ወራት ግን የህወሓት ኃይሎች በከባድ መሳሪያ በመደገፍ በአዋሳኝ የአፋር ክልል ወረዳዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም አምስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን እና በጥቃቱ በርካቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የአፋር ክልል ገልጿል።
ህወሓት በበኩሉ ለሳምንታት ከአፋር በኩል በተሰነዘረበት ጥቃት ምክንያት በአፋር ክልል ኃይሎች “የተደቀነውን ስጋት ለማስወገድ ጠንካራ እርምጃ” እንደወሰደ መግለጹ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልልና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ከሚታዩ ግጭቶች ባሻገር የጎላ ጦርነት ስለመኖሩ አስካሁን በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።