ዜና

ፖለቲካ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያላቸው አመለካከት አስደንጋጭ መሆኑ ተገለጸ

4 May 2022

አማኑኤል ይልቃል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሴቶች ፖለቲካ ውስጥ እንዳይገቡ በግልጽ ‹‹የማስፈራራት፣ የማሸማቀቅ፣ ነውር ድርጊት›› እንደሚፈጽሙ፣ ያጋጠሙት ሁኔታዎች የሚያስደነግጡና የሚያሳዝኑ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡ አንዳንድ ጊዜም የፖለቲካ አመራሮች የቦርዱን ሰብሳቢ የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ስም በመጥቀስ ጭምር፣ ‹‹አንቺ በመግባትሽ፣ አንቺ እዚህ ውስጥ በመሆንሽ ምንድነው የተጠቀምሽው? አገሪቱስ የምትጠቀመው ምንድነው? ከመሸማቀቅና ከመደነጋገር [ውጪ]›› የሚሉ ምሳሌዎች  እንደሚጠቀሙ ገልጿል፡፡

እንዲህ ዓይነት አመለካከቶች በተለይ “ግንባር ቀደም” በሆኑ የፖለቲካ መሪዎች ሲነሱ ነገሩን ከባድ እንዳደረጉበት ያስታወቀው ምርጫ ቦርድ፣ የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ተሰብስበው ባሉበት፣ ‹‹ሴቶች በፖለቲካው ዘርፍ ውስጥ በአመራርነትም ሆነ በአባልነት መግባት የለባቸውም፤›› የሚል ሐሳብ በግልጽ እንደሚነገር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስረድቷል፡፡

ቦርዱ የስድስተኛውን አገር አቀፍ አጠቃላይ ምርጫ አፈጻጸም ሪፖርቱን ቅዳሜ ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ባቀረበበት ወቅት እንደገለጸው፣ የቦርዱ አመራሮች የሴቶችን አሳታፊነት የሚወስን ሥርዓት የመዘርጋትን ሐሳብ በተደጋጋሚ ለፓርቲዎች ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኘም፡፡

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ስለጉዳዩ ለቋሚ ኮሚቴው ሲያስረዱ፣ ‹‹ሴቶች ሮጠው ማምለጥ አይችሉም፣ ስለዚህ ይህ አስቸጋሪ ነገር ነው ይላሉ፡፡ ሴቶች ፖለቲካ ውስጥ ከገቡ ማን ልጅ ሊጠብቅ ነው? ማን ቤት ሊያስተዳድር ነው? ይላሉ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አንዳንዶቹ ሁኔታውን ራሱ ነውር በማስመሰል ነው የሚያቀርቡት፤›› ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር “መጥበብ” በምክንያትነት በማቅረብ መታሰርና መሰደድን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ፣ ‹‹ይኼኛው ፆታ ከእዚህኛው ፆታ የተሻለ አቅም አለው፤›› የሚል ዓይነት አስተያየት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

አቶ ውብሸት አክለውም፣ ‹‹ይህንን የማነሳው ዛሬ እዚህ ላይ አጋጣሚው ከተገኘ ምናልባትም እዚህ ያላችሁ የምክር ቤት አባላት ነገሩ አስደንግጧችሁ ለእኛ ብቻ መሆኑ ቀርቶ መፍትሔ አሰባሰቡ፣ የእናንተም ጭምር እንዲሆን ለማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ቦርዱ የሴቶች ተሳትፎን በተመለከተ ከፓርቲዎች በኩል ያጋጠመውን ተግዳሮት ለቋሚ ኮሚቴው ያስረዳው፣ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ዕፀገነት መንግሥቱ፣ ከዚህ ቀደም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተደረገን ጥናት ጠቅሰው ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ ነው፡፡ ሰብሳቢዋ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በተደረገው ጥናት አንድም ሴት አባል የሌለው የፖለቲካ ፓርቲ፣ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ዕውቅና አግኝቶ ለምርጫ እንደሚወዳደር መታወቁን ገልጸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ቁልፍ ሚና ለመጫወት የሚያስችሉ ቦታዎች ላይ እንደማያስቀምጡ የተናገሩት ሰብሳቢዋ፣ የሴቶች ተሳትፎ ሲረጋገጥ ሁለንተናዊ በሆነና በአመራርነትም ጭምር መሆን እንዳለበት አውስተዋል፡፡

ወ/ሮ ዕፀገነት፣ ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲመዘገቡ ሊኖራቸው የሚገባ የሴቶች አባላት ቁጥርን እንደመሥፈርት ይጠቀም እንደሆነ ከጠየቁ በኋላ፣ ‹‹ምናልባት የሕግ ክፍተት ካለ እንደ አገር መሙላት እንዲቻል ሐሳብ እንድትሰጡበት እፈልጋሁ፤›› በማለት የቦርዱን አመራሮች ሐሳብ ጠይቀዋል፡፡

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን፣ ጎረቤት አገር ኬንያን ጨምሮ በሌሎች አገሮች ፓርቲዎች ተደራጅተው ሲመጡ ከአባላቶቻቸው ምን ያህሉ ሴቶች እንደሆኑ ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው፣ ቦርዱም ይህንኑ አሠራር ለመተግበር አቅዶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አክለውም ‹‹የግዴታ ገደብ (Threshold) ለማስቀመጥ አርቃቂዎቹም ተስማምተው እኛም ይሁን ብለን የምርጫ ሕጉ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ነበር፡፡ በፓርቲዎች በኩል ይህ ብዙ ተቀባይነት ስላልነበረውና ተቃውሞም ስለተነሳ ምክር ቤቱ ሳያፀድቀው አስቀርቶታል፤›› በማለት የቦርዱ ዕቅድ አለመሳካቱን አስረድተዋል፡፡

ቦርዱ ባደረጋቸው የምርጫ እንቅስቃሴዎች የሴቶች ተሳትፎ ላይ ውስንነት እንዳለ መመልከቱን የተናገሩት ወ/ሪት ብርቱካን፣ የሴቶች ዝቅተኛ የተሳትፎ መጠን በሕጉ ላይ ባይቀመጥም፣ በስምምነት ደረጃ ወጥቶ እንዲሠራ ቢጠየቅም ፓርቲዎች ፍላጎት እንዳላሳዩ ገልጸዋል፡፡ ቦርዱ ፓርቲዎች ባሏቸው ሴት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና ሴት ዕጩዎች ብዛት ጥቅማ ጥቅም በመስጠት፣ የሴቶችን ተሳትፎ ለመጨመር የሚሠራው ሥራ በቂ እንዳልሆነና የሕግ ማሻሻያ ማድረጉ የተሻለ መሆኑን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ዕፀገነት የምርጫ ቦርድ ስለሴቶች ተሳትፎ የሰጠውን ምላሽ ካዳመጡ በኋላ፣ ‹‹ለአስተያየት የማይመቹ፣ የወረዱ ነገሮች ነው እየሰማሁ ያለሁት፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹ነጣም ጠቆረም ይህች አገር የወንዶችም የሴቶችም ነች፣ እውነቱን መደበቅ አንችልም፡፡ ሕጉ ለዜጎች እስካልሠራ ድረስ ሕግ ሊሆን አይችልም የሚል እምነት አለን፤›› ብለዋል፡፡

ጉዳዩ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው የምርጫ ረቂቅ ሕግ ላይ ተካቶ ሳለ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስላልተቀበሉት መውጣቱን የኮነኑት ሰብሳቢዋ፣ ለብዙኃኑ ሕዝብ ጥቅም እስከሰጠ ድረስ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስለተቃወሙት ብቻ አንቀጹ እንዲወጣ መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሕጉ ሲወጣ የሴቶችን የተሳትፎ በግዴታነት ባለማካተቱና 50 በመቶ የሚሆኑ ሴቶችን ችላ በማለቱ፣ ምክር ቤቱ ረቂቁን ያፀደቀበት መንገድ ትክክል አይደለም ለማለት ድፍረቱ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው፣ የሕግ ክፍተቱ መሻሻሉ አስፈላጊ በመሆኑ ቦርዱ በቶሎ ተነሳሽነቱን ወስዶ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ማሻሻያው ለምክር ቤቱ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ አስመልክቶ ያነሳው ሌላኛው ጥያቄ ከ“ሴት ፖለቲከኞች የጋራ ምክር ቤት” ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድ ምክር ቤቱን የማቋቋም ሒደት ምን ላይ እንደደረሰ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

ስለጉዳዩ ማብራሪያ የሰጡት የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት፣ ሴት ፖለቲከኞችን የማሰባሰብና ማደራጀቱ ሥራ ሁለት ዓመት እንደፈጀ ተናግረው፣ ‹‹የመጀመርያው አደራጅ ኮሚቴ ተቋቁሞ መተዳደሪያ ደንቡን ከእኛ ጋር በመተባበር ቀርፀን ወደ አደባባይ ለማውጣት ስንሞክር፣ የመጀመርያው ችግር የገጠመን ከፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ነው፤›› ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሚባል ስብስብ መኖሩ “እንደ ትልቅ ምክንያት ተቆጥሮ” ችግር በመፍጠሩ፣ የ“ሴት ፖለቲከኞች የጋራ ምክር ቤት” የሚለው ስያሜ “የኢትዮጵያ ሴት ፖለቲከኞች ጥምረት” በሚል እንደተለወጠ ገልጸዋል፡፡

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዳንድ አባላትን በመላክ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን እንዳቋቋሙ ያስታወሱት አቶ ውብሸት፣ በአዲሱ ጥምረት ላይ ግን ለፓርቲዎቹ ፈቃድ ከተሰጠ ሴት ፖለቲከኞች እንዳይመጡ የሚያደርግ ሁኔታ ሊፈጠር ስለሚችል፣ ሙሉ ኃላፊነቱ ለሴቶች እንደተሰጠ ገልጸዋል፡፡ ምክትል ሰብሳቢው በዚህም የፖለቲካ ፓርቲ አባልና ፈቃደኛ የሆነች ሴት ፖለቲከኛ፣ ፓርቲዋ ቢፈቅድም ባይፈቅድም አባል እንድትሆን መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የጥምረቱ የመተዳደሪያ ደንብ ከ20 በላይ አንቀጾች ያለውና ስድስት ኮሚቴዎችን የሚያደራጅ ሆኖ በድጋሚ ተዘጋጅቶ 100 ሴት ፖለቲከኞችን ይዞ ከአንድ ወር ገደማ በፊት መቋቋሙን፣ ምክትል ሰብሳቢው አቶ ውብሸት ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡