24 ግንቦት 2022, 07:17 EAT

አሥመራ

ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 24 የኤርትራ 31ኛው የነጻነት ቀን ነው። ላለፉት ሳምንታት በአገር ውስጥ እና በውጪ የሚገኙ በርካታ ኤርትራውያን ይህን ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበሩት ይገኛሉ።

ለ30 ዓመታት የተካሄደውን የትጥቅ ትግል የመራው የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባርም (ሻዕቢያ) በዚሁ ቀን ነበር የኤርትራን መዲና አሥመራን የተቆጣጠረው።

ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ዳግም በኤርትራ የጦርነት ስጋት ያንዣበበ ይመስላል። ዛሬም በርካታ ኤርትራውያን የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ ተለያዩ አገራት ይሰደዳሉ። የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ክፉኛ ተጎድቷል።

ስደት

በኤርትራ ለረጅም ዓመታት የተካሄደው የትጥቅ ትግል ብዙ መፈናቀልን ያስከተለ እና አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እንዲሰደዱ ምክንያት እንደሆነ ይጠቀሳል።

ነጻ አገር ከሆነች በኋላ ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ አገራቸው መመለስ ጀምረው ነበር።

ይሁን እንጂ፣ አገሪቱ ውስጥ በተጀመረው ብሔራዊ አገልግሎት፣ የመብት ረገጣ እና ሌሎች ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ምክንያት በርካቶች መሰደዳቸውን ቀጥለዋል።

ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሕጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ኤርትራውያን ባገኙት አጋጣሚዎች ተጠቅመው አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ወደ 200,000 የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ይነገራል።

በሱዳንም እንዲሁ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እና በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ይኖራሉ።

ኤርትራ ላለፉት 31 ዓመታት ከከሰረችባቸው ነገሮች አንዱ ከፍተኛ የሆነ አምራች የሰው ኃይል ማጣቷ ሊባል ይችላል።

የመንግሥት ባለሥልጣናት የምዕራባውያን የስለላ ተቋማት እና ዓለም አቀፍ የስደተኞች መርጃ ድርጅቶች የሚከተሉት ፖሊሲ የኤርትራ ስደተኞችን ፍልሰት የሚያበረታታ ነው በሚል ይከሳሉ።

በቅርቡ ብሪታንያ ጥገኝነት የሚጠይቁ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማዘዋወር ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር ስምምነት መፈራረሟ ይታወሳል፤ ኤርትራ ይህንን ውሳኔ ተቃውማለች።

የጦርነት ደመና

ባለፉት 31 ዓመታት የኤርትራ ሕዝብ ከተጨባጭ ጦርነት እና ከጦርነት ወሬ ያረፈባቸው ጥቂት ዓመታት ብቻ ነበሩ።

ኤርትራ ነጻ አገር ሆና ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ ከሱዳን፣ ከየመን፣ ከጅቡቲ እና ከኢትዮጵያ ጋር በድንበር ውዝግብ የተነሳ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ገብታ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በወሰዱት እርምጃ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም “የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት” በመፈራረማቸው በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም ተስፋን መፈንጠቁ ይታወሳል።

በዚህ የሰላም ስምምነት የተነሳም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አግኝተዋል።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ላለፉት 30 ዓመታት በበላይነት ሲዘውር የነበረው ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ያለው አለመግባባት እያደገ መጥቶ በ2013 ዓ.ም ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ጦርነት ተቀሰቀሰ።

በዚህ ጦርነትም ከኢትዮጵያ ጋር አዲስ ዝምድና የመሰረተችው ኤርትራ ሠራዊቷን ከኢትዮጵያ ጦር ጎን አሰልፋ ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት ተሳታፊ ሆናለች።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ

በዚህ ጦርነት፣ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ እና የትግራይ ኃይሎች የጅምላ ግድያ እና ጾታዊ ጥቃት በመፈጸም በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና በሂዩማን ራይትስ ዋች ክሶች የቀረበባቸው ቢሆንም፤ ሁሉም ክሶቹን ያስተባብላሉ።

አሜሪካ ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ በኤርትራ የመከላከያና የደኅንነት ተቋማት፣ እንዲሁም በገዢው ፓርቲ፣ ድርጅቶቹ እና በባለሥልጣናት ላይ ዕቀባ ጥላለች።

ይህ ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው ጦርነት፣ ላለፉት ጥቂት ወራት ተቀዛቅዞ ቢቆይም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች አዲስ የጦርነት ዝግጅት እያደርጉ እና መግለጫዎች እያወጡ ነው።

ይህም ጦርነቱ ዳግም እንዳያገረሽ ትልቅ ስጋት ፈጥሯል።

‘ያሽቆለቆለው ኢኮኖሚ’

ኤርትራ በመጀመሪያዎቹ ሰባት የነጻነት ዓመታት ውስጥ ተስፋ ሰጪ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማሳየት ችላ ነበር።

ሆኖም ከኢትዮጵያ ጋር በተከፈተው የድንበር ጦርነት ምክንያት፣ በሁለቱ አገራት መካከል የነበረው የንግድ ልውውጥ በመቋረጡ እንዲሁም ሁሉም ትኩረት ወደ ጦርነቱ በመሆኑ ኤርትራን በእጅጉ ተጎድታለች።

በወቅቱ በኤርትራ የነበሩ ፋብሪካዎች ዋና ገበያቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ ስለነበር የውጪ ንግድ ተስተጓጎለ፤ ፋብሪካዎችም ማምረት አቆሙ።

ጦርነቱን ተከትሎ የሁለቱ አገራት ድንበር ከመዘጋቱ ባሻገር፣ በርካታ አምራች የሰው ኃይል በብሔራዊ ውትድርና ውስጥ ተሳታፊ በመሆኑ በአገሪቷ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናን አስከትሏል።

እድሜያቸው ከ18 እስከ 40 ዓመት የሆኑ፣ የንግድ ባለቤቶች ጭምር፣ ገደብ በሌለው ብሔራዊ ውትድርና ውስጥ እንዲሳተፉ በመገደዳቸው የተለያዩ ሥራዎችና የንግድ እንቅስቃሴዎች ለመዘጋት መገደዳቸው ይንገራል።

በተጨማሪም የኤርትራን ፖለቲካ በበላይነት የሚመራው ገዢው ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ (ህግዴፍ) የአገሪቱን ኢኮኖሚ በመቆጣጠሩ እና የባለሃብቶች ተሳትፎ በመጣበቡ አብዛኛዎቹ ከአገር ለመውጣት ተገደዋል።

በርካታ ኤርትራውያን ሥራ ፈጣሪዎች አገሪቱን ለቀው ወደ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ አንጎላ እና ደቡብ አፍሪካ ተሰደዋል።

ከዚህም በላይ በአገሪቱ ባለው እንቅስቃሴ መጠን የመሠረተ ልማት ባለመስፋፋቱ ብዙ የመንግሥትና የግል ተቋማት የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማጣታቸው ምክንያት ለከፍተኛ ኪሳራ መጋለጣቸውን እራሳቸው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ገልፀው ነበር።

ይህም በሌሎች የአገሪቱ የኢኮኖሚ ክፍሎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

ኤርትራ 31ኛ ዓመት የነጻነት ክብረ በዓል እያከበረች ትገኛለች።

በኤርትራ ከሚገኙት ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነውና ለረጅም ዓመታት የተቋረጠው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለኢኮኖሚው መዳከም መንስኤ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ መሆኑ ይነገራል።

የኑሮ መጎሳቆል

በጦርነት የተዳከመው የኤርትራ ኢኮኖሚ ላይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና ድርቅ ተጨምረውበት የአገሪቱን ዜጎች ኑሮ እንዳይሻሻል አድርጓል።

“ራስን መቻል” የሚለው መርህ እንደሚከተል የሚገልፀው የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግሥት፣ የውጭ አገራት ሰብዓዊ እርዳታ ወደ አገሪቱ እንዳይገባ ከልክሏል።

ከ2001 እስከ 2006 ባሉት ዓመታት ብቻ በርካታ የውጭ አገር የልማት ድርጅቶችና የእርዳታ ድርጅቶች ከኤርትራ ተባርረዋል።

እ.ኤ.አ. በ2005 የልማት እና የሰብዓዊ እርዳታዎችን የሚሰጠው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) በአገሪቱ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም ተደረጓል።

በመጋቢት ወር 2006 ‘መርሲ ኮርፕስ’፣ ኮንሰርን እና አኮርድ የተባሉ የእርዳታ ተቋማት የተሰጣቸውን የስራ ፍቃድ ተሰርዞ ከአገር ወጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዜጎች ከውጪ በሚላክ ገንዘብ የሚደገፍ ሆኗል። ይኹን እንጂ የውጪ ምንዛሪ ገበያው ገዢው ፓርቲ እና መንግሥት የሚቆጣጠሩት በመሆኑ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

በመሰረተ ልማት አኳያ ባለፉት 31 ዓመታት የትምህርትና የጤና ተደራሽነት ተስፋፍቷል ቢባልም እንደ ጤና እና ትምህርት ያሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ማሽቆልቆላቸው ይገለጻል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥት በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስር የሚተዳደሩ የጤና ተቋማትን መዝጋቱ እና መወረሱን ተከትሎ ቀውሱን አባብሶታል። የቤተክርስቲያኒቷ ትምህርት ቤቶች ጭምር በመንግሥት ተወስደዋል።

በሌላ በኩል በከተሞች ያለው ኢ-መደበኛ የመብራት እና የውሃ አገልግሎት ዜጎችን ለዓመታት ሲያንገላታ ቢቆይም የጤና ተቋማት የችግሩ ሰለባ ሆነዋል።

ኮሮናቫይረስ

ባለፉት ሁለት ዓመታት በዓለማችን የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ 15 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብን በመግደል ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።

የተለያዩ የዓለም አገራት ዜጎቻቸውን ከዚህ ወረርሽኝ ለመከላከል እና ዳግም ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ተደራሽ አድርገዋል።

ኤርትራ ግን በአፍሪካ ብቸኛዋ ዜጎቿን መከተብ ያልጀመረት አገር ናት።

ይህ በተለይ በንግድ እና በተለያየ ምክንያት ከአገሪቱ በሚወጡ ሰዎች ላይ ከባድ ጫና በማሳደሩ በርካታ ኤርትራውያን ወደ ጎረቤት አገራት በመሄድ የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ይሞክራሉ።

የሩሲያው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርግዬ ላቭሮቭ እና የኤርትራው አቻቸው

ዓለም አቀፍ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች

ኤርትራ በፈቃዷ እንዲሁም በአስገዳጅ ሁኔታዎች ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነቶች ተገልላ ቆይታለች።

ሩሲያ ዩክሬይንን መውረሯን ተከትሎ ያንጸባረቀችው አቋምም አነጋጋሪ ሆና ነበር።

በመጋቢት ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክርቤት ሩስያ ዩክሬይን ላይ የፈጸመችውን ወረራ በማውገዝ የተላለፈው ውሳኔን በመቃወም ከሩሲያ ጎን የቆመች ብቸኛ አፍሪካዊ አገር ሆናለች።

ኤርትራ የምከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመርኅ ላይ የተመሰረተ ነው ብትልም፣ ብዙ የቀድሞ ዲፕሎማቶች እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኞች ግን ተለዋዋጭ እና ስልታዊ ነው ይላሉ። ለዚህም በመካከለኛው ምሥራቅ ያሳየችውን የግንኙነቶች መቀያየር በአብነት ያነሳሉ።

ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ ለሚከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት ሆናለች የሚል ተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብባት ቆይቷል።

ሆኖም የተለያዩ አገራት የሚያጋጥማቸውን የውስጥ ችግር ለመፍታት ጥረት ስታደርግ እና ተነሳሽነት ስትወስድ ይታያል። ከ15 ዓመታት በፊት የተለያዩ የሶማሊያ ኃይሎችን ወደ አንድ ለማምጣት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

በሌላ በኩል ኤርትራ ኢትዮጵያ በምትገነባው የህዳሴ ግድብ ምክንያት በግብፅ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታትም ጥረት ማድረጓ ይገለጻል።

በቅርቡ ደግሞ እስከ አሁን መቋጫ ያላገኘውን የሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታት የሚያስችል አዲስ ተነሳሽነት መውሰዷን አሳውቃለች።

ተንታኞች ግን በአገሩ ውስጥ የፖለቲካ ብዙሃነት ያልፈቀደ እና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን የማይከተለው የኤርትራ መንግሥት ሱዳን ወደ ዲሞክራሲ በምታደርገው ሽግግር ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ሚና ውስን ነው ይላሉ።

ሰብዓዊ መብቶች እና የፖለቲካ ልማት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኤርትራ መንግሥት በከባድ የመብት ጥሰቶች ይከስሱታል።

ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ግለሰቦች ከሕግ ውጪ በፀጥታ አካላት ታስረዋል፣ ተሰውረዋል፣ ተገድለዋል።

መንግሥት አብዛኛዎቹ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን በማገድ፣ መሪዎቻቸውን ያለ ፍርድ አስሯል፣ በርካታ አማኞችም ለስደት ተዳርገዋል በሚል ይከሰሳል።

የኤርትራ መንግሥት ግን እርምጃው የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነትን ለመጠበቅ ነው ሲሉ የወሰደው እርምጃ እንደሆነ ይከራከራል።

ባለፈው ዓመት በኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ራፖርተር በኤርትራ ያለውን ሁኔታ ሲገልጽ “ኤርትራ እስከ አሁን በዴሞክራሲያዊ አግባብ ሰብአዊ መብቶች የሚጠብቁ ሕጎች እና ተቋማት የላትም” ብሏል።

ሕገ መንግሥት፣ ገለልተኛ የዳኝነት ሥርዓትና ሕግ አውጪ አካል አለመኖሩ በኤርትራ የሕግ የበላይነት ላለመኖሩ ማሳያ ነው ሲሉ ልዩ ራፖርተር መሐመድ ዓብደልሳላም ባቢከር ተናግሯል።

የ76 ዓመቱ ፕሬዝደንት ኢሳይያስ “ሳይታወጅ የሞተ ነው” ያሉት እና በ1997 የተነደፈው ሕገ መንግሥትን የሚተካ አዲስ ሕገ መንግሥት እንደሚጻፍ ከዓመታት በፊት ተናግረው ነበር።

ሆኖም እስከ አሁን ሕገ መንግሥት አልተጻፈም፤ የማርቀቅ ሂደቱም አልተጀመረም።