March 26, 2022 

ፍትሕ መጽሔት – Feteh Magazine 

ገሪቱ ከድኀረ-83 ጀምሮ የባህር በር አልባ መሆኗን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እጅግ ወሳኝ ተቋም መሆኑ አይካድም። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክም ግዘፍ-የሚነሳ ምልክት ነው። ይህም ሆኖ፣ ባለፉት ዐሥር ዐመት ወደ ሞት ሸለቆ እንዲያዘግም በራሱ አስተዳዳሪዎች ተፈርዶበት ቆይቷል። ለዚህ ዐይነቱ የክሽፈት ጉዞውም፣ ዋንኛ ተጠያቂዎቹ በሁለት ሊመደቡ የሚችሉ ኃላፊዎች ናቸው። የመጀመሪያው ሥራ-አስፈጻሚው ተወልደ ገ/ማርያም እና የቦርድ ሰብሳቢው አቶ አባዱላ ገመዳ ሲሆኑ፤ በሁለተኛነት ደግሞ፣ ይህን ሁሉ ጥፋት በታዛዥነት ያስፈጸሙና ምንግዴ የማንጅመንቱ አባላት፤ እንዲሁም፣ ከ2010ሩ ለውጥ ወዲህ የተከሰቱ ችግሮችን በቸልተኝነት የተመለከቱት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ናቸው።

ዋና ሥራ-አስፈጻሚው ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላ፣ ቁጥራቸው እጅግ የበዙ ሠራተኞችን ‹አልሰገዳችሁልኝም?›፣ ‹የዓይናችሁ ቀለም አላማረኝም›፣ ‹ኢሕአዴግን አትደግፉም› በሚሉና በሌሎች ረብ- የለሽ ምክንያቶች አፈናቅሏል። ‹ሥልጣኔን ይቀናቀናሉ› ብሎ ከሰጋቸው የማነጅመንት አባላትም አብዛኛውን አባርሯል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የድርጅቱን ነባር አሠራርና እድገት አሰጣጥ ልማድን በመሻር፤ ኔትዎርክ እና ታማኝነትን የተመረኮዘ ባህል አንብሯል። ባለፉት ስድስት ወራት ደግሞ “ታመምኩ” በሚል ሰበብ አሜሪካን ቢመሽግም፤ “እዚህ ሆኜ ሥራዬን እየሠራሁ ነው፤” በማለት በዶላር ፐርዳየም ሲወስድ ከርሟል። በመሃሉ ለስብስባ ቢጠራም፤ ለመምጣት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። የቦርድ ሰብሳቢው አቶ አባዱላ ገመዳም ‘ውጪ ሆኖ መሥራቱ ችግር የለውም’ የሚል ሽፋን ይሰጡት ነበር። ይሁንና፣ ተቋሙ በየቀኑ የእሱን ውሳኔ የሚጠይቁ በርካታ ትራንዛክሽኖች ቢኖሩትም፤ አሜሪካ ሲነጋ፣ ኢትዮጵያ እንደሚመሽ ቢታወቅም፤ እዚህ የሠራተኞች መውጪያ፣ እዚያ መግቢያ ቢሆንም… እንዴት ኃላፊነቱን “በአግባቡ” ይወጣ እንደነበረ ቦርዱም ሆነ መንግሥት በቂ ምላሽ የላቸውም።

በዚህ ላይ፣ ብዙ ሺሕ ማየሎች ርቆ ለሚመራው ተቋም፣ በቅርቡ አምስት አውሮፕላኖችን በ1.6 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት መዋዋሉን ለሚዲያ ሲናገር ተደምጧል። የተጠቀሰው ገንዘብ እና የአውሮፕላኖቹ መሻጫ ዋጋ የሰፋ ልዩነት እንዳላቸው ሳይዘነጋ፤ “ታምሜያለሁ” ብሎ አሜሪካ በመሸገባቸው ስድስት ወራት መምጣት ያልፈለገው ወደ ኢትዮጵያ እንጂ፤ ደቡብ አፍሪካ እና ቤልጄምን ጨምሮ፣ ወደተለያዩ አገራት ይመላለስ አንደነበረ መረጃዎች አሉ። በአናቱም፣ አቶ ተወልደ ከአገር ሲወጣ አልጋና ሳጥን ሳይቀር በካርጎ ጭኖ መሄዱ፣ ዋንኛው ምክንያት ህመም አለመሆኑንና ቀድሞ እንደተዘጋጀበት በበቂ ይናገራል። ሌላው ቀርቶ፣ የጤና ችግሩን ‘አምነን እንቀበለው’ ቢባል እንኳ፤ የዛሬ ሦስት ሳምንት በቤልጄሟ ሌዥ ከተማ ከመታየቱ አንፃር፣ መልቀቂያውን አዲስ አበባ ተገኝቶ ሊያቀርብና ኃላፊነቱን ሊያረካክብ የማያስችለው የጤና ችግር እንደሌለበት ያስረግጣል። ሠራተኛውን በብሔርና በሃይማኖት ለመከፋፈል መሞከሩም፣ ከሚወቀስባቸው ጥፋቶቹ አንዱ ነው።

በነገራችን ላይ፣ ተቋሙ የደረሰበት አስከፊ ድቀት፣ በተለይ ከፈረንጆቹ 2023 ጀምሮ ጎልቶ መውጣቱ አይቀርም።

ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፈው፣ ከአቶ ተወልደ በተጨማሪ፤ በርካታ ኃላፊዎችም በቢሯቸው ለረዥም ጊዜ ሳይገኙ መቅረታቸው ነው። በአብዛኛው የVice President (VP) እና የManaging Director (MD ) ቦታዎች “Acting” እየተባሉ በውክልና በተቀመጡ ሰዎች መመራቱ የዐደባባይ እውነታ ነው። በርግጥ፣ በውክልና መሥራት በራሱ ስህተት ባይሆንም፤ ዋና ዋና ቦታዎች ላይ የነበሩ ኃላፊዎች በዚህ መጠን በቢሯቸው ሳይገኙ ሲቀሩ፣ ቦርዱም ሆነ መንግሥት ‹ለምን?› ብሎ አለመጠየቁ አስደንጋጭ ነው። መልቀቂያ ሳያስገቡ ከአገር የኮበለሉ በተለያየ ከፍል ያሉ ሠራተኞችም በርካታ ቢሆኑም፤ የእርምታ እርምጃ እንዳይወሰድ ያደረገው አንዱ ምክንያት ይህ እንደሆነ ይታመናል።

ሌላው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቁ ችግር፣ አቶ ተወልደ በተለይ አገሪቱ የትየለሌ በጀት መድባና አያሌ ጊዜ ፈጅታ ያሠለጠነቻቸውን ካፒቴኖችን ጨምሮ፤ የጥገና ባለሙያዎች እና የበረራ አስተናጋጆችን ታይቶ በማይታወቅ መጠን በውሃ ቀጠነ ሰበብ እያባረረ፤ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ዶላር ከውጭ አገር ፓይለቶችን ሲቀጥር የነበረበት ብክነት ነው። በአሁኑ ወቅትም፣ ከ 250 በላይ የውጭ አብራሪዎችን ቀጥሮ እንደሚያሠራ ልብ ይሏል።

የሆነው ሆኖ፣ የሥራ-አስፈጻሚውን በ“ፍቃደኝነት” መልቀቅ ተከትሎ፣ ቢዘገይም አቶ ግርማ ዋቄ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸው፣ ተቋሙን ከገባበት ችግር ለማውጣት የሚደረገውን ሂደት በእጅጉ ያግዛል። ዐዲሱ አለቃ አቶ መስፍን ጣሰውም፣ አቶ ተወልደ በተቋሙ ካራመደው ዘረኝነትና ክፍ ውርስ ርቆ፣ ሁሉንም የአየር መንገዱን ማኀበረሰብ ያሳተፈ ሪፎርም ሊያደርግ እንደሚገባ ለማስታወስ እንወዳለን። በተለይ ለሚከተሉ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠቱ ይመከራል፡-

  1. በትክክል ድርጅቱ ያለበትን ወቅታዊ ቁመና (እነ ተወልደ ሲያንከባልሏቸው የቆዩትን ዕዳዎቹን እና በኬመን ደሴት ያሉትን ሃብት ጭምሮ) በባለሙያ አስጠንቶ፣ ለሚመለከተው አካል ይፋ ማድረግ፤
  2. ለሠራተኛ ማኀበሩ እና ለተለያዩ ሙያ ማኀበራቱ እውቅና ሰጥቶ መቀራርብ፤ በተቋሙ የሰፈነውን ልዩነት ለማጥበብ መሥራት፤
  3. አቶ ተወልደ አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት የገፋቸውንና ለድርጅቱ ሊጠቅሙ የሚችሉትን ሠራተኞች ይቅርታ ጠይቆ ወደ ቦታቸው መመለስ፤
  4. በታማኝነት ብቻ ያለብቃት የተሾሙትን አንስቶ፤ ብቁ በሆኑ ሠራተኞች መተካት፤
  5. በተቋሙ ሥልጣን አሁን ያለበትን የጥቅለላ አያያዝ ቀይሮ፣ በተዋረድ ላስፈጻሚው መመለስ፤
  6. የእድገትና ኃላፊነት አሰጣጥን ከአቶ ተወልደ በፊት እንደነበረው በውድድርና በፈተና ማድረግ፤
  7. ከሠራተኞች ጋር ተቀራርቦ ሰፊ ውይይት ማካሄድ፤ ለቅሬታዎቻቸውም መፍትሔ መስጠት።

በሌላ በኩል፣ ሠራተኛ ማኀበሩ ለጊዜው መብቱንና ጥቅሙን ሰውቶ ከማንጀመንቱ ጋር እጅና ጓንት በመሆን፣ ተቋሙን የማዳን ሥራ ላይ ሊረባረብ እንደሚገባ “ፍትሕ መጽሔት” ትመክራለች።