

13 April 2022
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በ11 ተቃውሞና በ17 ድምፀ ተዓቅቦ ያፀደቀውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ አባላትን ሹመትና አጠቃላይ የአባላት ምልመላ ሒደት እንዲስተካከል፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጠየቀ፡፡
ምክር ቤቱ ሚያዝያ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ሹመት የፀደቀው፣ ከዓመት በፊት ፓርላማው ያወጣውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ድንጋጌን በመጣስ ነው፡፡ የአዋጁ ድንጋጌ እንደሚያስረዳው፣ የባለሥልጣኑ ቦርድ አባላት ምልመላ ሲካሄድ፣ ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ሕዝብ አስተያየት እንደሚሰጥና የተመራጮች ዝርዝር በመገናኛ ብዙኃን ይፋ ይደረጋል፡፡ እነዚህንና ዝርዝር ድንጋጌዎችን በመተላለፉ የቦርድ አባላቱ ሹመት መጽደቁ ተገቢ አለመሆኑን ምክር ቤቱ በመግለጫ ተቃውሟል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ሹመትን በተመለከተ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
‹‹በምክር ቤቱ የተካሄደው ሕገወጥ የቦርድ አባላት አመላመልና አሿሿም ሒደት እንዲስተካከል በአንክሮ እንጠይቃለን››
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነፀ በኃላፊነት ስሜት ሕዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በአገራችን እንዲጎለብት የሚሠራ ሲሆን ከ61 በላይ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃንን እንዲሁም የጋዜጠኞች የሙያ ማኅበራትን በአባልነት ያቀፈ ተቋም ነው፡፡
ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክረ ቤት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላትን ሹመት ባለፈው ሳምንት ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ምክር ቤቱ ይህንን ሹመት ያፀደቀው ፓርላማው ከዓመት በፊት ያወጣውን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተፃረረ ሁኔታ መሆኑን ተመልክተናል፡፡
በመጀመርያ ደረጃ አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን፣ አዋጁን ከረቂቁ ጀምሮ ምክር ቤታችን በትኩረት ሲከታተለው የነበረና በብዙ መድረኮች ላይ ተገኝቶም ሐሳብ ያዋጣ ሲሆን፣ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጠራ የሕዝብ አስተያየት መቀበያ መድረክ ላይ ተገኝቶ፣ ለሚዲያ ሥራ አስቸጋሪ ያላቸውን ሐሳቦች ያቀረበ ከመሆኑም በላይ ከፍትህ ሚኒስትሩ ጋር ቀጠሮ በመያዝ ሰፊ ውይይት አካሂዷል፡፡
የአዋጁ አርቃቂ ኮሚቴ አባላት ገለልተኛ የሕግና የሚዲያ ዕውቀት ባላቸው ግለሰቦች መዋቀሩን ምክር ቤታችን በበጎ ጎኑ የተመለከተው ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎም በፍትህ ሚኒስቴር ሥር የተዋቀረው የሕግ ማሻሻያ አማካሪ ቡድን ሥራውን ከመጀመሩ በፊት፣ ባለፈው የፕሬስ አዋጅ ላይ ያሉና አላሠራ ያሉ ድንጋጌዎች የትኞቹ እንደሆኑ አስቀድሞ የዳሰሳ ጥናት ባከናወነበት ወቅት ከተገኙ ውጤቶች መካከል አንዱና ዋናው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንን በቦርድ አባልነትም ሆነ በዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩ ግለሰቦች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊና የገዥው ፓርቲ ቁልፍ ሰዎች የመሆናቸው ሁኔታ፣ ሚዲያውን በነፃነትና በገለልተኝነት እንዳያገለግሉ እንቅፋት መሆኑን ያመላከተ ነበር፡፡
በዚህም የተነሳ አዲስ በሚረቀቀው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ላይ ቦርዱንም ሆነ ባለሥልጣኑን የሚመሩት ግለሰቦች ከፓርቲ አባልነትና ወሳኝ ከሆነ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ነፃ እንዲሆኑ ከፍተኛ ትግል ተደርጎበታል፡፡ ይህንኑ የሚዲያውና የፕሬስ ነፃነት አቀንቃኝ ወገኖች አስተያየት መነሻ በማድረግ በአዋጁ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡
ሆኖም ሰሞኑን የምክር ቤቱ በተደረገው የቦርድ አባላት አሰያየምና የሹመት አሰጣጥ በአዋጁ ከተቀመጠው ድንጋጌ ያፈነገጡ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡
በመጀመርያ ደረጃ የባለሥልጣኑ የቦርድ አባላት ከመሰየማቸው በፊት ምልመላው የሚካሄደው ‹ግልጽ በሆነ የሕዝብ ጥቆማና በመገናኛ ብዙኃን በሚተላለፍ ማስታወቂያ ነው› ይላል በአዋጁ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ፡፡
የቦርዱ አባላት ዕጩዎችን የመመልመልና የማፅደቁ ሒደት ሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን ያለበት ሲሆን፣ በሒደቱም ሕዝቡ ዕጩ ግለሰቦችን በጠቆምና በዕጩዎች ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ዕድል እንዲሰጣቸው ያደርጋል፣ የዚህን አዋጅ ዓላማዎችና መርሆች ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የዕጩዎች አመራረጥ ሒደትና የተመረጡ ዕጩዎች ዝርዝር በመገናኛ ብዙኃን ወይም በሌሎች ኤሌክትሮኒክ ማሠራጫዎች ታትሞ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል፣ የዕጩዎች ምልመላ የኢትዮጵያን ብዝኃነት ያማከለ ፌዴራላዊ ውክልና እንዲኖረው ይደረጋል ይላል፡፡
ይህ አልተደረገም፣ በመገናኛ ብዙኃንም ሕዝቡ እንዲጠቁም ዕድል አልተሰጠውም፣ አስተያየትም አልተሰጠም፡፡ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ይህንኑ በተመለከተ ላነሷቸው ጥያቄዎች በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የሰጧቸው ምላሾች ተገቢ ሆነው አላገኘናቸውም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የቦርዱ አባላት የሚመረጡበትን መሥፈርት በተመለከተ በአንቀጽ 11 ላይ 7 ያህል መሥፈርቶችን አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህ መሥፈርቶች መካከል በስድስተኛ ደረጃ ላይ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ወይም ተቀጣሪ ያልሆነ፤›› ይላል፡፡
ነገር ግን በምክር ቤቱ የተሾሙ ግለሰቦችን ስንመለከት ሰብሳቢውን ጨምሮ ሌሎች አባላት የብልፅግና ፓርቲ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ቁልፍ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች ናቸው፡፡
ሌላው የቦርዱ አባላት ስብጥርን በተመለከተ በአንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 5 ላይ ቢያንስ ሁለት የቦርድ አባላት ከመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እንዲሆኑ ይደነግጋል፡፡
ከቦርድ አባላት መካከል፣ ሁለቱ ከሲቪል ማኅበረሰብ፣ ሁለቱ ከመገናኛ ብዙኃንና ሁለቱ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ጠቀሜታና አግባብነት ካላቸው የተለያዩ ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ሦስቱ አግባብነት ካላቸው የመንግሥት አካላት፣ የተውጣጡ ይሆናሉ፤›› ይላል፡፡
ከተሾሙት ግለሰቦች መካከል ግን አንድም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ አልተካተተም፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አግባብነት ካላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚለው መሥፈርትም እነማን እንደተመረጡ ግልጽ አይደለም፡፡ ከሲቪክ ድርጅቶች እንዲካተቱ የተመጡት ሁለት ግለሰቦችም ከሦስት ሺሕ በላይ የሲቪክ ድርጅቶች ባሉበት አገር ሁለቱም ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ መሆናቸው የአዋጁን መንፈስ የሚቃረን ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በንዑስ አንቀጽ (ለ) ላይ የተመለከተው ‹አግባብነት ካላቸው የመንገሥት አካላት› የሚለውም ቢሆን የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ተቀጣሪዎች እንዳይሆኑ አዋጁ በግልጽ ከልክሏል፡፡
ሌላው ምክር ቤቱ ከወራት በፊት የሰየመው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የዳይሬክተሮች ሹመትም ሕግን የተከተለ እንዳልሆነ መመልከት ይቻላል፡፡ ይኸውም የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዳይሬክተሮች የሚሾሙት በአዋጁ አንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት፣ ቦርዱ ከተሰየመ በኋላ በቦርዱ አቅራቢነት እንጂ ከቦርዱ በፊት መሆን አልነበረበትም፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሥልጣንና ተግባራት፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በቦርዱ ተመልምሎ በመንግሥት አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሰየማል ይላል፡፡
ነገር ግን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመው ፓርላማው ሹመታቸውን ያፀደቀው መቅደም ያለበትን የቦርዱን አባላት ሳይሰይም ነው፡፡
ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና ካላቸው የዲሞክራሲ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የመገናኛ ብዙኃን፣ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መቋቋምና ሥራውን ያለ አድልኦ መሥራት ካልቻለ፣ የሚታሰበው ለውጥ ዕውን የመሆኑ ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል፡፡
መንግሥት አዲሱን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እንዲሻሻል ሲያደርግ፣ ባለፉት 27 ዓመታት በሕግ መንግሥቱ ላይ የተቀመጡት ‹‹ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት›› በተሻለ ሁኔታ እንዲከበር በማሰብ እንደሆነ እንገነዘባለን፣ ሆኖም ከፍተኛ ትግልና ተሳትፎ ተደርጎበት የወጣው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ ግልጽ የሆነ የሕግ ጥሰት ሲገጥመው መከላከል የዘርፉ ተዋናያን ብቻ ሳይሆን የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ድርሻ በመሆኑ፣ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተካሄደው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባላት ሕገወጥ አመላመልና የአሿሿም ሥርዓት እንዲታረም በአንክሮ እንጠይቃለን፡፡
ጉዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታችሁ አካላትም ይህ ሕግን የተፃረረ አካሄድ እንዳይደገምና ልምድ ሆኖ በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ እንዳይቀጥል ድምፃችሁን እንድታሰሙ እንጠይቃለን፡፡