የዓለም ባንክና ገንዘብ ሚኒስቴር የድጋፍ ስምምነቱን ሲፈራረሙ
የዓለም ባንክና ገንዘብ ሚኒስቴር የድጋፍ ስምምነቱን ሲፈራረሙ

ፖለቲካ

18 May 2022

ምስጋናው ፈንታው

መንግሥት በጦርነት የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መልሶ ለማቋቋም 20 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚመደበው ገንዘብ በ2015 ዓ.ም. ለሚተገበር የመልሶ ማቋቋም መርሐ ግብር የሚውል መሆኑን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ገልጸዋል። መንግሥት በሰሜኑ ጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ የሚውል ከዚህ ቀደም አምስት ቢሊዮን ብር መመደቡ ይታወሳል።

በጦርነትና በተለያዩ ግጭቶች የተጎዱ አካባቢዎችን ለመደገፍ የገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር ባደረገው የዕርዳታ ስምምነት ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ከዚህ በፊት ከተመደበው ገንዘብ በተጨማሪ ለ2015 ዓ.ም. 20 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።

ገንዘብ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጮች ለተጎዱ ሰዎች የሚውል የ300 ሚሊዮን ዶላር (15.6 ቢሊዮን ብር) የድጋፍ ስምምነት ተፈራርሟል። ድጋፉ በተለይም በጦርነት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች መሠረተ ልማትን ለመገንባትና አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ምላሽ ለመስጠት የሚያግዝ እንደሆነ አቶ አህመድ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ፆታዊ ጥቃቶች የደረሰባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ለመደገፍ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ የተገኘ መሆኑን አክለዋል። በዋጋ ንረትና በኮቪድ፣ እንዲሁም በጦርነት ምክንያት የተጎዳውን ኢኮኖሚ ከመደገፍ አኳያም የዓለም ባንክ ያደረገው ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም ሌሎች የድጋፍ ማዕቀፎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን በበኩላቸው ድጋፉ በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በተከሰቱ ግጭቶች ለተጎዱ ወገኖች ይውላል ብለዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች ለሚገኙ አምስት ሚሊዮን ሰዎችም ድጋፉ ተደራሽ እንደሚደረግ፣ በተለይም ጤናና ትምህርት ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ አክለዋል።

የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በክልሉ ስምንት ዞኖች ብቻ ከሰኔ 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ባደረገው ጥናት፣ በጦርነቱ ምክንያት ከ288 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት መውደሙና መዘረፉን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።