27 AUGUST 2014 ተጻፈ በ  

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና ሱዳን የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረባቸውን ሁለት ምክረ ሐሳቦች ለመፈጸም ስምምነት ፈረሙ፡፡

ግብፅ በኢትዮጵያና በሱዳን የጋራ ሐሳብ ላይ መስማማት ባለመቻሏ ተቋርጦ የነበረው የሦስቱ አገሮች የጋራ ውይይት ባለፈው ሰኞና ማክሰኞ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በተካሄደበት ወቅት ነው ሦስቱ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስምምነቱን የተፈራረሙት፡፡

የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ማክሰኞ ማምሻውን የሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረባቸው ሁለት ምክረ ሐሳቦችን ለመተግበር፣ ሁለት ጥናቶች በድጋሚ እንዲጠኑ ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ለአንድ ዓመት ያህል የህዳሴውን ግድብ የተመለከተ ጥናት ካካሄደ በኋላ፣ ለሦስቱ አገሮች የጥናት ሪፖርቱንና ምክረ ሐሳቦችን ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ከተሰጡት ምክረ ሐሳቦች መካከል ሦስቱ አገሮችን በጋራ የሚመለከቱት ምክረ ሐሳቦች ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ኃይድሮሎጂ ሲሙሌሽን ሞዴል›› ማለትም ግድቡ በውኃ የሚሞላበትና የውኃ አለቃቅ በተለያዩ የዝናብ ወቅቶች ምን መምሰል አለበት የሚለው አንደኛው ምክረ ሐሳብ መሆኑን በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ሁለተኛው ምክረ ሐሳብ ደግሞ የግድቡ መገንባት በሦስቱ አገሮች ላይ ሊያደርስ የሚችለው የማኅበራዊና አካባቢያዊ ጉዳት ጥናትን የሚመለከት መሆኑን አቶ ፈቅ አህመድ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተጠቀሱትን ሁለት ጥናቶች በራሷ መንገድ ማጥናቷን፣ ነገር ግን በሦስቱ አገሮች መካከል መተማመንን ለመፍጠር በድጋሚ ቢጠና በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተቃውሞ አለመኖሩ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ሥልጣን ዘመን ውይይቶች ቢጀመሩም፣ በግብፅ ተለዋዋጭ አቋም ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ባለፈው ሰኞ በሱዳን የተጀመረው የሦስትዮሽ ውይይት ቀድሞ ከተቋረጠበት የተጀመረ ወይም አራተኛው ዙር የሦስትዮሽ ውይይት ነው፡፡

በዚህ ስብሰባ የመጀመሪያ ቀን ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ዓለማየሁ፣ ‹‹ይህ የሦስትዮሽ ውይይት የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረባቸው ሐሳቦችን መተግበር የሚያስችል ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ ነጥብ ውጭ ያሉና ለዚህ ውይይት የማይጠቅሙ ሐሳቦችን ወደ ጐን በማድረግ በዋና የውይይቱ ጭብጥ ላይ ትኩረት ቢደረግ፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ሁለት ቀናት በፈጀው የሦስትዮሽ ውይይት ላይ የተነሱ አዳዲስ ሐሳቦች ስላለመኖራቸው ግን ለሕትመት እስከገባንበት ማክሰኞ ምሽት ድረስ ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ ይሁን እንጂ የግብፅ የመስኖና ውኃ ሚኒስትር የሆኑት ሆሳም አል ሞጋሃዚ ከሦስትዮሽ ውይይት ቀደም ብሎ በሰጡት መግለጫ ግብፅ በዚህ የሦስትዮሽ ውይይት ላይ አዲስ ሐሳብ እንደምታቀርብ አሳውቀው ነበር፡፡ አዲስ ሐሳብ ያሉትም የህዳሴው ግድብ ውኃ የመያዝ አቅም እንዲቀንስ ኢትዮጵያን መጠየቅ ነበር፡፡

ዲአ ኤልቁሲ የተባሉ የግብፅ የውኃ ሀብት ኤክስፐርት አህራም ለተባለው የግብፅ ሚዲያ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹የህዳሴው ግድብ ርዝመት አሁን በታቀደው 150 ሜትር፣ እንዲሁም ግድቡ 74 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ እንዲይዝ ግብፅ አትፈቅድም፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓባይ ተፋሰስ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ሸሪፍ ኢሳ ናቸው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ ያከናወነችው የመጀመሪያ ጥናት ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ጥናት ቢካሄድ ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ይታወቃል፤›› በማለት ሸሪፍ ኢሳ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ግን፣ ከላይ የተጠቀሰው ክርክር የበለጠ የሚጠቅመው ኢትዮጵያን መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያ የግድብ ሥራውን የሰጠችው ሳሊኒ ለሚባለው ታዋቂ የጣሊያን ኩባንያ ተቆጣጣሪ ድርጅቱም የፈረንሳይ ታዋቂ ኩባንያ መሆናቸውን፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የተሰጠው ኮንትራት ‹‹EPC›› ወይም የኢንጂነሪንግ ግዥና ግንባታ ሥራውን አጠቃሎ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህም ማለት በመጀመሪያው ጥናት ላይ የታዩ ሕፀፆች በሁለተኛ ደረጃ ጥናቱ ላይ እየተቀረፉ እንደሚሄዱ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ሁለተኛው ዙር ጥናት ቀርቦለት ቢሆን ይህንን ምክረ ሐሳብ እንደማያቀርብ በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን  ነው ሦስቱ አገሮች የተባሉትን ሁለት ምክረ ሐሳቦች በጋራ እንዲያጠኑ የፈቀደችው በጥናቱ ላይ እርግጠኛ በመሆኗ እንደሆነም ይከራከራሉ፡፡