

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርጫን በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ ማቀዱን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
4 May 2022
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎቹ ምርጫ ባለመካሄዱ እስካሁን መንግሥት መመሥረት ባልቻለው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚደረገውን ምርጫ፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ለማጠናቀቅ ማቀዱን አስታወቀ፡፡
ቦርዱ ያልተጠናቀቁ ምርጫዎችን በተመለከተ ትኩረት የሰጠው ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ በሌሎች ክልሎች የሚደረጉ ምርጫዎችን የሚያካሂደው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምርጫ ማካሄድ ሲቻል መሆኑን ተናግሯል፡፡
የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የአፈጻጸም ሪፖርቱን ቅዳሜ ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው ምርጫ ቦርድ፣ ከቋሚ ኮሚቴው ስላልተጠናቀቁ ምርጫዎች ጥያቄ ተነስቶለታል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በፀጥታና ሰላም ዕጦት ምክንያት ምርጫ ያልተደረገባቸው አንዳንድ አካባቢዎች መኖራቸውን አንስቶ፣ ቦርዱ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ባለባቸው አካባቢዎች በተያዘው በጀት ዓመት ምርጫ ለማካሄድ ስላለው ዝግጅት ጠይቋል፡፡
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የምርጫ ቦርድ ሰብሰቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በአማራ ክልል ስድስት፣ በአፋር ክልል አምስት፣ ኦሮሚያ ክልል ሰባት እንዲሁም በደቡብ ክልል ሁለት ምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ እንደሚደረግ ወይም እንደሚደገም ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ከእነዚህ ክልሎች በተለየ ሁኔታ በቤኒሻልጉል ጉሙዝ ክልል በ17 ምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ እንዳልተካሄደና በዚሁ ምክንያት መንግሥት መመሥረት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡
‹‹ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ በተመለከተ የማጠናቀቂያ ሥራው ቤኒሻንጉልን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት ብለን ወስነናል፤›› ያሉት ወ/ት ብርቱካን፣ ይኼንኑ ዕቅድ ለማሳካት የጊዜ ሰሌዳ ጭምር ከወጣ በኋላ በአገሪቱ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ሒደቱ መቋረጡን ለቋሚ ኮሚቴው አስታውሰዋል፡፡ ሰብሳቢዋ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ቦርዱ ምልከታ ማደረግ መቀጠሉንና አሁንም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ላይ ምርጫ ለማድረግ የማያስችል ሁኔታ ቢኖርም አንዳንድ ቦታዎች ላይ የፀጥታ መሻሻል እንዳለ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በክልሉ በመገኘት ምርጫውን ለማካሄድ፣ ዕቃ ለማጓጓዝና ጣቢያ ለማቋቋም የሚያስችል ሁኔታ ስለመኖራቸው ቦርዱ ተገኝቶ ጥናት እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቦርዱ ጥናቱ የሚደረግበትን ዕቅድ አውጥቶና ማጣራት የሚደረግበትን ዘዴ ለይቶ ያደራጀውን ቡድን በተያዘው ሳምንት ለመላክ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
ጥናት ለማድረግ የተደራጀው ቡድን ቢያንስ በክልሉ አብዛኛው አካባቢ ላይ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ እንዳለ ካረጋገጠ በሌሎች ክልሎች ምርጫ የሚደረግባቸውን ምርጫ ክልሎችም በማካተት ምርጫ እንደሚካሄድ አስረድተዋል፡፡
ቦርዱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ምርጫ በተቻለ መጠን በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየሞከረ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሪት ብርቱካን፣ ‹‹ጊዜው በጣም እየጠበበ መሆኑ ይገባናል፣ በተለይ የቤኒሻንጉልን ነገር ዓይናችንን ከፍተን ነው የምንመለከተውና የምንከታተለው፣ ፕላናችንና ሪፖርታችንን ለኮሚቴው የምናሳውቅ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ካልተጠናቀቁ ሥራዎች በተጨማሪ በሁሉም ክልሎች ስላልተደረገው የአካባቢ ምርጫ ጥያቄ አንስቷል፡፡ የአካባቢ ምርጫ ባለመካሄዱ የዞንና የወረዳ ምክር ቤቶች ተቋቁመው ለሕዝቡ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው የአካባቢ ምርጫን በተመለከተ ቦርዱ እያከናወነ ስላለው ቅድመ ዝግጅት ገለጻ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
የአካባቢ ምርጫ ከአጠቃላይ ምርጫ በተለየ በክልሎች ሕግ የሚተዳደር መሆኑን ያስረዱት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን፣ ክልሎች በየትኛው ደረጃ ምክር ቤት እንደሚያቋቁሙ፣ የትኛው ምክር ቤት ምን ያህል አባል እንደሚኖርና ተያያዥ ጉዳዮችን እንደሚወስኑ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ክልሎች ለአስተዳዳር ምቹነት ወይም ለውክልና በማለት የዞንና የወረዳ አደረጃጀት ላይ ማሻሻያ ቢያደርጉም አብዛኛዎቹ ክልሎች ማሻሻያዎቹን በሕግነት አጠቃለው ለቦርዱ እንዳላሳወቁ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህም ክልሎቹ ያደረጓቸውን ማሻሻያዎች ለሚመለከተው ምክር ቤት አስወስነው ለቦርዱ እንዲያሳውቁ መጠየቁን አስረድተዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የአካባቢ ምርጫ ማድረግ ቦርዱ ለአጠቃላይ ምርጫ ካወጣው ወጪና የሰው ኃይል እጥፍ ሊጠይቅ እንደሚችል የጠቆሙት ሰብሳቢዋ፣ ‹‹በተለይ በቀበሌ ደረጃ ምክር ቤቶቹ ሰፊ ስለሚሆኑና ብዙ አባላት ስለሚኖሯቸው፣ በዚህ ቁጥር የአባላት ምርጫን ብናደርግ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንወድቃለን ብለን ነው የምናስበው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ሲባል ቦርዱ፣ ለመራጮች የተሻለ ውክልና የሚሰጥ፣ ዲሞክራሲያዊ መንግሥትን ለማምጣት የሚያስችል፣ ክልሎች ሊቀበሉት የሚችሉትና ወጪን የሚቀንስ የምርጫ አፈጻጸምን የሚያመጣ አደራጃጀት የትኛው ነው የሚለው ላይ ጥናት እያስደረገ መሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡ ጥናቱ ተጠናቆ ምክረ ሐሳቡ ሲቀርብም ከክልሎች ጋር ለመነጋጋር እንደታቀደና ይህ ሒደትም ከአንድ ወር በላይ ጊዜ እንደማይወስድ ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡