ኦፌኮ የመበተን አደጋን ጨምሮ ሊከሰቱ ይችላሉ ያላቸውን  አራት ቢሆኖች አቀረበ
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረ ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) መሃል መግለጫውን ከሰጡ በኋላ

ፖለቲካ

15 May 2022

አማኑኤል ይልቃል

‹‹ከምርጫ ተገፍተን እንደወጣን ከአገራዊ ምክክሩም ተገፍተን ልንወጣ እንችላለን››

መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ የኦፌኮ ሊቀመንበር

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ መንግሥት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችንና አገሪቱን በአግባቡ መምራት ባለመቻሉ ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት እንደገባች ገልጾ፣ በቀጣይ የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን አራት ቢሆኖችን አቀረበ፡፡

ፓርቲው ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ሐሙስ ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፖለቲካ ውድቀት፣ የእርስ በእርስ ጦርነትና የኢኮኖሚ ቀውስ ተሳስረው ኢትዮጵያን እያናጉ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ የኢኮኖሚውም ውድቀት በጦርነቱ መዘዝ ሳቢያ የቀጠለ መሆኑን የገለጸው ፓርቲው፣ ‹‹ለጦርነቱ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ማበጀት ካልቻልን፣ ለአገራችን መፍትሔ ማበጀት እንችልም፣ ሕዝባችንንም ማትረፍ አንችልም፤›› ብሏል፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) በመግለጫው ላይ፣ መንግሥት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ነፍጥ ካነገቡ ታጣቂዎች ጋር የገባውን ጦርነት በድርድርና በውይይት የማይፈታ ከሆነ አራት ቢሆኖች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ የመጀመርያው ቢሆን መንግሥት ያለውን ሥልጣን፣ የአገሪቱን ሀብትና ጉልበቱን ተጠቅሞ ‹‹ጠላት›› የሚላቸውን ማሸነፍና ቀሪዎቹንም የፖለቲካ ኃይሎች የሚያፍንበት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚከሰት ከሆነም ሥልጣኑን የያዘው ገዥው ፓርቲ ደርግ ለ17 ዓመታት፣ ሕወሓት ደግሞ ለ27 ዓመታት እንዳደረጉት መግዛት የሚችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይነት የተቀመጠው የዚህ ተቃራኒ የሆነው ‹‹ቢሆን›› የትግራይ፣ የኦሮሚያ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወይም ሌሎች ታጣቂዎች መንግሥትን የሚያሸንፉበት ነው፡፡ እንደ መረራ (ፕሮፌሰር) ገለጻ፣ ይህ የሚከሰት ከሆነ፣ አዲስ ፖለቲካ ሥርዓት ማምጣት መቻልና አለመቻሉ የሚፈተንበት ይሆናል፡፡

‹‹ፖለቲካዊ መበስበስ›› ተብሎ የተቀመጠው ሦስተኛው ቢሆን፣ ጦርነቱ አሁን ባለበት ሁኔታ ቀጥሎ በመንግሥትም ሆነ ታጣቂዎች አሸናፊ ሳይሆኑበት የሚቀጥል ነው፡፡ ሊቀመንበሩ ይኼንን ቢሆን ሲገልጹ፣ ‹‹የዚህ አገር ፖለቲካ ለተወሰነ ጊዜ መበስበሱን መቀጠልና የረባ ነገርም ሳንሠራ ሞትና ሕይወት መሀል ስንንገዳገድ መዋል [ነው]፤›› ብለውታል፡፡

ይኼንን ተከትሎ የሚመጣውና አራተኛ ተብሎ የተጠቀሰው ቢሆን፣ ኢትዮጵያን እንደ ሶቪየት ኅብረትና ዩጎዝላቪያ ለመበተን አደጋ የሚዳርግ ስለመሆኑ ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ ያገባናል የሚሉ ፖለቲከኞች ካላዳኗት በስተቀር የመበተን አደጋም ሊመጣ ይችላል፤›› ያሉት መረራ (ፕሮፌሰር)፣ ፍላጎታቸው ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች በሙሉ መጠያየቅ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

ሊቀመንበሩ ከእነዚህ ቢሆኖች ውስጥ እንዲህ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው፣ ኢትዮጵያ የተሻለ ዕድል እንዲያጋጥማት ማድረግ ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ ኃይሎችና በጫካ ከሚገኙ ታጣቂች እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡

‹‹ዋናው ጉዳይ የተረጋጋች ኢትዮጵያ፣ ሰላማዊ የሆነች ኢትዮጵያ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የፈጠረች ኢትዮጵያና ሁላችንንም በእኩልነት ላይ በተመሠረተ መንገድ የምታስተናግድ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ነው፤›› ያሉት መረራ (ፕሮፌሰር)፣ ይህ ካልሆነ ጫካን ምርጫ የሚያደርጉ ብዙ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

ለእንዲህ ዓይነት ችግሮች እውነተኛ አገራዊ ውይይት ማድረግን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ያቀረበው ኦፌኮ፣ በሒደት ላይ ያለውን አገራዊ ምክክር ተችቷል፡፡ የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሡልጣን ቃሲም አገራዊ ምክክሩ፣ ‹‹አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ›› እየሄደ ነው የሚል ትችት ሰንዝረዋል፡፡ አክለውም አገራዊ ምክክር የሚደረገው በፖለቲካ ሐሳብ የተራራቁ ኃይሎችን ወደ መሀል ለማምጣት መሆኑን አውስተው፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ አገራዊ ምክክር እናደርጋለን ብለው የተሰባሰቡት ኃይሎች በፖለቲካ ዕይታቸው ምናልባት ስለኢትዮጵያ ባላቸው አመለካከት እጅግ በጣም የተቀራረቡ፣ ምናልባትም ሥልጣን ተጋርተው አገር እናስተዳድራለን እያሉ ያሉ ኃይሎች [ናቸው]፤›› ብለዋል፡፡

በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ከዚህ የራቁት ኃይሎች ደግሞ ታጥቀው ጫካ ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የእስር በርስ ጦርነት እየተካሄደ አገራዊ ምክክር ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ተቋቋመ የሚባለው ኮሚሽንም ገለልተኛ፣ አሳታፊ፣ ነፃ፣ ተዓማኒና ጫካ ባሉትም ጭምር ተዓማኒ መሆን አለበት፡፡ በዚያ ደረጃ ብቃት ከሌለው ትርጉም የለውም፣ ውጤታማ አይሆንም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ሊቀመንበሩ መረራም (ፕሮፌሰር)፣ ይኼንን ሐሳብ በማስተጋባት የተቋቋመው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ትግራይና ደምቢ ዶሎ ወይም ቦረና ጫካ ያሉትን ምክክሩ ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ አቅሙ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል፡፡ ‹‹እዚህ ያለነው ልንጨቃጨቅ እንችላልን፣ ዋናው ጉዳይ ግን ዕልቂቱና ጥፋቱ መቆም መቻል አለበት፤›› ብለው፣ ምክክሩ የታጣቁ ኃይሎችን ሳያካትት ጦርነት ከቀጠለ ምንም ውጤት እንደማያመጣ ተናግረዋል፡፡ ቀጥለውም፣ ‹‹ከምርጫ ተገፍተን እንደ ወጣን ከዚህም ተገፍተን ልንወጣ እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

በግጭቶች ምክንያት ሕይወታቸው እየተቀጠፉ ያሉ ንፁኃንን ሕይወት ለመታደግ ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲገባ ያሳሰበው ኦፌኮ፣ ይኼንን የማድረግ ኃላፊነቱ መንግሥትና ጫካ ያሉ ታጣቂዎች ላይ እንደሚያርፍ ገልጿል፡፡