

22 May 2022
የብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ መስጠት እንዲያስችል ተደርጎ ሊሻሻል መሆኑን፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ ምንነት፣ አቀራረፅና አስፈላጊነት ላይ ከመከላከያና ከደኅንነት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ከፖሊሲ አርቃቂዎች፣ ከተመራማሪዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል፡፡ የደኅንነት ፖሊሲው አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ እንዳልነበረና ሊሻሻል እንደሚገባው በምክክሩ ላይ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ በግልጽ የተጻፈና ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር የተጣመረ የብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ የነበራት መሆኑን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ አምባው (ዶ/ር)፣ ትኩረቱም ከውጭ የሚመጣን ሥጋት መከላከል ላይ ብቻ ማድረጉን ተናግረዋል።
ነገር ግን አሁን ባለው ዘመናዊ አስተሳሰብ መካተት ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው፣ እነዚህን ሁኔታዎች ያካተተ አዲስ ስትራቴጂ መቅረፅ ያስፈልጋል ብለዋል። በተለይም ሰው ሠራሽ ችግሮችንና እንደ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን ጭምር መከላከል የሚቻልበትን የሚያካትት ሆኖ እንደሚዘጋጅ አስረድተዋል።
ስትራቴጂው በዚህ ወቅት መቀረፁ በአገሪቱ የሚስተዋለውን ግጭትና የደኅንነት ችግሮች ለመፍታት ፈጣን ለውጥ ያመጣል ተብሎ ባይታሰብም፣ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ለሚደረገው የረጅም ጊዜ ጥረት ግን ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል። አዲሱ ስትራቴጂ ሲዘጋጅም የመንግሥትን የደኅንነት ሥራ እንቅስቃሴዎች በግልጽ የሚታዩበትን መንገድ የሚያስቀምጥና ኅብረተሰቡም ግልጽ መረጃ እንዲኖረው የሚያደርግ በመሆኑ፣ መንግሥት የዜጎች ደኅንነት ለማስጠበቅ የገባውን ቃል ኪዳን መከታተያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
በተጨማሪም የደኅንነት ሥራ በርካታ ሀብት ፈሰስ የሚደረግበት በመሆኑ፣ ይህንን ሀብት በአግባቡ ለማስተዳደርና ብክነትን ለመከላከል ስትራቴጂው ጠቃሚ እንደሚሆን አብራርተዋል።
የኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃዕፈር በድሩ በበኩላቸው፣ ከእዚህ ቀደም የነበረው የደኅንነት ስትራቴጂ የመንግሥትን ደኅንነት ማስጠበቅ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ እንደነበር ገልጸዋል። ነገር ግን በአዲሱ ስትራቴጂ የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚቻልባቸውን መንገዶች ማመላከት ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
ከዚህ በፊት በመንግሥትና በተቋማት ላይ ብቻ መሠረት ያደረገውንና ጠባብ የነበረውን ዕይታ በመቀየርም፣ በየጊዜው ከሚኖረው ሁኔታ ጋር እየተሻሻለ የሚሄድ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም በየወቅቱ የሚኖሩ ሥጋቶችን መለየትና ዘመኑ ከሚያመጣቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ተደርጎ መዘጋጀት እንዳለበት ተናግረዋል።