26 መጋቢት 2022, 12:07 EAT

ጭምብል አድርገው በመንገድ ላይ የሚታዩ ሰዎች

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ በአንድ ሚሊዮን መጨመሩን የብሔራዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ ይፋ ያደረገው መረጃ አመለከተ።

በከፍተኛ ፍጥነት በሚዛመተው ኦሚክሮን ቢኤ 2 ዝርያ በዩኬ ከ16 ሰዎች መካከል አንዱ በቫይረሱ እንደሚያዝ በተደረጉ ምርመራዎች ተረጋግጧል።

ይህም በድምሩ 4.3 ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው በቫይረሱ መያዙን የሚያሳይ ሲሆን ከሳምንት በፊት የነበረው ከዚህ በአንድ ሚሊዮን የሚያንስ ወይም 3.3 ሚሊዮን ነበር።

ባለለፈው ሳምንት የወጣው ይህ መረጃ ቫይረሱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን ስርጭት የሚያንጸባርቅና ትክክለኛው አሃዝን የሚያመላክት እንደሆነ ይታመናል።

በእንግሊዝ እና በዌልስ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ የጨመረ ሲሆን፣ በስኮትላንድ ከመጨመር አልፎ እስካሁን ያልተየ ቁጥር ተመዝግቧል። በተቃራኒው በሰሜን አየርላንድ በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ ማሽቆልቆል ጀምሯል።

በዩናይትድ ኪንግደም ያለው በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔ

ምንም እንኳን ክትባቶች አሁንም በቫይረሱ የመያዝ ዕድልን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንሱ ቢታመንም፣ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ከበረከቱ በዩናይትድ ኪንግደም ለኮሮናቫይረስ ህክምና ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ሰዎች እንደሚጨምሩ ይገመታል።

ባለፈው ሐሙስ በወጣው የመጨረሻ መረጃ መሰረት በዩኬ 17,440 የኮቪድ ታማሚዎች በሆስፒታል ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ለሌላ ህክምና ሄደው ቫይረሱ የተገኝባቸው ናቸው።

ከእነዚህ ህሙማን ውስጥ ከ300 በላይ የሚሆኑት የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ [ቬንትሌተር] ህክምናቸውን መከታተል ያለባቸው ናቸው።