

30 March 2022
በ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት ለፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግሥት ከሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ፣ ከ19 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ብልፅግና 7.7 ሚሊዮን ብር በመውሰድ ከፍተኛ ድርሻ ሲይዝ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) 281 ሺሕ ብር በመውሰድ ዝቅተኛውን ድጋፍ ያገኘ ፓርቲ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ከተለያዩ አገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር፣ በ2014 ዓ.ም. ለፓርቲዎች ስለሚደረግ የገንዘብ ድጋፍና አጠቃላይ የፓርቲዎች አቤቱታን አስመልክቶ ውይይት አካሂዷል፡፡
በምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች በተመደበው 50 ሚሊዮን ብር ክፍፍል ቀመር መሠረት 30 በመቶ ለአገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ 20 በመቶ ለክልላዊ ፓርቲዎች ሲደለደል ቀሪው ገንዘብ ደግሞ ፓርቲዎቹ ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን በአባልነትና በአመራርነት በሚያሳትፉበት ልክ ክፍፍል መደረጉ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በውይይት መድረኩ የቀረበው የፖለቲካ ፓርቲዎች የ2014 ዓ.ም. የበጀት ድጋፍ ድልድል እንደሚያመለክተው፣ በድልድሉ ከተዘረዘሩ 19 አገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ብልፅግና 7.7 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) 1.8 ሚሊዮን ብር፣ የቀሪዎቹ 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርሻ ደግሞ ከ900 ሺሕ ብር እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር እርከን ውስጥ ይገኛል፡፡
ቦርዱ ለ35 የክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ መሥፈርት የበጀት ድጋፍ ድልድል ያደረገላቸው ሲሆን፣ በድልድሉ የጋምቤላ ሕዝቦች ለፍትሕ ለሰላምና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ (ጋሕፍሰልዲን) እና የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እያንዳንዳቸው 1.1 ሚሊዮን ብር በማግኘት ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል፡፡
ከተጠቀሱት ክልላዊ ፓርቲዎች መካከል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) 281 ሺሕ ብር በመውሰድ ዝቅተኛውን ድርሻ ሲይዝ፣ ቀሪዎቹ 32 ፓርቲዎች ከአንድ ሚሊዮን ብር በታች ባለው እርከን ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ስለበጀት ድጋፍ ክፍፍሉ አስረድተዋል፡፡ የክፍፍል መሥፈርቱ በዋነኝነት የፓርቲዎቹ አጠቃላይ አፈጻጸም፣ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሕዝብ ተወካዮችና በክልል ምክር ቤት ባገኙት የወንበር ብዛት፣ በፓርቲው ውስጥ ባሉ የሴት አባላትና አመራሮች ተሳትፎ፣ የአካል ጉዳተኞች አባላት ብዛትና በአመራር ደረጃ ያላቸው የቁጥር ብዛት የሚሉና መሰል መሥፈርቶች መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ በ2014 ዓ.ም. ለፓርቲዎች ድጋፍ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ለመንግሥት ያቀረበው ጥያቄ አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ በፓርላማውና በገንዘብ ሚኒስቴር ውድቅ በመደረጉ፣ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለኅትመት ሥራዎች ታስቦ ከነበረው ገንዘብ የተረፈ 50 ሚሊዮን ብር በመገኘቱ መንግሥት ተጠይቆ ለፓርቲዎች ድጋፍ እንዲውል መፈቀዱን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከአጠቃላይ 54 አገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የገቢ ደረሰኝና የኦዲት ሪፖርት አሟልተው ያቀረቡት 15 የፖለቲካ ፓርቲዎች በመሆናቸው፣ ቀሪዎቹ ፓርቲዎች የተጠየቀውን መረጃ እስኪያቀርቡ ድረስ ገንዘቡ እንደማይለቀቅላቸው ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል፡፡