የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር)

ፖለቲካ

18 May 2022

ሲሳይ ሳህሉ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ሰባተኛ መደበኛ ስብሰባ ከቱርክ መንግሥት ለወታደራዊ ፋይናንስ የተደረገን ከ6.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አፀደቀ፡፡

በነሐሴ 2013 ዓ.ም. በቱርክ አንካራ በሁለቱ አገሮች የተደረገው የወታደራዊ ፋይናንስ ትብብር አንድ መቶ ሚሊዮን የቱርክ ሊሬ ወይም በአሁኑ የምንዛሪ ዋጋ ወደ ዶላር ተቀይሮ ከ6.3 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚደርስ ሲሆን፣ በገንዘቡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ቱርክ ሠራሽ የሆኑ ወታደራዊ  ቁሳቁሶችን በአምስት ዓመት ውስጥ ከቱርክ ኩባንያዎች እንዲገዛ የሚያስገድድ መሆኑን በአዋጁ ተብራርቷል፡፡

ረቂቁ  መቅረቡን ተከትሎ፣ ቱርክ የፋይናንስ ድጋፍ ስታደርግ ከኢትዮጵያና ግብፅ ጋር ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ሊያሳድረው የሚችለው ጫና በደንብ ታይቷል ወይ? የሚል ከአባላቱ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

በተለይም ዓለም በተለያየ ጎራ ተከፋፍሎ በተሠለፈበት በዚህ ወቅት ይህ የገንዘብ ድጋፍ አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ምን ያክል ታይቷል? ሲሉ የጠየቁት የምክር ቤት አባል አቶ ኡስታዝ ከሚል ሸምሱ ናቸው፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ እያንዳንዱ የአገሮች ግንኙነት ሌላ አካልን ለመጉዳት ታስቦ የሚደረግ ግንኙነት አይደለም፣ ‹‹ሁለቱ አገሮች የጋራ ጥቅም የሚያረጋግጡና የሚያስከብሩ ጉዳዮችን መሠረት አድርገው የፈጸሙት ስምምነት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም ይህ ለአምስት ዓመታት የሚቆየው የገንዘብ ድጋፍ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተደረገ ስምምነት እንጂ ሦስተኛ ወገንን ለማስቆጣት ተብሎ የተደረገ ስምምነት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡

የአገር መከላከያን አቅም ለማሻሻል ከቱርክም ሆነ ከሌላ አካል ማግኘት የሚቻለውን እናገኛለን፡፡ ምንም እንኳ ሥጋቱ የማይተው ቢሆንም ከቱርክ ጋር አብራችሁ ስለሠራችሁ የእኔ ጠላት ናቸሁ የሚል አካል ካለ ጉዳዩ ሌላ ነው የሚሆነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከቱርክ መንግሥት ከተደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ሁለቱ አገሮች በወታደራዊ መስክ፣ በትምህርት ሥልጠና በተናጠል ወይም በጋራ በሚያዘጋጁት ወታደራዊ ልምምዶች ለመካፈል፣ በመከላከያ ኢንዱስትሪ፣ በመከላከያ መረጃ ልውውጥ፣ በመከላያ መረጃ ሎጅስቲክ፣ በመከላከያ ጤና አገልግሎት፣ በኮሙዩኒኬሽን፣ አሌክትሮኒክስ፣ የመረጃ ሥርዓትና የሳይበር ጥቃት መከላከል ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የተረገ ስምምነትና የአምስት ሚሊዮን የቱርክ ሊሬ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈረመ የፋይናንስ ድጋፍ ማስፈጸሚያ ፕሮቶኮልን አፅድቋል፡፡