

27 March 2022
የአማራ ክልል መንግሥት የሕወሓት ኃይሎች ‹‹ለዳግም ወረራ›› ይመጣሉ የሚል ሥጋት በመኖሩ ‹‹ጦርነቱ ተጠናቋል›› የሚል ሐሳብ እንደሌለውና በሕወሓት የተያዙ የክልሉ ወረዳዎችንም የተደራጀ ጦር በማሰለፍ ነፃ ማውጣት እንደሚገባ አሳሰበ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ሕወሓት በያዛቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ለርሃብና ለሕክምና ዕጦት መዳረጋቸውን ለሕዝቡ ሲባል ሕወሓት በክልሉ ላይ የፈጸመው ‹‹ወረራ›› በፍጥነት ምላሽ ማግኘት አለበት የሚለውን ሐሳብ እንደሚጋሩ ተናግረዋል፡፡
መጋቢት 15 እና 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር፣ አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔው ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ይልቃል (ዶ/ር) በርካታ ወረዳዎች አሁንም በሕወሓት ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዝቋላ፣ ፃግብጂ፣ አበርገሌ፣ አድርቃይና ጠለምት አከባቢዎች አሁንም ነፃ እንዳልወጡ በፕሬዚዳንቱ ከተጠቀሱ አከባቢዎች መካከል ናቸው፡፡
ይልቃል (ዶ/ር) የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለመመለስ ሲል፣ ሌሎች መደበኛ እንቅስቃሴዎችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እያስኬደ እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ፣ በሕወሓት በኩል የተደቀነው አደጋ ግን አሁንም ከክልሉ መንግሥት ትኩረት ውስጥ እንዳልወጣ ተናግረዋል፡፡ የዋግ፣ የሰሜን ወሎ፣ የወልቃይት ሁመራና የምዕራብ ጎንደር ዞን ሚሊሻዎች አሁንም እየተፋለሙ መሆኑን አስረድተው ‹‹የእኛ ሕዝብ በየቀኑ እየተታኮሰ፣ እየተጋደለ እየሞተ ነው ያለው፣ ጦርነት እኮ አልቆመም፤›› ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉባዔው ላይ ይህንን ማብራሪያ እንዲሰጡ ካደረጓቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ በሰሜን ወሎ ዞን፣ የዋርላ ወረዳ ምርጫ ክልል ተወካይ ከሆኑት የምክር ቤቱ አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው የቀረበ ነው፡፡ አቶ ዮሐንስ በክልሉ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት የአማራ ሕዝብ ላይ ጋርጦ የነበረው ከፍተኛ አደጋ በአንፃራዊነት እንደቀነሰ ተናግረው፣ የክልሉ ሕዝብ ‹‹ለዳግም ወረራ›› ተጋላጭ የመሆኑ ጉዳይ ግን ጥያቄ የሌለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹ጠላት በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘጋጀ ነው›› ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ ሕወሓት በመቶ ሺዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን እያሠለጠነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱም ካለፈው ጦርነት ትምህርት ሳይወስድ ቀርቶ ‹‹ታሪካዊ ኃላፊነቱን›› ባለመወጣት ሕዝቡን ለዳግም ጥቃት ያጋልጠዋል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
አክለውም ሕዝቡን ‹‹ማዘጋጀት አለብን፣ እውነቱን መንገር አለብን፡፡ ለዳግም ጥቃት የተጋለጠ ሕዝብ ነው ያለው፤›› ካሉ በኋላ፣ የዳግም ጥቃቱ ‹‹የወደሙትን ድጋሚ ማውደም፣ እንዳይነሱ ማድረግ፣ ያልወደሙትን የክልላችን አከባቢዎች ደግሞ መዝረፍ፣ መውረርና ማዋረድን ያመጣል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
ይኼ ሥጋት ‹‹ደፈር ተብሎ›› እየተነገረ እንዳልሆነ ያስረዱት አቶ ዮሐንስ፣ ሥጋቱ ከፊት የሚታይ እውነታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ሲባል የሚደረገው ዝግጅት ከአሁኑ ሊታሰብበት እንደሚገባና ሕዝቡ ለዝግጅቱ ‹‹ወገቡን ጠበቅ›› ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ከበለሳይ ምርጫ ክልል የመጡ አቶ ግዛት የተባሉ ሌላ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው፣ በሕወሓት ተይዘው የነበሩ የክልሉ አከባቢዎችን ለማስለቀቅ ብዙ መስዋዕትነት እንደተከፈለ ተናገረው፣ አሁንም ግን በዋግኽምራና ሰሜን ጎንደር በሕወሓት ሥር ያሉ አካባቢዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
የፌደራሉ መንግሥት ግጭትን በማቆም ሕይወት እንዳይቀጠፍ መወሰኑ ላይ ብዙም ተቃውሞ እንደሌላቸው የጠቀሱት የምክር ቤት አባሉ፣ በሕወሓት ሥር የሚገኙ አከባቢዎች ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ግን ምን ሊደረግ እንደታሰበ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ከሌሎችም የምክር ቤት አባላት ተመሳሳይ ጥያቄችን ያስተናገዱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል (ዶ/ር)፣ ክልሉ በጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰበት በመናገር፣ የክልሉ መንግሥት፣ የመንግሥታዊ ሥራዎችን በማስጀመርና የተጋረጠው ሥጋት ላይ ትኩረት በማድረግ በኩል ሚዛናዊ አካሄድን እንደመረጠ አስረድተዋል፡፡
ይሁንና የክልሉ ሚሊሻዎች አሁንም ድረስ እየተዋጉ እንደሆነ በመግለጽ የክልሉ መንግሥት ‹‹ጦርነቱ አልቋል›› በማለት እንዳልተቀመጠ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወያኔ እንደሚያደርገው፣ ትምህርት ቤት ዘግተን፣ የመንግሥት ሥራ ዘግተን፣ ሁሉን ነገር እናዝምተው ካልን ማድረግ እንችላል፤›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ማድረግ ግን አዋጪ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ይልቃል (ዶ/ር)፣ ‹‹የእኛ በርካታ ወረዳዎች ከጠላት ነፃ አልሆኑም›› ካሉ በኋላ ‹‹የተቀናጀ ጥምር ጦር በጋራ አሠልፈን ነፃ ማድረግ አለብን፣ ከፌደራል መንግሥት ጋርም የጋራ ዕቅድ አለን፤›› ብለዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በግንባር ላይ የነበሩ የሚሊሻ አባላት ወደ የመኖሪያ ቅዬአቸው የተመለሱት ቤተሰብ እንዲያገኙና እረፍት እንዲኖራቸው ከሚሊሻው ጋር በተደረገ ንግግር መሆኑን አስረድተው፣ አስፈላጊ ከሆነና ሥጋቱ ካየለ ሚሊሻውን በድጋሚ ማንቀሳቀስ እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡
በጉባዔው ላይ በተደጋጋሚ የተነሳው ሌላኛው ጥያቄ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩና ጥቃትና መፈናቀል እያስተናገዱ ያሉ የአማራ ተወላጆች ጉዳይ ነው፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በጉባዔው መጀመሪያ ቀን ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ከኦሮሚያ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ደቡብ ክልሎች በማንነታቸው ምክንያት ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ክልሉ የተፈናቀሉ ከ692 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በየክልሉ የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን በተመለከተ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከኦሮሚያና ከአፋር ክልሎች ጋር በጋራ በመሆን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የሚንዱ ጥቃቶችን መከላከል እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልልም በክልሉ ይኖሩ የነበሩና የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን፣ ከአማራ ክልል ሰላማዊ ወደ ሆኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች ለመውሰድ ቃል እንደገባ አስረድተዋል፡፡ የሰላሙ ሁኔታ ሲረጋገጥም ተፈናቃዮቹ ይኖሩበት ወደ የነበረው አካባቢ ለመመለስ እንደተስማማ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል፡፡