

30 March 2022
- መስመሩ ኢትዮጵያን ከሳዑዲና ሌሎች ዓረብ አገሮችንም እንደሚያገናኝ ታሳቢ ተደርጓል
ኢትዮጵያና ጂቡቲን ዳግም ለሚያስተሳስረው ሁለተኛው የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ የዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የመጨረሻ ግምገማ ላይ መሆኑ ታወቀ።
ለሁለተኛው የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማት ግንባታ ከሚያስፈልገው ወጪ ውስጥ፣ ከኢትዮጵያ ድንበር በኋላ ያለውን የመሠረተ ልማት ግንባታ የዓለም ባንክ እንዲሸፍን በጂቡቲ መንግሥት መጠየቁ ታውቋል።
በጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ የተመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት የቆየ የሥራ ጉብኝት አድርጎ ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ጂቡቲ የተመለሰ ሲሆን፣ የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ከሌሎችም ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ከመከረባቸው ጉዳዮች መካከል፣ የኃይል አቅርቦትና የጋራ መሠረተ ልማት ዝርጋታ እንደሚገኝበት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
ለሁለተኛው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ የጂቡቲ መንግሥት ያቀረበውን የብድር ጥያቄ፣ የዓለም ባንክ ሲገመግም የቆየ ሲሆን፣ የባንኩ ቦርድ በብድር ጥያቄው ላይ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲ የተዘረጋውንና በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል እየቀረበበት የሚገኘው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር፣ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተገነባ ሲሆን፣ ሁለተኛው የኃይል ማስተላለፊያ ግንባታ ደግሞ በአፍሪካ ልማት ባንክና በዓለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚከናወን ታውቋል።
በኢትዮጵያ በኩል የሚገነባውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ለማከናውን የሚያስፈልገውን ወጪ የአፍሪካ ልማት ባንክ ለመሸፈን ባለፈው ዓመት በነሐሴ ወር እንደወሰነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያ በኩል የሚገነባው መስመር ከአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እስከ ጂቡቲ ድንበር ጋላፊ የሚዘልቅ 102 ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ አንዱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ከኮምቦልቻ አንስቶ በአፋር ሚሌ ከተማ ውስጥ እስከሚገነባው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የሚዘረጋ 170 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ይገኝበታል።
ይህንን ግንባታ ለማከናውን የሚያስፈልገውን አጠቃላይ ወጪ የአፍሪካ ልማት ባንክ የሚሸፍን ሲሆን፣ ለዚህም 83 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፈቅዷል።
በጂቡቲ በኩል የሚገነባው መስመር ከጋላፊ ድንበር እስከ ነጋድ የተባለ አካባቢ የሚዘልቅና 190 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሲሆን፣ ለዚህ ግንባታ የሚያስፈልገውን 55 ሚሊዮን ዶላር የዓለም ባንክ በብድር እንዲያቀርብ የጂቡቲ መንግሥት ጠይቋል።
የጂቡቲ መንግሥት ለዓለም ባንክ ያስገባው የፕሮጀክት ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ ሁለተኛው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ጂቡቲ ያለባትን ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2035 እተገብረዋለው ላለችው የኢኮኖሚ ልማት መርሐ ግብር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
ኢትዮጵያንና ጂቡቲን ካስተሳሰረው የመጀመሪያው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በአማካይ 80 ሜጋ ዋት ኃይል ጂቡቲ እያገኘች መሆኑን የሚያመለክተው መረጃው፣ ይህ የኃይል አቅርቦት ካለው የጂቡቲ የኃይል ፍጆታ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል።
ይሁን እንጂ ይህ የኃይል አቅርቦት ጂቡቲ ካቀደችው ግዙፍ የኢኮኖሚ ልማት መርሐ ግብር አንፃር መገምገም ኢምንት እንደሆነና ሁለተኛው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሲጠናቀቅ ግን፣ ጂቡቲ ከኢትዮጵያ የምታገኘውን የኃይል አቅርቦት ወደ 220 ሜጋ ዋት እንደሚያደርሰው ያመለክታል።
ይህ ፕሮጀክት የጂቡቲን የኃይል አቅርቦት ችግር ከመፍታቱ ባሻገር፣ የዓለም ባንክ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ የዓረብ አገሮችን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰርና ቀጣናዊ የኃይል አቅርቦት ገበያ ለመመሥረት ከወጠነው የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ጋር የሚጣጣም መሆኑን፣ የጂቡቲ መንግሥት የፕሮጀክት ሰነድ ያሳያል።
ሰነዱ እንደሚገልጸው ጂቡቲ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ የዓረብ አገሮችን (ፓን ዓረቢያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ገበያ) አባል አገር በመሆኗ፣ ሁለተኛው የኢትዮ ጂቡቲ የኃይል መስመር መገንባት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የኃይል ቋትን በመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ውስጥ በጂቡቲ በኩል ከሳዑዲ ዓረቢያ በማገናኘት የፓን ዓረቢያ የኃይል አቅርቦት ትስስርን እንድትቀላቀል ያደርጋታል።
ጂቡቲን ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር በየመን በኩል በኃይል የማስተሳሰር ውጥን የተያዘ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በየመን ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ከተቀረፈ ፕሮጀክቱን በአጭር ዓመታት ውስጥ ለመጀመር ዕቅድ መያዙን መረጃዎች ያመለክታሉ። የየመን ቀውስ የሚቀጥል ከሆነ ፕሮጀክቱ ሊዘገይ እንደሚችል ወይም የፕሮጀክት ወጪውን ከፍ በማድረግ ከየመን ውጪ በቀይ ባህር ውስጥ በሚያልፍ የባህር መስመር ከሳዑዲ ዓረቢያ የማገናኘት አማራጭ መኖሩንም፣ የተገኙ ሌሎች መረጃዎች ያመለክታሉ።
ግብፅና ሳዑዲ ዓረቢያ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ቋቶቻቸውን ለማገናኘት፣ ከግብፅ ባደር እስክ ኤል መዲናህ የሚዘረጋ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል ዩሮ አፍሪካ ኢንተርኮኔክተር የተሰኘ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ትስስር ፕሮጀክት የግብፅን ብሔራዊ ቋት በባህር ውስጥ በሚዘረጋ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከግሪክ የማገናኘት ፕሮጀክት፣ እ.ኤ.አ. በ2020 ይፋ መደረጉን መረጃዎች ያሳያሉ።
በጂቡቲ መንግሥት የፕሮጀክት ሰነድ ላይ እንደተገለጸው፣ በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ በጂቡቲና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል የኃይል አቅርቦት ትስስር መሠረተ ልማት የሚገነባ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ዕምቅ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ እንዲሁም ወደ ግብፅና ለሌሎች የዓረብ አገሮች ኤክስፖርት የማድረግና ሜዲትራኒያን በማቋረጥ የአውሮፓ የኃይል ገበያን የመቀላቀል ዕድል መኖሩን ያመላክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአንድ ወር በፊት በብራሰልስ የተካሄደውን የአውሮፓና የአፍሪካ የጋራ ፎረም ተካፍለው ሲመለሱ በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ ዕምቅ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሀብቷን ለአውሮፓ ገበያ ጭምር የማቅረብ ዕድል እንዳላት መናገራቸው ይታወሳል።