በሰብዓዊ ድጋፎች ላይ ግልጽነት መኖሩ የአገር ውስጥ ዕርዳታን ለማስተባበር ወሳኝ ነው ተባለ
የቀይ መስቀል ማኅበራት የጠራው ሚዲያ ፎረም

ፖለቲካ

22 May 2022

ኤልያስ ተገኝ

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣውን የለጋሽ ተቋማት ድጋፍ ለመተካት ከተፈለገ፣ ሰብዓዊ ድጋፎች ምን ላይ እንደዋሉ መገለጹ የአገር ውስጥ ዕርዳታን ለማስተባበር ወሳኝ መሆኑ ተነገረ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ‹‹ሰብዓዊነትና የሚዲያ ተቋማት ሚና›› በሚል ርዕስ፣ ከሚዲያ ተቋማት ጋር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ባደረገው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ አወያይ የነበሩት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ቦርድ አባልና የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አብርሃም ኃይለ አምላክ (ፕሮፌሰር)፣ ከውጭ አገሮች ወይም ለጋሾች የሚገኘው ሀብት በመቀነሱ የአገር ውስጥ አቅምን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ታኣ በበኩላቸው፣ ማኅበሩ ከአደጋ ምላሽ እስከ መልሶ ማቋቋም የሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሥልታዊ በሆነ አግባብ ጥቅም ላይ እንዲውል ሚዲያው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ኮሙዩኒኬሽን ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑትና የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ንጉሤ መሸሻ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሚዲያና ሰብዓዊ ተግባር በኢትዮጵያ›› የሚል የውይይት መነሻ ጥናት ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

በጥናቱም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ይገኝ የነበረው ድጋፍና ዕርዳታ፣ በተለይም ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ እየቀነሰና እያነሰ እንደመጣ ተገልጾ፣ ስለሆነም ያለው አማራጭ የውስጥ ሀብትን ማንቀሳቀስ ሊሆን ይገባል ተብሏል፡፡

ሚዲያው ከሰብዓዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተጨባጭና አሳማኝ መረጃዎችን ከመንግሥትም ሆነ እንደ ቀይ መስቀል ካሉ ተቋማት ሊያገኝ እንደሚገባ ተጠቁሞ፣ የሚቀርቡ መረጃዎችም ዝም ብለው በግርድፉ የሚቀርቡ ሳይሆን በአግባቡ ተቀምረው በፍጥነት ተቀናጅተው የሚቀርቡ ሊሆን እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ በመድረኩ ላይ እንዳስታወቁት፣ ሰብዓዊነትን ማገዝና መጠበቅ አስፈላጊነቱ ለድርድር የማይቀርብ ነው፡፡

አቶ አማረ በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ቀይ መስቀልን ለመደገፍ የሚወጣው ገንዘብ በትክክል ለኅብረተሰቡ ይደርሳል ወይ? የሚለው አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ ይህንን ጉዳይ በአግባቡ ማሳወቅ ከተቻለ ኅብረተሰቡ በውስጥ አቅም ድጋፍ እንዲያደርግ የሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከሰብዓዊ ሥራዎች ጋር ተያይዞ አንዱና ዋነኛው ሚዲያው እየፈተነበት ያለ ጉዳይ የመረጃ ተደራሽነት (Access to Information) እንደሆነ ያስታወቁት አቶ አማረ፣ ሚዲያው ጉዳት ወይም ግጭት የደረሰበት ቦታ ሄዶ እንዳይሠራ እንቅፋት የሚሆኑበት ጉዳዮች በርካታ ናቸው ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኝ ከተፈለገ፣ የቀይ መስቀልን ጨምሮ ሌሎች አካላት ሊተባበሩ እንደሚገባ አቶ አማረ አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ  ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አገሪቱ ለተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ተጋልጣ ስትፈተን መቆየቷን ተናግረው፣ በዚህም የተነሳ በማኅበረሰብም ሆነ እንደ አገር ከቀላል አስከ ከባድ የሚባሉ ተፅዕኖዎች ደርሰዋል፣ እየደረሱም ናቸው ብለዋል፡፡        

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ጦርነትና የተለያዩ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን አስታውሰው፣ በእነዚህ ምክንያቶች የተጎዱትን ዜጎች ሕይወት ለመታደግና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን መልሶ ለማቋቋም የጤና ሚኒስቴር ከአደጋ ሥጋትና አስተዳደር ኮሚሽን፣ ከሌሎች ከሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች በተጨማሪ፣ ከቀይ መስቀልና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ተግባራዊ ዕርምጃ ሲሰጥ እንደቆየ ሊያ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በሰብዓዊ ምላሾች ውስጥ የሚዲያ ተቋማት ሰፊ ሚና አላቸው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ችግሮች እንዳይፈጠሩ አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ማኅበረሰቡ ላይ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ፣ ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ በችግሮቹ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር በመንግሥትና በተለያዩ አካላት የሚሰጡ ምላሾችን በማሳወቅ ረገድ ሚዲያው የተለያዩ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የሚዲያ ተቋማት በሰብዓዊ ሥራዎች መሠረታዊ እንደሆኑ ተገልጾ ይህም ኅብረተሰባዊ ንቅናቄ ከማድረግ፣ የዕርዳታ ማሰባሰብ ተግባር እንዲከናወን፣ ከግንዛቤ ማስጨበጫ አንስቶ መንግሥትና ረጂ ድርጅቶች ምላሽ እንዲሰጡ ግፊት በማድረግ እንደሆነ በምክር መድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

በግዮን ሆቴል በተደረገው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት የብሔራዊ አደጋ ሥጋትና አስተዳደር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ በሰጡት አስተያየት፣ ረጂ አካላት ስለቀነሱ በውስጥ አቅም ወቅታዊውን ችግር መቋቋም ይገባል ከተባለ፣ ምን ያህል ተነሳሽነቱና ኅብረሰቡን ለማነቃነቅ ተሠርቷል ተብሎ ቢጠየቅ የተሠራው አጥጋቢ አይደለም ብለዋል፡፡

አቶ ደበበ በተጨማሪም እያንዳንዱ የረድኤትም ሆነ የሰብዓዊ መብት ተቋም፣ ሚዲያውና የመንግሥት አካላት የተረጂነት መንፈስ እንዲወገድ የሚያስችል ተጨባጭ ሥራ ማከናወን እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡