· ቱሉ ፎርሳ በነሐሴ ወር 1968 እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በጎሕ መፅሔት ላይ ለአንባብያን የቀረበ ሥነ ፅሁፍ ነው።

የቱሉ ፎርሳ ደራሲ አይታወቅም ። ማን ያውቃል አሁን በሕይወት ሊኖርም ላይኖርም ይችላል።የደራሲውን እጣ ፈንታ ባናውቅም ሥነ ፅሁፉ ግን ዘላለማዊ ነው። የዘመን መቀያየር እንኳ የሥነ ፅሁፉን ውበት ሊቀይረው አልቻለም።አሁንም ከብዙ ጊዜ በኋላ ሥነ ፅሁፉ የማይሰለች ነው።

”ቱሉ ፎርሳ

ቱሉ ፎርሳን ማን የማያውቅ አለ ? እናንተ አታውቁትም እንዴ ? ቱሉ ይሄ ማካሮኒ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠራው እኮ ነው። ኦ ቱሉን ማን የማያውቅ አለ? ቱሉ ሠላሳ ዓመቱ ነው።ወይም ወደዚያ ግድም ነው። እና ቱሉ ቁመቱ ረጅም ነው። የቱሉ እጆች ትላልቅ ናቸው።የቱሉ ክንዶች ጠንካሮች ናቸው።የቱሉ መዳፎች ሸካራ ናቸው። ቱሉ ከማካሮኒ ፣ፓስታና ፓስቲኒ ፋብሪካ ውስጥ ወፍጮ ክፍል ነው የሚሠራው። ወፍጮ ክፍል ስድስት ዓመት ሠርቷል። የፋብሪካው ባለቤት ሙሴ ጋሌብ ናቸው። ጌታ ጋሌብ እዚች ሃገር (ይቺው የኛይቱ የምንላት) ሲገቡ ቤሳቤስቲን አልያዙም።

እዚህ ከገቡ በኋላ ነው ይህንን ሁሉ ያፈሩት፣ ያንን ሁሉ ቪላ ሠርተው የሚያከራዩት፣ያንን ሁሉ ሱቅ የከፈቱት። ጌታ ጋሌብ የናጠጡ ዲታ ናችው።አቤት ሠራተኛ ሲፈራቸው።ጌታ ጋሌብ ሽማግሌ ናቸው።አጭር ፣መላጣ ባርኔጣ የማይለያቸው አማርኛ አቀላጥፈው የሚያውቁ ዕድላም ሰው ናቸው። ስለ አበሻ ሲናገሩ << አበሻ ሥራ አይወድም።አበሻ ሠነፍ ነው።ለዚህ ነው ሃብታም የማይሆነው — እንደኔ>> ይላሉ።

ቱሉ ፎርሳ በወር ሠላሳ አምስት ብር ያገኛል።ያ ደመወዝ ነው። ቱሉ ፎርሳ ሲሏችሁ ፎርሳ የአባቱ ስም እንዳይመስላችሁ።አይደለም።የወፍጮ ቤት ሥራ አታውቁትም እንዴ? ስንዴ በካሚዮን ይመጣል። ከካሚዮን ወደ መጋዘን ይጋዛል።ከመጋዘን ወደማንጠርጠሪያው የወንፊት ሞተር ቤት ይወስዳል።ከዚያ ይታጠባል።ከዚያ በሞተር ይደርቃል። ከስንት ጣጣ በኋላ ይፈጫል። ዱቄት በጆንያ እየታሰረ ወደ ቡኮ ክፍል ይተላለፍል።ይህንን ሁሉ የሚያደርገው የሰው ትከሻ ነው።ካሚዮን ሲመጣ ካቦው ሰው ይጠራል እንዲያወርዱ፤ << አንድ ሁለት ፎርሳ …. >> ከመኪናው ላይ ኩንታሉን እየተሸከሙ ወደ መጋዘን ትንንንን…..እና በስራ ቱሉን የሚያህል የለም። ኩንታል ተሸክሞ ሲበር ጭብጥ ላባ የያዘም አይመስልም። ሁል ጊዜ በጩኸት << አንድ ሁለት ፎርሳ …. >> ይወዳል ።

ለዚህ ነው ቱሉ ፎርሳ ተብሎ የቀረው እንጂ ያባቱ ስም ሆኖ አይደለም። የቱሉ ሚስት ጠንፌ ነው የምትባለው። እንጀራ ለመግዛት ጉልት የሄደ ሁሉጠንፌን ያውቃል። መሽት ሲል ወደ ጉልት ብቅ ያለ ጠንፌና የእንጀራ ሰፌዷን ይለምዳል። መሸት ሲል የቀን ሠራተኞች ወደቤታቸው ይመጣሉ። እግረ መንገዳቸውን እንጀራ ይገዛሉሲመሽ የእንጀራ ገበያ ይደራል።

<<እሲኪ እንጀራው?>> ይላል ጠጋ ይልና።

<< ይኸው ወርቅ የመሰለ እንጀራ >> ይባላል።

<< ጤፍ ነው ቅይጥ ይላል ላፉ።>>

<< ንጹሕ የበቾ ጤፍ >> ተብሎ ይነገረዋል።

ጠንፌ ዘንድ ግን ብዙዎቹ እንዲያ ብለው አይጠይቁም። ብዙዎቹ ስለሚያቋትዝም በለው ነው የሚገዟት አንዳንዴም ከተጠየቀች።

<< ጤፍ ነው ? >>

<< ትንሽ ዘንጋዳም አለበት >>የቀን ሠራተኞች ላፋቸው ነው የሚጠይቁት።

ያገኙትን ነው የሚገዙት። የሚገርመው ነገር የቀን ሠራተኞቹ ወንደላጤዎች ናቸው።የቀን ሠራተኞቹ ወጥ አይሠሩም። የቀን ሠራተኞቹ ብዙ ሆነው በትንሽ ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት።ታዲያ ለምን ዳቦ(ሞፎ) ገዝተው አይበሉም? ሞፎ ወጥ አያስፈልገውም። ሞፎ የወንደላጤ ምቹ ምግብ ነው። ግን የቀን ሠራተኞቹ እንጀራን ይመርጣሉ። ደርቅ እንጀራ ማላመጥ ደስ ይላቸዋል። ምንአልባት የቀድሞ ቤታቸውን ፣ የወትሮ ትዳራቸውን የሚያስታውሳቸው እየመሰላቸው ይሆናል።እንጀራ የወደፊቱ የተስፋ ምልክት እየመሰላቸው ይሆናል።

ጠንፌ አንድ ሃያ አምስት ዓመት ይሆናታል።ጠንፌ ከሁለት ዓመት በፊት ቱሉ ፎርሳን አገባች። በፊትም ከአያቷ ጋር ስትኖር የመንደር እንጀራ ጋጋሪ ነበረች፡፤እንጀራ መጋገር እንዴት ዓይነት ሥራ መሰላችሁ? አንዱ ቤት ሰላቢ ነች ይላሉ፣ ሌላ ቤት ማገዶ አይመክታትም ይላሉ፣ ሌላው ቤት እንጀራ ታወፍራለች ፣ ሌላው ቤት ታሳሳለች…….. ጣጣ ነው። በመጨረሻ አያቷ ሲሞቱ ጋግሮ ከማብላት ይልቅ (በሦስት ብር ተቀጥሮ ) ጋግሮ መሸጥ ይሻላል ብላ በነጋዴነት ተጠቃለለች፡፤ከቱሉ ጋር የተዋወቁት በእንጀራ ደንበኝነት ነው። ሆሆይ!! ይሄ ደግሞ እራሱን የቻለ ታሪክ እኮ ነው።

ታዲያ ጠንፌ ወንድ ልጅ ወለደች። ልጁ ደግሞ ጤና የለውም፤ እሷንም ጤና ነሳት እቴ። የእንጀራ ንግዱም አላዋጣ አለ እንደ ዱሮ እርካሽ ዱቄት ፍለጋ መንከራተት አለ፣ ማገዶ ፍለጋ አገር ጥሎ መሄድ አለ።… እረ ስንቱ ።በዚህ ላይ ልጇ ጤና የለውም። ባሎች ሁሉ ሚስቶቻቸውንይማታሉ።ባሎች ሁሉ ይሰክራሉ።ቱሉ ግን አይማታም ፣ አይሰክርም ፣ ከጠንፌ ምንም አይደብቅም።አምላኩ ጠንፌ ናት ።ያለ ጠንፌ ምን ሕይወት አለውና! ጠንፌም ባሏን ትወዳለች ፣ ታከብራለች።

<<ጠንፌ!>>

<<አቤት።>>

<<ዛሬ ደመወዝ ተቀብዬ ከጓደኞቼ ጋር ጠላ ቤት ገብቼ ስልሳ ሳንተም አጠፋሁ።>>

<<ደግ አረክ።>>ጠንፌ ቀና ብላ አታየውም። ጠንፌ ለቱሉ ቱሉ ለጠንፌ የተፈጠሩ ይመስላሉ።ትሳሳለታለች።

<<ጠንፌ ዛሬ ደመወዝ ተቀበልኩና ስመጣ ሉካንዳ ቤት ገብቼ የሃምሳ ሳንቲም ሥጋ ገዛሁልሽ።>>

<<ጥሩ አረክ።>>

<<ከዚያ በፊት አማረኝና አንድ ብርሌ ጠጅ ጠጣሁ። ምነው ጠንፌ ከፋሽ እንዴ?>>

<<እኔቴ።>>ቱሉ ሚስቱን ትኩር ብሎም አያያትም። የምትሟማ ይመስለዋል። ይሳሳላታል።ታዲያ ልጁ እያደር ይታመም ጀመር። በተወለደ በአስር ወሩ የጠና ሕመም ታመመ።ይቃትት ጀመር። ያጣጥር ጀመር።

<<ሀኪም ቤት ውስጂው >> ይላሉ ጎረቤቶቹ ።

<< የትኛው ሀኪም ይሻላል? >>

<< አሮጌው አውሮፕላን ጣቢያ ያለው ጥሩ ነው። >>

<< እሺ እስቲ >> ትላለች ጠንፌ ። ለበሏ ግን አትነግረውም። ምን ብላ ትንገረው ? የቤት ኪራይ አስር አራት ብር ፣ የቤት ጣጣ ሌላውን ይወጣዋል። ምን ብላ ትንገረው ? እንጨቱ ውድ፣ እህሉ ውድ፣ የኩራዝ ጋዝ እንኳ ካቅሙ ዱሮ ሁለት ፍራንክ የሚሸጠው ዛሬ በአራትም ፍራንክ አይገኝም። ሁሉ ቀጥሏል። የረከሰ ቢኖር የሰው ነፍስ ነው።ታዲያ ምን ብላ ትንገረው ? ልጁ ጠናበት። የሰው አፍ ደግሞ አይጣል ነው።

<< በቅሎ ግዙ ግዙ ፤ አንድጨው ላይገዙ >> ማለት ያ ነው።

<< ኸረ ባካችሁ ሀኪም ውስዱት ? >> አሉ አንድ ቀን ማታ ሊጠይቁ የመጡ የመንደር አሮጊት ።

<< የትኛው ይሻላል ? >> አለች ጠንፌ ።

<< የውሬሏ ጥሩ ናት ሲሉ ሰምቻለሁ። >>

<< እንዲህ እንዳይመስልሽ ፣ አሁን የዛች የቀለሟ ልጅ ታማባት፣እንዲው በጠና ተይዛባት እዛ ሄዳ እንደው ባንድ መርፌ አዳነቻት። ደግሞ ዋጋው ትንሽ ነው።ሁለት ብር ከፍሎ ካርኔ መቁረጥ ነው..በቃ!።

>>ጠንፌ ልቧ ስንጥቅ አለ። የውሬሏ ሀኪም ሁለት ብር። ሲመሽ የታመመው ዕፃን ከቶውንም ጡት መሳብ ተሳነው። ያ የፈራችው ሊመጣነው። ወልዶ መቅበር ላይቀርላት ነው።አዬ ሰው መሆን።

<<ቱሉ?>>

<<ምን አልሺኝ ጠንፌ ?>>

<<ሁለት ብር አለህ?>>

<<አይ አሁን? …… እንዴት ? እኔ ሁለት ብር ነው ያልሺኝ?>>

<<አወን ሁለት ብር ለውሬሏ ሀኪም የሚከፈል።>>

<<ሀኪም መሄድ ያስፈልጋል?>>

<<አወን በጣም አሞታል። አታየውም ትኩሳቱን?>>

እ ….. ይሁን…. ጠዋት እበደራለሁ፣ ግድ የለም ጠንፌ አታስቢ። ሕፃኑ መቃተቱን ቀጠለ። ከቶውንም ማልቀስ እያቃተው ሄደ። ጠንፌ ለባሏ የሚበላውን ሰጠችውና ልጅዋን አቅፋ ቁጭ አለች። – እንብላ እንጂ ጠንፌ ?- እኔ ስበላ ነው የዋልኩት እባክህ። የሴት ነገር ስቀምስም ስበላም ጠገብኩ። ቱሉ የቀረበለትን እንጀራ ፍርፋሪ በኩራዙ ብርሃን አስተዋለው። ትናንት ከፊቱ የተነሳው የሻገተ እንጀራ ነው።ጠንፌ ዋሽታለች። ጠንፌ ምንም አልቀመሰችም። ጠንፌ ጦሟን ልታድር ነው —– ለሱ ብላ።ጠንፌ ልጆን ታቅፋ በዓይኗ እንቅልፍ ሳይዞር ነጋላት። ቱሉ ብር ሊበደር ወደ ፋብሪካ ሄደ። በሽተኛ ሕፃን ፣ ምስኪን እናት እንባ በትንሿ ጎጆ ውስጥ ቀሩ።ቱሉ ጠዋት ተነስቶ ወደ ፋብሪካ ሄደ ። ፈቃድ ተቀበለ።በደንቡ መሠረት ፍቃድ የወሰደ ደመወዝ የለውም ። ቢሆንም መቼስ ምን ይደረጋል ? ልጅህ ሞቷል ና ቅበር ከመባል ልጄ ሞቷል ኑ አቃብሩኝ ማለት ይሻላል።ጠዋት ሠራተኞቹ ወደ ስራ ተሰማሩ ።

<< አንድ ሁለት ፎርሳ ፣ አንድ ሁለት ፎርሳ…… >>

እንዴት ያለ ዘፈን ነው? ሠራተኞች ጆንያውን ተሸክመው ይበራሉ። ጆንያ ተሸክሞ በዝግታ መራመድ እራስን መጉዳት ነው ። መሮጥ ነው የሚበጀው። ማን ዝግ ብሎ ?

ያውስ ካቦው << ዳይ ፣ዳይ፣ ዳይ ፣ ሲል መቼ ፋታ ይሰጣል።

ቱሉ እንደ እንግዳ ሠራተኞቹን ቆሞ አስተዋላቸው። እንደ ጅል ተመለከታቸው። ጠጉራቸው ዱቄት ለብሷል። ግንባራቸው ዱቄት ተለቅልቋል። ልብሳቸው ዱቄት ተነስንሷል። ወደ አንገታቸው የሚንቆረቆረው ላብ ፊታቸው ላይ ትናንሽ ጅረቶች የሠሩ ይመስላሉ። ጫንቃቸው ጉብጥ ያለ ይመስላል።ትንፋሻቸው ቁርጥ ቁርጥ ይላል። ሰዎች በጣም ይሠራሉ።ያም ሆኖ ጌታ ጋሌብ አስተያየት ሲሰጡ << አበሻ ሥራ አይወድም ፤ሰነፍ ነው ። ለዚህ ነው እንደኔ ዲታ የማይሆነው >> ይላሉ።

ሠራተኞቹ ለብዙ ዘመናት ሙሉ ቀን ሲሰሩ ነው የሚውሉት። ዲታ ግን አልሆኑም። ከቶውንም መናጢ ናቸው። ቀደም ብሎ ብድር የጠየቃቸው ሠራተኞች ሁሉ ሁለት ብር የላቸውም። አበበ እንዲውም የሞፎ ዋጋ መክፈል አቅቶት ብድር ተከልክሏል። ከለላ ትላንት የጎማ ጫማውን ሸጦ ነው እራት የበላው። እርገጤ የቤት ኪራይ መክፈል ተስኖት ሊባረር ነው። ተክሌ የኮሾ ሲጋራ መግዣ ፍራንክ አጥቶ ያዛጋል።ሁሉም ምስኪን ነው። ሠራተኞች ብዙ ይሠራሉ። ብዙ ገንዘብ ግን አያገኙም።ማንን ይጠይቋል ?

ማንን ይለምኗል ?

ቱሉ በሙሉ ሠራተኞቹን በብድር ጥየቃ አዳርሶ ሳይሳካለት ቀረ።ማንም ገንዘብየለውም። ገንዘብ ያላቸው ምናልባት የቢሮ ሠራተኞች ናቸው። እነርሱ ቢሮ ደግሞ << ያለ ሥራ መግባት ክልክል ነው። >> ደግሞ ከቢሮ ቢሮ ሲንጦለጦል ጌታ ጋሊብ ቢያዩትስ? በካልቾ ብለው ከሥራ ወዲያውኑ ያባርሩታል። ቱሉ ከፋብሪካው አጥር ሲወጣ ችግሩን ለዘበኛው ለበቀለ አወያያቸው።

አቶ በቀለ ምንም እንደሌላቸው ይልቁንም በሌት ዘበኝነት የብርድ መከላለያ አሮጌ ካፖርታቸውን ማስጣፊያ ገንዘብ በማጣት እትት ሲሊእንደሚድሩ አዋዩት።አልሆነም።ሁለት ብር ቢያገኝ ኖሮ ልጁ ይታከም ነበር። ሁለት ብር ቢኖር ኑሮ ምንናልባት ልጁ ይድን ነበር። የውሬሏ ሀኪም እጅዋ መድኃኒት መሆኑን ጠንፌ ነግራዋለች።ሁለት ብር ከየት ይመጣል።የለበሰው አሮጌ ቱታ ምንም ዋጋ አይወጣም። ከመኪና ጎማ ውዳቂ የተሠራው መጫሚያው ስሙኒም አይሸጥ። አቤት ድህነት ፤መልኩ ምንኛ አስቀያሚ ነው ? ቱሉ ሰማይ ምድር ዞሮበት አውራ ጎዳናውን ተከትሎ ሲንገላወድ ከፀሐይ ቡና ቤት አጠገብ ደረሰ። ፀሐይ ቡና ቤት የወይዘሮ ፀሐይ ንብረት ነው። ከመንገዱ ዳር የተሰራ አምሮ የተሰራ ቤት ነው። መኝታ ክፍሎች አሉት። የአበባ መደብ አለው ። ምግብ ቤት አለው። ፀሐይ ቡና ቤት ተራ ሰው አይገባም። ሠራተኞች በውጭ ሲልፉ የቤቱን ድርጅት ከማድነቅ በቀር ገብተው አያውቁም። ቱሉ ከፀሐይ ቡና ቤት ግቢ ሰተት ብሎ ገባ። ወደ ጓሮ ዞረ። አንድ ምግብ አቅራቢ ትኩር ብሎ አየው።- የኔ ወንድም ፤ ወይዘሮ ፀሐይ አሉ ?- አወን አሉ ። ማን ነው የፈለጋቸው ? – ተልኬ ነበር ብቅ ብታስደርግልኝ ። – ማን ነው የላክህ ?

– የለም እዚህ ላይ ያሉ ዲታ ናቸው ።ምግብ አቅራቢው ገብቶ ወይዘሮ ፀሐይን ጠራቸው። ወይዘሮ ፀሐይ ቆንጆ ናቸው ይባላል፤ ወፍራም ናቸው። ጉንጫቸው ብርቱካን ይመስላል። ገና ብቅ ሲሉ ተንደርድሮ እግራቸው ስር ወደቀ።<

< በንብረትዎ ፤ በትዳርዎ ሲሉ ይለመኑኝና ሁለት ብር ያበድሩኝ። እንደው ደፈረኝ አይበሉና ሁለት ብር ስለነፍስ ብለው ልጄ ታሞብኛል … >><< ሂድ ወዲያ !!

>> አሉና እሜቴ ፈንጠር ብለው ቆሙ ።

<< የማንም ዕብድ መጫወቻ አደረገኝ እንዴ ! እከከከ ሌባ ቀጣፊ ሠርተህ አትበላም ? እንዲህ ነችና ፀሐይ … >> እንደ ወፈፌነት አደረጋቸው ። ዘበኛው መጣና ፤ << ሰውዬ ቀስ ብለህ ውጣ ሳትደበደብ >> አለው።

ቱሉ ዓይኑ ረጠበ ። ቅልጥሙ ካደው ። ይንቀጠቀጥ ጀመር ። እየተገላመጠ ከግቢው ወጣና ካጥሩ ስር ኩርትም አለ። ዘበኛው መጣ።

– ስማ ሰውዬ ምን ሆነሃል ?

– ፍርሃት ይዞኛል ። – ቤት የለህም ?

– አለኝ ቤት ነው ? እ…. የኔ ቤት እ…

– ሰክረሀል መሰልቱሉ ደረቅ ሣቅ ያዘው ። ከቶውንም ይንፈቀፈቅ ገባ ። አፈፍ ብሎ ተነስቶ ቆመ። – ሃሃ ሃሃሃ እኔ ? እኮ እኔ ልስከር ? ቱሉ ሽቅብ ይሮጥ ጀመር ። እየሳቀ ። እንደ ሰከረ ሰው ለብቻው እየፈነደቀ ። ምን ይታወቃል ሰክሮ ይሆናል ? እየሮጠ ወደ ቤቱ ሄደ ። ከደጃፉ ቆመ ። ፀጥ አለ። ለንቦጩን ጣለ ። ማልቀስ ቃጣው ። ልጁ ሞቶ አላበቃም። እንደ ደህና ሰው ወደ ቤት ገባ- ቀናህ ቱሉ ?

– እ ምን አልሺኝ ? የት ? መቼ ?- ብሩን አገኘህ ?- አዎን- ጎሽ እንካ ልጁን ያዝልኝ ። ከማማ ወደሬ ቤት ጃንጥላ ተውሼ ልምጣ ፤ ፀሐዩ ግሮአል።- ካዛንችስ ሀኪም ቤት ልትሄጂ ?- አዎን- አይ አትሂጂ ጠንፌ ፤ ጠንፌ አትሂጂ ምንም ዋጋ የለውም ።እኔ እ…..አውቀዋለሁ።ዋጋ የለውም።- ምነው ? ለምን ዋጋ የለውም ?

– አሁን ስመጣ አሁን እዛጋ እንትን አገኘኝ ።

– ምን?- ይሄ ምንድነው ስሙ ? ት …. ትልቅ ሰው ።ጠጉሩ በ ….. በጣም ትልቅ። ትልቅ ትልቅ ቃልቻ አገኘሁ። ዋዋ ….. ዋና ባ …. ባሕታዊ መስቀል ሁሉ የያዘ ትልቅ አዋቂ አ …… አዋቂ ።

– ታዲያ ምን አለህ ?

– አትድከም አለኝ።

– አትድከም?- አ …… አዎን ። ልጁ አ …… አይ አይ …… አይድንም አለኝ።ጠንፌ ከመሬቱ ላይ ልጅዋን እንደታቀፈች ሟሟች ። በክንድዋ የታቀፈችው ሕፃን ገለጥ አድርጋ ፊቱን አየችው ትኩሳት የጠበሰው ጨቅላ በትኩስ እንባ ቀቀለችው። ተንሰቀሰቀች። << ልጄ ወይኔ ልጄ >> ብላ በተሸፈነ ድምፅ አለቀሰች። ቱሉ ቤቱን ጥሎ ወጣ ። ራቅ ብሎ ከምድሩ ላይ ቁጭ አለ።

<< ወይኔ ልጄ ልጄን በላሁ ።ነፍሴን በውሸት ሸጥኩ – ወይኔ ወይኔ >> አለ።

ይነደው ጀመር። ቱሉ ዋሽቶ አያውቅም አለዛሬ። አይሆንለትም። ያየውን አላየሁም ያለበት ጊዜ ነበር ። ሳያይ አየሁ ያለበት ጊዜ ግን አለ ዛሬ …… ቱሉ እንባ አልወጣውም። አንጀቱ ግን ተንሰፈሰፈ ፤ ቁጭ ብሎ ወባ እንደያዘው ይንዘፈዘፍ ጀመር ።

ስለኑሮው እያሰበ እራሱን ረገመ – ቱሉ ፎርሳ ምነው ወደክ እንዴ ?-

እእ ….. እኔ አወን ። የለም አለሁ ።- በል ተነስ እንካ ትንሽ ገንዘብ ።- ገንዘብ? ምንድነው እሱ ጋሼ ምትኩ ? ል ….. ልጄ ሞተ ?የእድር ገንዘብ ነው እንዴ ?

– ምንድነው የምትለው ቱሉ ፎርሳ ? ትቃዣለህ ልበል ? እንካ ሃያ ብር የሠራተኛ ማህበር ብድር ነው። ወደ ፊት ትከፍላለህ።

– ማ … ማህ …. ማህበር ? የኛ ማህበር ? ለኔ ለ …. ለኔ ነው ሃያ ብር ።

– ኋላ ትፈርማለህ ። አሁን እቸኩላለሁ ። ወደ ፋብሪካ ልመለስ ነው ። ጠፍቼ ነው የመጧሁት ልሰጥህ ። ቱሉ ብቻውን ቀረ ። እሱና ሃያ ብሮቹ ። አንድ ቀይ አንድ ቢጫ ፤ አምስት አረንጓዴ ብሮች – – – የሚሰራው ጠፋው ።ፊቱን ጠረገው ።ቆጠረው

<<አልማለሁ ልበል >>አለ ለራሱ እራሱን አርገፈገፈው።

<< የለም ሕልም አይደለም >> እየሮጠ ወደ ቤቱ ገባ ። ጠንፌ ከልጇ ጋር ተኮራምታ ትንሰቀሰቃለች። በሩን በርግዶ ዘሎ ገባ ።

<<ጠንፌ ጠንፌ >>ብሎ ተጣራ ። ቀና ብላ አየችው ። ፊቷ ንፍሮ ይመስላል።

– እንሂድ ጠንፌ ።

– የት?

– ሀኪም ቤት ፤ የውሬሏ ሀኪም እጇ መድሃኒት ነው ብለሽ የለም ?

– የለም ዋጋ የለውም ከንቱ ነው። – ለምን ዋጋ የለውም ?- ልጄን ከሞት አያድንም ።

– እንዴት አወቅሽ ?

– ያ ያገኘኸው አዋቂ ሰው አይድንም ብሎህ የለ ?

– እሱን ተይው አያውቅም ።- ያውቃል ቱሉ ። ሰውየው ያውቃል።ቱሉ ደነገጠ በገዛ ገመዱ እንደተተበተበ ገባው።

<< ስሚ ጠንፌ በመጨረሻ ያለኝ እኮ ሃኪም ቤት ከሄደ ይድናል ነው። >>አላት።

<<የውሬሏ ሀኪም ቤት — የካዛንቺሷ ሀኪም ቤት >> አለና ሀያ ብር አጠገብዋ አስቀመጠ ፡፤ ቀና ብላ አየችው ።

ለመጠየቅ ጊዜ የላት።ወደ ሃኪም ቤት ጠንፌና ቱሉ ልጁን ይዘው በረሩ።

በሶስተኛው ቀን ሕፃኑ እንደልብ ይጠባ ጀመር ። ዳን ያለው መቼም አይሞትም ። ብቻ ከልጁ መዳን ጋር በቤቱ ፀጥታ ሰፈነ።እንደ ቀድሞው መነጋገር መጨዋወት ቀረ። ሁለቱም ተፈራሩ። ጠንፌ ባሏን ሰረቅ አድርጋ ታይና ቁና ትተነፍሳለች። ለመጠየቅ ትከጅልና መልሳ ጥያቄውን ትውጠዋለች። አንድ ማታ ከራት በኋላ ድፍረቷን ሁሉ ሰብስባ

<<ቱሉ>> አለችው ። ድምፅዋ ፀጥታውን ሲሰብር ቤቱ የፈረሰ ያህል ሆነ፡፤ – ቱሉ- ምነው ጠንፌ ?- አንድ ነገር ልጠይቅህ ?

– ምንድን ነበር ጠንፌ?

– ሃያውን ብር ከየት አመጣኸው ቱሉ?ድንገት በሩ ተንኳኳና ተከስተ ገባ ። መሽቷል ፤ ሦስት ሰዓት ሊሆን ነው።

– እንዴት አመሻችሁ ሕፃኑስ ደህና ዋለ?

– ደህና ነው፣ አሁንማ ተሻለው ።ምንም አይለውም- ጥሩ ጥሩ ። እንኳን ተሻለው ጃል። እኛማ በቀደም ደንግጠን ።

– አረፍ በል ጋሼ ተከስተ !

– የለም ልሂድ ፣ እቤት አልደረስኩም ። ገና ከስብሰባ መውጣቴ ነው ።

– ስብሰባ እሰከ አሁን የሚያቆይ?

– አወን እባክህ ሰሞኑን እንድ ትዕዛዝ መጥቷል።

– የምን ትዕዛዝ ?

– ማኀበሩን አፍርሱ የሚል ።

– ማኀበሩን ? ማን? የ …. የት ? …. እ … እንዴት ? ማ … ማን አባቱ ?

– ከሚኒስተሩ ነው አሉ ። – አኮ ለምን ?

– ሙሴ ጋሌብ ሠራተኛውን ስራ አስፈታ፤ አባለገ ብለው አመልክተው ነው ይባላል። ብቻ ገና ነው እስኪ እንሰማው የለ ? በሉ ደህና እደሩ እቸኩላለሁ።

ተከስተ ፋብሪካው ውስጥ መካኒክ ነው ። ተከስተ የሠራተኛው ማኀበር ፀሐፊ ነው ። ተከስተ ማለፊያ ሰው ነው ። ተከስተ ከቱሉ ቤት ወጣ ። ቱሉ ከበራፉ ላይ ቆሞ በጭለማ ውስጥ የሚወዛወዘውን የተከስተን ቅርፅ ትኩር ብሎ ያየው ጀመር ። ከባሻገር ያዲስ አበባ የኤሌትሪክ ብርሃን እንደጧፍ ሲንቀለቀል ይታያል ፡፤ ከላይ ከሰማይ ከዋክብት ይፍለቀለቃሉ ። እነርሱ እንደ ጧፍ ናቸው ይባላል። ከዚያ ዳር የቱሉ ሁለት ዓይኖች አለወትሮአቸው በሲቃ ተጎልጉለው እሳት የሚተፉ ይመስላሉ ከኋላው ደግሞ ጋዝ ያለቀባት የቱሉ ኩራዝ ብልጭ ድርግም ታላለች። ቱሉ ሁለት እጆቹን በኃይል ጨብጦ ስሩ እየተግተረተረ ፣ ጥርሶቹን ነክሶ ፤ጡንቻው እስኪነፋፋ ካማጠ በኋላ፣ << ይቺ ማኀበር ነፍሴ ቆማ አትፈርስም >> አለ።