· እንኳን ለአርበኞች ቀን አደረሳችሁ!

በዓሉን በማስመልከት ከአርበኞች ተጋድሎ የተወሰነውን የምናጋራ ይሆናል

ራስ አሞራው ውብነህ ተሰማ

—-

የኢትዮጵያ ነጻነት እንዳይደፈር፣ የሕዝቡ ሰላማዊ ኑሮ እንዳይታወክ፣ ሰላቶ በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ እንዳይሰለጥን በአጭር ታጥቀው አምሥት ዓመት ሙሉ የፋሽስትን ወራሪ ሰራዊት በዱር qከል ራስ አሞራው ውብነህ አንዱ ናቸው።

ራስ አሞራው ውብነህ ትውልዳቸው ዳባት ጃኖራ ልዩ ስሙ መረባ አስተርእዮ ሜዳ በሚባል ስፍራ ነው። ጦርና ጀግንነት ከቤተሰቦቻቸው የወረሱት ነው። አባታቸው አርበኛ ተሰማ ጋርድ በጎንዳጉንዲ እና ጉራ ላይ ከግብፅና ከቱርኮች ጋር ተዋግተው ድል ያደረጉ ጀግና ነበሩ። ወንድሞቻቸው ወፍ አይስቱም የሚባሉ ጀግኖች ናቸው።

የፋሽስት ኢጣሊያ ሰራዊት በኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ በትግሬና ኦጋዴን ወረራ ሲፈጽም ራስ አሞራው ውብነህ አዲስ አበባ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ነበሩ። የአገራችን መወረር በሰሙ ጊዜ በዱር በገደል ያለው ሽፍታ ምህረት ተሰጥቶት የስሜንን የቆላ ጠረፍ በአበጋዝነት ይዤ ከጠላት ጋር እንድዋጋ ይፈቀድልኝ በማለት ለጃንሆይ ጥያቄ አቀረቡ። ጃንሆይም ቀድሞ የስሜን አዛዥ ሁን ብለዋቸው የነበረውን ያልተቀበሉት ከብልሃት መሆኑ ገብቷቸዋልና ይሁን ብለው ፈቀዱላቸው።

ወጣቱ ራስ አሞራው ውብነህ እንደ ጥንቱ የፋኖ ባህል ትጥቅና ስንቃቸውን አጥብቀው የግራዝማችነት ማዕረግ ከደጃዝማች አያሌው ብሩ ተወብለው የአርማጭሆን፣ የበለሳንና የጃናሞራን ሕዝብ ማስተባበሩን በይፋ ገቡበት። የመጀመሪያውን ውጊያቸውን በሽሬ ግንባር አደረጉና የጠላትን ክንድ አደቀቁት። ጥቅምት 29 ቀን 1929 ዓ.ም ደብረሲና በሚባል ቦታ ላይ ሰላቶውን ገጥመው ጭዳ አደረጉት። በዚህ ጊዜ ዝናቸው አገር መናኘት ጀምሮ ነበር። ጠላትም አሞራው ውብነህን ለገደለ ሰው ከፍ ያለ ጥቅም እንደሚሰጥ እያስነገረ የባንዳውን ሆድ ማስጮኽ ጀመረ። በቤተሰቦቻቸው ላይም እርምጃ ወሰደ። በዚህ ጊዜ ራስ አሞራው ውብነህ “አንደበታችን ስለጠላት የጭካኔ ሥራ ይናገር፤ ጠመንጃችን በጠላት ግንባር ላይ ይነጣጠር” በማለት ለአርበኞቻቸው መመሪያ አውርደው ትጥቃቸውን ይበልጥ አጠበቁ። በጥር 12 ቀን 1929 ዓ.ም በጭልጋ ልዩ ስሙ ሰባሰጌ በተባለው አካባቢ ምሽግ ሰርቶ ሰፍሮ የነበረው የፋሽስት ጦር አደጋ ጥለው ደመሰሱት።

ጠላት ቂም ይዞ ሲፈክርባቸውና ሲፈልጋቸው ከቆዬ በኋላ በዓመቱ በጥር ወር 1930 ዓ.ም ጃኖራ ቀንጣ በሚባል ስፍራ ጦር ገጠማቸው። ራስ ውብነህ ተሰማ አርበኛውን አስተባብረው ጠላትን በሚገባው ቋንቋ አናግረው ውኃ ውኃ አሰኝተው ያመጣውን 12 ሺህ ጦር ግማሹን ዶጋ አመድ ሲያደርጉ ቀሪውን ማረኩት።

በጥቅምት ወር 1931 ዓ.ም የጠላት ጦር ከጎንደር ተነስቶ በለሳ ደረሰ። አሞራው ውብነህ ጥጥ መጠበቂያ ከተባለው ተራራ አካባቢ ገጠመው። የፋሽስት ጦርም ተደምስሶ የጦር መሪዎቹ ከጥቂት ወታደሮች ጋር በመሆን ለማምለጥ ሲሞክሩ አርበኞች አሳደው ያዙዋቸው። አሞራው ውብነህ ከበለሳው ጦርነት በሁዋላም ስሜን ጃንአሞራና ደረስጌ ማርያም የነበረዉን ጦር ለመግጠም ገሰገሱ።

በዚህን ጊዜ በጠላት ጦር በድንገት ተከበቡ። ጀግናው አርበኛ አሞራው ውብነህ ግን ከበባውን ሰብረው በመዉጣት ለሕዝቡ እንዲህ አሉት “ያገሬ የሰሜን ሕዝብ አይዞህ እርዳኝ፣ተባበረኝ የተከበበ አውሬ አያምልጠን “።እንደገና በጀግኖቻቸውና በሕዝቡ ማካኝነት በራሳቸውም ስልት ተጠቅመው ጠላትን አስከብበው መውጫ ቀዳዳ አሳጡት።በዚህም ወቅት እንድህ ተብሎ ተገጠመላቸው፥

የሰማዉን እንጃ ይሮም ገስገሰ፣

የጦሩ መድሃኒት አሞራው ደረሰ፤

ያየህም ተናገር የሰማህም አውራ፣

ተገናኝቶ ዋለ አሞራው ካሞራ፤

ጎንደር ከግንቡ ላይ ያለው ነጭ አንበጣ

ከምን ሊገባ ነው አሞራው ስመጣ።

የሚገርመው ደግሞ ራስ አሞራው ውብነው ከኢጣልያን ጋር ሲያደርጉት በነበሩባቸው ጦርነቶች ሁሉ ከሁለትና ከሶስት ቀና በላይ አይፈጅባቸው ነበር። ብዙም ጊዜ ሳይወስዱ አመድ ያደርጉዋቸው ነበርና። ከ1928-1934 አ.ም ከኢጣልያ ሰራዊት ጋር ባደረጉት የላቀ የጀግንነት ተግባር ‘አሞራው ‘ የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቶቸዋል።

ጣልያኖች “ካልታሰበና ካልተጠበቀ ስፍራ እየተገኘ አደጋ እየጣለ ጦራችንን በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠቃ አሞራ ነው” ይሉት ነበር። ጀግናው ራስ አሞራው ከጦር ሜዳ ዉሎ ጀግንነት በተጨማሪ በየስፍራዉ ነጋሪት እያስጎሰሙ “ለሀገር እና ለነፃነት ስትል ለፋሽስት ኢጣልያ እንዳትገዛ ፣ለሀገር ሙት ተጋደል” በማለት እያበረታቱ ማዕረግም እየሰጡ የጠላትን ከንቱ ምኞትና ፖለቲካ ባጭሩ እንዲቀጭ አድርግዋል። ለሀገሪቱ ለፃነት በብዙ አቅጣጫ የታገሉ ስመጥር አርበኛ ለሞሆን የበቁ ታላቅ ሰው ናቸው ራስ አሞራው ውብነህ።

በ1933 አ.ም የኢትዮጵያ አርበኞች ከ እንግሊዝ ወታደሮች ጋር በመሆን ፋሽስትን በማስለቀቅ ጎንደር ደረሱ። ውጊያው ከፍተኛ ዋጋ አስከፈል። ለወራት የቆየ ዉግያም ተካሄደ። ጀግናው ውብነህና አርበኞቹ በ ህዳር 19 ቀን 1934 አ.ም ከፍተኛ ውጊያ አድርገው ጀኔራሉንና ተከታዮቹን ለመማረክ በቁ ። በዚህም ጊዜ እንዲህ ተብሎ ተገጠመላቸው፥

በአርማጭሆ መንገድ፥ በወገራ መንገድ፣

በስሜንም መንገድ፥ በመረባም መንገድ፣

በበለሳም መንገድ አይተላለፉ፣

አሞራው አርበኛ ይማታል በክንፉ፤

የሮማን ነጭ በሬ ተከቧል በብረት ፣

ሊበላው ነው አሉ አሞራው ዞረበት።

ከነፃነት በሁዋላ አቶ አለማየሁ ደርቤ (በሁዋላ ደጃዝማች )፣ከንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ታዘው በተህሳስ ወር 1934 አ.ም ራስ አሞራው ዉብነህን ይዘው እንዲመጡ ወደ ጎንደር ተላኩ። ራስ አሞራው ውብነህም በአዲስ አበባ የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ግምጃ ቤት በነበረው ህንፃ ላይ አንድ ክፍል ቤት ተሰጥቶዋቸው እንዲቀመጡ ተደረገ።

በዚህም ጊዜ፣ ከነፃነት መልስ የተዋጉለት አላማ ሌላ መልክ እንደነበረው ተረዱ። በነገሮች ያዝኑና ይበሳጩም ጀመር። ይባስ ተብሎም በአርበኝነት ዘመናቸው የተሰጣቸውን ራስነት ዝቅ በማድረግ ደጃዝማችእንዲሰጣቸው ተደረገ።

ራስ አሞራውም በዚህን ጊዜ “እኔ አኮ የማእረግ ስም አልፈልግም ጠላት ያውጣልኝ ስም ‘አሞራው’ ብቻ ይበቃኛል” በማለት ተናገሩ። በታህሳስ ወር 1937 አ.ም ላዑል ራስ እምሩ ኃይለስላሴ የበጌምድርና የሰሜን ጠቅላይ ገዥ ሁነው ተሾሙ ።ራስ አሞራው ውብነህም የጠቅላይ ግዛቱ “ዳይሬክተር “ተብለው በጥር ወር 1937 አ.ም ጎንደር ገቡ።

ራስ እምሩ ለአንድ ዓመት ያህል ከሰሩ በሁዋላ በምትካቸው ቢትወደድ አንዳርጋቸውን መሳይ መጡ ።የወራሪው የጣልያን አብዛኛው የጦር መሳርያ ሰፍሮ የነበረው ጎንደር ላይ ነበር ።ታድያ ንብረቱ ተጭኖ ወደ ሌላ ስፍራ እንዲወሰድ ከበላይ ትእዛዝ ተላለፈ።

ራስ አሞራው ታድያ “ይሄ ሀብት ሲመዘበር ቆሜ አላይም ” በማለት በገዛ ፍቃዳቸው ስራዉን ለቀው ወደ አዲስ አበባ ይሄዳሉ። ከተወሰነ ጊዜም በሁዋላ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነው እንዲሰሩ ይደረጋሉ ።

ስመጥሩው አርበኛም ለሀብትም ለሹመትም ሳይሆን ለሕዝብ መብት በመከራከር አዘዉትረው ይታትሩ ጀመር ።ለዚህም ዋጋ ከፍለዉበታል።

በደርግ ዘምን ያደርጉት የነበረው ማህበራዊ እንቅስቃሴ በበጎ ያልተመለከቱላቸው የጊዜው ባለስልጣናት በ ሻምበል መላኩ ተፈራ አማካኝነት መኖርያ ቤታቸው ከሙሉ ንብረቱ ጋር እንዲወረስ አድርገዋል።

ራስ አሞራው ውብነህ በጠና ታመው በተወለዱ በ 94 አመታቸው መስከረም 5 ቀን 1975 አም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የቀብራቸው ስነ ስርዓትም የአርበኞች መካነ መቃብር በሆነው በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፀመ። ራስ አሞራው ውብነህ የፋሽስትን ጦር የሰማይ አሞራ ሁነው የዘነጠሉት ሰው ናቸው።

ምንጭ; “ያልተዘመረላቸው ቅጽ ሁለት”\ ደራሲ ፍፁም ወልደማርያም551 ShareLikeCommentShare