12 June 2022

አማኑኤል ይልቃል

በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚቀጥለው በጀት ዓመት አንስቶ የሚያቀርቧቸው አዳዲስ የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚጸድቁላቸው፣ ትምህርት ሚኒስቴር ከሰጣቸው የልህቀት ማዕከልነት ልየታ ጋር ከተስማማ ብቻ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ ዩኒቨርሲቲዎችን የምርምር ዩኒቨርሲቲ፣ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲና አጠቃላይ (ኮንፕሬሲቭ) ዩኒቨርሲቲ በሚል በሦስት የልህቀት ማዕከልነት መድቧቸዋል፡፡ በዚህም መነሻነት ሁሉም ዩኒቨርሰቲዎች ለልህቀት ማእከልነት የተቀመጠውን ስታንዳርድ ለማሟላት የሚቀራቸውን መሰረተ ልማት ለመለየት፣ የመሰረት ልማት ልየታ ለማካሄድ ቡድን መዋቀሩን በሚኒስቴሩ የአስተዳደርና መሠረተ ልማት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ብዛት የላቸው የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚገኙባቸው ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን በቅርቡ ባደረገው ጥናት በ41 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የዋጋ መስተካከያ የሚጠይቁና ያልተጠናቀቁ 450 ገደማ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡ ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች የተጓተቱ በመሆናቸውም በየጊዜው ለሚከሰት የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ ንረት በመጋለጥ፣ ከተያዘላቸው በጀት በላይ ወጪ ያስወጣሉ፡፡

በቀጣዩ በጀት ዓመት ዩኒቨርሲቲዎች በተደረገላቸው የበጀት ምደባ በእጃቸው ላይ ያለ የግንባታ ፕሮጀክትን ማጠናቀቅ ትኩረት እንደተሰጠው ያስረዱት ሰለሞን (ዶ/ር) ከዚህ ወዲህ ግን ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ትኩረትና ተልዕኮ ጋር ካልተጣጣመ የሚያቀርቡት አዲስ ፕሮጀክት እንደማይጸድቅ ገልጸዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው እንደሚያስረዱት ለዩኒቨርሲቲዎች በተሰጠው ልየታ አሥር ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር፣ 15 የዩኒቨርሲቲዎች የአፕላይድ ሳይንስ ተብለው ሲለዩ፣ የተቀሩት ደግሞ አጠቃላይ ተብለዋል፡፡

በሳምንቱ መጀመሪያ በተደረገው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ግምገማ ይኼ ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ ስለ አገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ገለፃ የሰጡት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ ከልየታ የሚሄድ ፕሮጀክት የማፅደቅ ጉዳይን አንስተው፣ ‹‹የጤና ኤክሰለንስ ሴንተር ይሆናል ያልተባለ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ [ሆስፒታል] ግንባታ ጥያቄ ያመጣል›› ካሉ በኋላ፣ በቀጣይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚገነቡ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ከልየታው ጋር የሚሄዱ መሆናቸው እንደሚረጋገጥ አስረድተዋል፡፡

ሰለሞን (ዶ/ር) እንደሚገልጹት ከአሁን በኋላ የሚመጡ አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት ያላቸውን መሠረት ልማት ኦዲት ለማድረግ ታቅዷል፡፡ በዚህ ኦዲት ዩኒቨርሲቲዎች ምን መሠረተ ልማትና ሀብት እንዳላቸው በልየታቸው መሠረትስ ምን እንደሚጎላቸው እንደሚለይ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሚኒስቴሩ የዩኒቨርሲቲዎች መሠረተ ልማት ስታንዳርድ ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ስታንዳርዱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገነቧቸው መኖሪያ ቤቶች፣ የተማሪች መኖሪያዎች፣ መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጽሐፍትና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ማሟላት የሚጠበቅባቸውን አነስተኛ ስታንዳርድ እንዳስቀመጠ ሰለሞን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ስታንዳርዱ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮጀክቶቻቸውን ሲገነቡ ለየትኛው ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው እንደሚጠቁምም አክለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች መሠረት ልማት ኦዲት ሲደረግ ያላቸው መሰረተ ልማት ከዚህ ስታንዳርድ አንጻር እንደሚታይም ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት የተገነቡት ሕንጻዎች የመጨረሻውን ስታንዳር ካላሟሉ ስታንዳርዱን የሚያሳካ እድሳት ለማድረግ መታሰቡን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ለምሳሌ አንድ የመማሪያ ክፍል አምስት ሜትር በአምስት ሜትር ይሁን ተብሎ የተሰራው ክፍል ግን ‹‹ሁለት በሦስት›› ከሆነ ሁለት ክፍሎች ተቀላውለው  በስታንዳርዱ ይታደሳል፤›› ብለዋል፡፡