

13 April 2022
የመንግሥት ተቋማት ከግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ግዥ እንዳይፈጽሙ መከልከሉን፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ።
የመንግሥት ተቋማት ዓመታዊ በጀታቸውን ለመጨረስ ሲሉ በተለይ የበጀት ዓመት በሚጠናቀቅበት የሰኔ ወር፣ ያልተጠና ግዥ በመፈጸም የሀብት ብክነት እንዳይፈጥሩ ትዕዛዙ መተላለፉን፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰጠኝ ገላን ለሪፖርተር ገልጸዋል።
የመንግሥት ተቋማት በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ የሚመደብላቸውን በጀት ከፍ ለማድረግ ሲሉ ያለፈውን ዓመት በጀት በትክክል እንደተጠቀሙ በማስመሰል፣ አግባብነት የሌላቸውን ግዥዎች ሲፈጽሙ ይስተዋላል ብለዋል።
ከአሁን በፊት በበጀት ዓመት መጨረሻ ጊዜያት የሚደረጉ ግዥዎች ለብክነት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ለተቋማቱ የተለያዩ ግንዛቤ ማስጨበጫ ግንዛቤዎች ቢሰጡም፣ ውጤታማ አለመሆናቸውን አክለዋል።
በመሆኑም ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ የፌደራል መንግሥት የሚመራቸው ተቋማት የሚፈጽሟቸው ግዥዎች፣ አስፈላጊነታቸውና አዋጪነታቸው ተጠንቶ መፈጸም እንዳለባቸው ትዕዛዝ እንደተላለፈላቸው የገለጹት አቶ ሰጠኝ፣ ይህም ከግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል።
የመንግሥት ተቋማቱ ከግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በኋላ የሚፈጽሟቸው ግዥዎች አስቸኳይ ከሆኑ ብቻ እንደሚፈቀዱ፣ አስፈላጊነታቸው ከታመነበት ለመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በማሳወቅ ፈቃድ በማግኘት እንደሚሆን ተናግረዋል። በተቋማቱ የበላይ ኃላፊዎች ፊርማ የሚፈቀዱ ግዥዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ለዚህም ተቋማቱ ኃላፊነት እንደሚወስዱና ኦዲት ተደርገው ያላግባብ ግዥ መፈጸሙ ከተረጋገጠ ቅጣት እንደሚጣልባቸው አስረድተዋል።
ክልከላቸው የመድኃኒት ግዥን እንደማያካትት፣ ከአስፈላጊነቱ አንፃር የመድኃኒት ገዥ ተቋም ኃላፊነት እንዲወስድ መደረጉን አቶ ሰጠኝ አክለዋል። የትምህርት መሣሪያዎች ለሚቀጥለው ዓመት ቀድመው መገዛት ስለሚኖርባቸው፣ የግዥ ፈቃድ እንደሚያገኙ አስታውቀዋል።
የግዥና ንብረት ባለሥልጣን ያስተላለፈው ውሳኔ የክልል ተቋማትን የማያካትት መሆኑን፣ ግዥን በተመለከተ ክልሎች ራሳቸው እንደሚወስኑ ነገር ግን ተጠሪነታቸው ለፌደራል መንግሥት የሆኑ ሁሉንም ተቋማት እንደሚመለከት ገልጸዋል።
ተቋማቱ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ትዕዛዙን ተላልፈው ግዥ ቢፈጽሙና ኦዲት በሚደረግበት ወቅት ቢረጋገጥ፣ ሪፖርቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ቀርቦ ከመጪው ዓመት በጀት ቅነሳን ጨምሮ የተለያዩ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ አቶ ሰጠኝ ጠቁመዋል።
ከ2013 በጀት ዓመት አንፃር የ18 በመቶ ዕድገት የታየበት የፌደራል መንግሥት የ2014 ዓ.ም. በጀት ለመደበኛ ወጪዎች 162 ቢሊየን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች 183.5 ቢሊዮን ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 203.9 ቢሊዮን ብር፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 12 ቢሊዮን ብር፣ በአጠቃላይ 561.6 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል። በጦርነቱ ሳቢያም 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መፅደቁም አይዘነጋም፡፡