MAY 4, 2022 09:04 AM

 BY EDITOR 

የቤተ-ክርስቲያን መስኮት ሰብረው ከሙዳየ ምፅዋት ገንዘብ ሰርቀው ሊሰወሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ተያዙ።

በጉራጌ ዞን በሶዶ ወረዳ ጊሚሴ ቀበሌ ቤተክርስቲያን ሰብረው ገንዘብ የዘረፉ ግለሰቦች በሁለት ወንድማማች እና በአከባቢው ህብረተሰብ ትብብር ለህግ አካል እንዲቀርቡ መደረጋቸውን ወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት አስታወቀ።

ትዛዙ ፍቅሬና አብርሀም ሞላ የተባሉት ተጠርጣሪዎቹ መድሀኒዓለም ቤተ-ክርስቲያን መስኮት ሰብረው ከሙዳየ ምፅዋት ውስጥ ገንዘብ ሰርቀው ሊሰወሩ ሲሉ በመቅቡል መሀመድ፣ በሀይሩ መሀመድ እና በአካባቢው ማህበረሰብ አማካኝነት እጅ ከፍንጅ ተይዘው ለህግ አካል እንዲቀርቡ መደረጉን የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር አለማየሁ ደነቀ ተናግረዋል።

ወንጀለኛ አብርሀም ሞላ ከዚህ በፊትም ነጌሳ ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የተቀመጠ ጤፍ በመዝረፍ ክስ ቢመሰረትበትም እድሜው አልደረሰም በሚል የተለቀቀ ሲሆን ሁለተኛው ወንጀለኛም ከዚህ ቀደም የማጭበርበር ወንጀሎችን ይሰራ የነበረ ግለሰብ ነው ብለዋል።

የወረዳው ቤተ-ክህነት ሥራ አስኪያጅ መልአከ መዊ አወቀ ወንድሙ በወረዳው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቤተ-ክርስቲያናት እየተሰበሩ ሙዳየ ምፅዋቶች እየተዘረፉ እንደሆነና ዘራፊው ገንዘቡን ሳይሆን የሚፈልገው ህዝቡ ተረጋግቶ እንዳያመልክ ስለሆነ መንግስትም ሆነ ማህበረሰቡ የእምነት ተቋማትን መጠበቅና ችግሮች ተፈጥረው ሲገኙ መረጃ ለህግ አካል መስጠት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ሂደት ሁለቱ ሙስሊም ወንድማማቾች ያደረጉት ተግባር የሚያስመሰግን ነው ብለው በተያዙት ወንጀለኞች ላይም አስተማሪ የሆነ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ መናገራቸውን የሶዶ ወረዳ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታውቋል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ