Sileshi Yilma Reta

 · ዝክረ- አርበኞች (አንድ)

ከወራት በፊት የተከበረውን 119ኛውን የአድዋ ድል መታሠቢያ በዓል በማስመልከት ለተከታታይ ቀናት የተለያዩ ፅሑፎችን በአማርኛና በእንግሊዝኛ በማቅረብ በዓሉን ለመዘከር ሞክሬ ነበር። በተመሣሣይ ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም የሚከበረውን “የአርበኞች መታሠቢያ ቀን”ን የሚዘክሩ ልዩ ልዩ ፅሑፎችን ከዛሬ ጀምሮ ማቅረብ እጀምራለው።

አጋጣሚው የሀገራችንን ባለውለታዎች ምሥጋና የምናቀርብበት ሲሆን፤ እግረመንገዳችንንም እውቀት የምንለዋወጥበትና የሠለጠነ ውይይት የምናከናውንበት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። ለዝክሬ ማሟሻ የሆነውን ተከታዩን ፅሑፍ ያገኘሁት አንድርዜይ ባርትኒስኪና ዮዓና ማንቴል-ኒየችኮ ጽፈውት በዓለማየሁ አበበ “የኢትዮዽያ ታሪክ (ክፍል ሁለት-2003ዓ.ም)” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ከመለሠው መጽሐፍ ነው።

የፅሑፉ ማጠንጠኛ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ኢትዮዽያን በቁጥጥሩ ስር የማድረግ ሙከራ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች (በወቅቱ አጠራር ጠቅላይ ግዛቶች)በአርበኝነት ንቅናቄ መሪነት ተሠማርተው ሕልሙን ያከሸፉበትን ድንቅ የኢትዮዽያ የቁርጥ ቀን ልጆች ነው። (የቦታዎቹና የአርበኞቹ ቅደም ተከተል መፅሐፉ ላይ በተቀመጠው መሠረት ነው የቀረበው)

“የአርበኝነቱ ትግል ይበልጥ በተጠናከረበት በሸዋ ውስጥ እጅግ ጐልተው ሚታወቁት መሪዎች ውስጥ ባላምባራስ አበበ አረጋይ፣ ደጃዝማች ፍቅረ ማርያም፣ደጃዝማች አውራሪስ፣ ደጃዝማች መንገሻ ወሰኔ፣ ደጃዝማች መስፍን ስለሺ፣ ደጃዝማች ሀብተ ሥላሴ፣ ደጃዝማች ኃይሉ ወልደ መድህን፣ወ/ሮ ከበደች ስዩም፣ ባላምባራስ በሻህ ኃይሌ፣ ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ፣ ደጃዝማች ተሾመ ሸንቁጥ፣ ደጃዝማች ዘውዴ አስፋው፣ ፊውታራሪ ተድላ መኰንን፣ ፊውታራሪ ፀሐዩ እንቁየ ሥላሴ፣ ፊታውራሪ ወልደ ጻድቅ፣ ፊታውራሪ ከበደ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ፊታውራሪ መኰንን ወልደ ጊዮርጊስ፣ ፊታውራሪ ተሰማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ፊታውራሪ ዳርጌጌ ጐርጂ፣ ፊታውራሪ ኃይለ ማርያም ቸሬ፣ ፊታውራሪ ደምሴ ወልደ አማኑኤል፣ ፊታውራሪ ከበደ ብዙነሽ ሜታ፣ ከንቲባ ከበረ ኃይለ ሥላሴ፣ ልጅ ኃይለ ማርያም ማሞ፣ ቀኛዝማች ጐበዜ፣ ቀኛዝማች ደጋጋ ዲዲኖ፣ ቀኛዝማች በቀለ ወልደ መድህን፣ ግራዝማች ኃይለ ሥላሴ በላይነህ፣ ባሻ ወልዴ፣ ባሻ ኤፍሬም፣ ልጅ ግዛቸው ኃይሌ፣ ልጅ ተኰላ ድል ነሳሁ፣ልጅ ሣህሌ እንቁየ ሥላሴና አቶ ተሰማ ዕርገቴ እና ሌሎችም ይገኛሉ።

ከትግሬ የተቃውሞ ንቅናቄ መሪዎች ውስጥ ደጃዝማች ገብረ ህይወት፣ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ፣ ደጃዝማች ዓባይ ካሣ፣ ደጃዝማች ውብነህ ተሰማ፣ ፊታውራሪ መስፍን ረዳና ፊታውራሪ ኃይሉ ክብረት እና ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸው። ራስ ስዩም መንገሻ፣ ቀኃሥ አገር ለቅቀው ከሄዱ በኋላ የተቃውሞ ንቅናቄቄ ዋጋ አይኖረውም የሚል አቋም በመያዛቸው፣ በዚህ ቀበሌ ያለውንቅ የአርበኝነት ትግል በጣም ጐድቶታል።

በበጌምድር ያለው የተቃውሞ ንቅናቄ በደጃዝማች አስፋው፣ደጃዝማች ዳኘው ተሰማ፣ ፊታውራሪ አስፋው ይግዛው፣ ፊታውራሪ በረደድ አስፋው፣ ፊታውራሪ ይማም ተሰማ፣ ልጅ ደስታና ደጃዝማች አዳነ የተመራ ነው።

በጐጃም እጅግ ዝነኛ ከሆኑት መሪዎች ውስጥ፦ራስ ኃይሉ በለው፣ ቢትወደድ ነጋሽ በዛብህ፣ ደጃዝማች መንገሻ ጀምበሬ፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ፊታውራሪ ኃይለ ኢየሱስ ፍላቴ፣ ፊታውራሪ ዘለቀ ደስታ፣ፊታውራሪ አያሌው፣ፊታውራሪ ደረሰ ሽፈራው፣ ፊታውራሪ በቀለ አምባዬ፣ ፊታውራሪ ሽፈራው ረታ፣ ፊታውራሪ በየነ ቢሻውና ፊታውራሪ ካሣ ይገኛሉ።

በሌሎች ጠቅላይ ግዛቶች ውስጥ እጅግ ታዋቂ መሪዎች መካከል በሲዳሞ ራስ ደስታ ዳምጠው፣ በአርሲ በባሌና በሐረር ደጃዝማች በየነ መርዕድ፣በሐረር፣ በጅጅጋና ጨርጨር ፊታውራሪ በዕደና ሌሎችም ይገኛሉ። የኦሮሞ ሕዝብ ተወላጅ የሆኑት ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ በወሊሶና በአመያ የታወቁ የአርበኛ መሪ ሲሆኑ፣ እንዲሁም በወጨጫ ደጃዝማች ባልቻ፣ በጉራጌ ደጃዝማች በቀለ ወያ፣ አቶ ከበደ አቦዝን፣ በጐሬና መጌላ ደጃዝማች ተስፋዬ ወልዴ፣ በወለጋ ፊታውራሪ ዮሐንስ በቦረና፣ ፊታውራሪ ኃይለ አባ መርሳ በጋሙ ጐፋ ይጠቀሳሉ።” (ገጽ 150-151)

….. “በአዲስ አበባ ዙሪያ ገና በ 1936 በበጋው ጀምሮ አያሌ የአርበኛ ቡድኖች ነበሩ። ደጃዝማች ፍቅረ ማርያም በየነ፣ ደጃዝማች አበራ ካሣ በሱሉልታ፣ ደጃዝማች ባልቻ በወጨጫ፣ ግራዝማች ዘወዴ አስፋውና መስፍን በገፈርሳ ይዋጉ ነበር። ….” (ገጽ 151)

….. “ኢጣሊያ አገሪቱን እንደ ያዘ ወዲያው የአርበኝነት ትግል ከጀመሩት ኃይሎች ውስጥ በተለይ ሲዳሞ ውስጥ ይዋጋ የነበረው የራስ ደስታ ዳምጠው ጦር ሊጠቀስ የሚገባው ነው። … ከራስ ደስታ ዳምጠው በቀር ሲዳሞ ውስጥ ሌሎች 5 ደጃዝማቾች ይዋጉ ነበር። …በለቀምት በደጃዝማች ገብረ ማርያም የሚመራ፣ በአርሲ በበጅሮንድ ፍቅረ ሥላሴ፣ በወለጋ በፊታውራሪ ዮሐንስ፣ በጅማ በከንቲባ ታን፣ በባሌ በደጃዝማች በየነ መርድ የሚመራ አርበኛ ነበር።ኋላም እያደር አዳዲስ የአርበኛ ጦር ተፈጥሮ በሁሉም የኢትዮዽያ ጠቅላይ ግዛቶች ውስጥ ይገኝ ነበር።”(ገጽ 152-153)

ዝክረ-አርበኞች (ሁለት)

ስለ ውስጥ አርበኞች…

“…ከሴቶች የውስጥ አርበኞች ከፍተኛ ዝና ያገኘችው አርበኞች አዲስ ዓለም የመሸገውን የጠላት ጦር እንዲደመስሱ ሁኔታቸውን ያመቻቸችላቸው ሸዋረገድ ገድሌ ናት። የውስጥ አርበኞች ድርጅት ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስ የቻለው በሁለቱ ከተሞች፣በአዲስ አበባና በጐንደር፣ ነው። በተለይም በዋና ከተማው የምድር ባቡር ሠራተኞች በመዋቅሩ የተጫወቱት ቁልፍ ሚና እንቅስቃሴውን ላብ አደራዊ ባሕርይ ሰጥቶት ነበር።

ባጠቃላይ ጣልያኖች ናላቸው የዞረው አርበኞቹ ከሚያደርሱባቸው ጥቃት ይልቅ የውስጥ አርበኞቹ በሚያደርሱባቸው ግዝገዛ ነበር ማለት ይቻላል። ምክንያቱም አርበኞቹ በርቀት የሚወጓቸው ሲሆኑ፣ የውስጥ አርበኞቹ ግን እነሱኑ መስለው፣ አንዳንዴም ቢጠራጠሩ እንኳ እንዳይያዙ የሽፋን ስም እየተጠቀሙ በመሆኑ ነው።” (ገጽ 181)

ምንጭ፦ “የኢትዮዽያ ታሪክ ከ 1847 እስከ 1983” (በፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፣አአዩ ፕሬስ፣ 2003)