ለላብራቶሪ ናሙና የሚሰጥ ሽንት የያዘ እጅ

ከ 6 ሰአት በፊት

ለበርካቶች ፕሮስቴት ሲባል ሁለቱ የወንድ ልጅ የዘር ፍሬዎች አካባቢ ወይም የዘር ፍሬ ከረጢቱ ውስጥ ያለ አካል እንደሆነ ነው የሚያስቡት።

የኩላሊት፣ የፕሮስቴት፣ የሽንት ፊኛ እና ቧንቧ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ፍፁም ሠለሞን ግን ፕሮስቴት ከሽንት ፊኛ በታች ያለ አካል ነው ይላሉ።

እንደ ዶ/ሩ ገለጻ ከሆነ ፕሮስቴት በወንድ ልጅ ብልት እና ፊኛ መካከል የሚገኝ እጢ ነው።

ፕሮስቴት የዘር ፈሳሽ የማመንጨት ጥቅም አለው። የወንድ ልጅ የዘር ፈሳሽ ወደ ውጪ ሲፈስ ሰባ በመቶ ያህሉን የሚያመነጨው ፕሮስቴት መሆኑን ዶ/ር ፍፁም ያብራራሉ።

የወንድ ልጅ የዘር ፈሳሽ ሀዋስ የሚዋኘው እንዲሁም ምግቡን የሚያገኘው ከዚህ ፈሳሽ መሆኑን አክለው ይጠቅሳሉ።

ታድያ የፕሮስቴት ችግር ያለበት ወንድ የዘር ፈሳሹ ወደ ውጪ መፍሰሱን ትቶ የሚመለሰው ወደ ፊኛው ነው።

ስለዚህ ይላሉ ዶ/ር ፍፁም ፕሮስቴት፣ የዘር ፈሳሹ ወደ ፊኛ እንዳይመለስ እና ወደ ውጪ እንዲወጣ ይረዳል።

ፕሮስቴት ልክ እንደ ምራቅ አመንጪ እና ታይሮይድ እጢዎች ሁሉ እጢ (ግላንድ) ነው።

የፕሮስቴት እጢ የሚገኘው ወንድ ላይ ብቻ ነው።

ፕሮስቴት በምስሉ ላይ በቀይ እንደሚታየው  ከሽንት ፊኛ በታች ያለ አካል ነው
የምስሉ መግለጫ,ፕሮስቴት በምስሉ ላይ በቀይ እንደሚታየው ከሽንት ፊኛ በታች ያለ አካል ነው

ፕሮስቴት ካንሰር

እንደ ዶ/ር ፍፁም ገለጻ በየትኛውም የሰውነታችን ክልፍ ላይ ካንሰር ሊከሰት ይችላል፣ ስለዚህም ፕሮስቴትም ለካንሰር  ይጋለጣል።

በዓለም ላይ ከስምንት ወንዶች መካከል አንዱ በሕይወት ዘመኑ በፕሮስቴት ካንሰር ይያዛል።

ፕሮስቴት አጥቢ እንስሳት ላይ በሙሉ የሚገኝ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስም ካንሰሩ ከሰው ውጪ የታየው ውሾች ላይ ብቻ ነው።

80 በመቶ ያህሉ ፕሮስቴት ካንሰር ቀስ ብሎ የሚያድግ እንዲሁም ህመም ሳያስከትል ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ነው።

በብዛት የፕሮስቴት ካንሰር በመጀመሪያ ከፕሮስቴት እጢ ላይ ተወስኖ ይቆይና ከባድ ጉዳት በማያስከትል መልኩ ቀስ እያለ የሚያድግ ችግር ነው።

ማን የበለጠ ተጋላጭ ነው?

ለፕሮስቴት ካንሰር አጋላጭ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል አንዱ እድሜ ነው።

እድሜያቸው ከ50 በላይ የሆኑ፣ ጥቁር ወንዶች እንዲሁም በቤተሰባቸው ውስጥ የፕሮስቴት ካንሰር የተያዘ ሰው የሚገኝ ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።

የዩናይትድ ኪንግደም ተመራማሪዎችም እድሜያቸው 40 የሞላቸው ወንዶች በየዓመቱ ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመክራሉ።

ዶ/ር ፍፁም በበኩላቸው ፕሮስቴት ካንሰር ከ40 ዓመት በታች በሆኑ ሰዎች ላይ የመገኘት እድሉ እጅጉን በጣም አነስተኛ መሆኑን ይናገራሉ።

እድሜያቸው ከ20 እስከ 30 የሆነ ወንዶች በፕሮስቴት የመያዝ እድላቸው አንድ በመቶ ብቻ ነው።

ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የፕሮስቴት ካንሰር የሚከሰተው እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ በሆናቸው ወንዶች ላይ ነው ይላሉ ዶ/ር ፍፁም።

አፍሪካውያን ከነጮች አንጻር ሲታይ በዚህ ካንሰር የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ተመሳሳይ የቤተሰብ ታሪክ ያላቸው ግለሰቦች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

ወንድም፣ አባት፣ አያት እንዲሁም አጎቱ በፕሮስቴት ካንሰር የተያዘበት ግለሰብ የተጋላጭነት ዕድሉ ሰፊ ነው።

ከቅርብ ቤተሰብ መካከልም አባቱ በዚህ ካንሰር የተያዘ እና አያቱ የተያዘ ወንድ እኩል የተጋላጭነት ልክ እንደሌላቸው ዶ/ር ፍፁም ያብራራሉ።

አባቱ ወይንም ወንድሙ በፕሮስቴት ካንሰር የተያዘ ወንድ፣ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከሁለት እና ሦስት እጥፍ በላይ ተጋላጭ ነው።

ሌላኛው መታየት ያለበት በቤተሰብ ውስጥ ካንሰር የተያዘው ሰው በስንተኛው ዕድሜው ላይ ተገኘበት የሚለው ወሳኝ ነጥብ መሆኑን ዶ/ር ፍፁም ያብራራሉ።

ይህንንም ሲያብራሩ ከ65 ዓመት በታች የፕሮስቴት ካንሰር የተገኘበት አባት፣ ልጁ ለካንሰሩ የመጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህም ማለት ልጁ እስከ 5 እጥፍ ድረስ የተጋለጠ ነው።

ሌላኛው ደግሞ ይላሉ ዶ/ር ፍፁም፣ አባቱ እና አያቱ በፕሮስቴት የተጠቁ እና አባቱ ብቻ የተያዘ ልጅን ብናወዳድር፣ ይህ ሁለቱም የቤተሰብ አባላት የተያዙበት ግለሰብ የበለጠ ተጋላጭ ነው ይላሉ። 

የዘረመል እክል (ጄኔቲክ ሚውቴሽን) ላይ እክል ካለ የበለጠ ለዚህ ካንሰር ያጋልጣል።

ካንሰር በአብዛኛው ሲታይ ህዋሱ በተነሳበት አካል ወይንም ስፍራ ከመጠን በላይ ይራባል።

ከዚያም በመቀጠል ባለበት አካል ላይ ብቻ ተገድቦ ሳይቀመጥ ወደ ሌላ የአካል ክፍል ይሰራጫል።

ፕሮስቴት ካንሰር ተገቢውን ሕክምና በተገቢው ሰዓት ካላገኘ የሽንት ፊኛን ሊያፍን ያችላል።

የፕሮስቴት እጢ ከተራባ በኋላ ፕሮስቴት አጠገብ ያሉ የሽንት ቧንቧ እና ፊኛ ላይ ይዛመታል።

ከዚያም አልፎ በደም ስር ተሰራጭቶ ወደ ጀርባ ይሄዳል።

ፕሮስቴት ካንሰር ብዙ ጊዜ በደም ስር አድርጎ ወደ ጀርባ፣ አከርካሪ አጥንት እና ሆድ ውስጥ ወዳሉ ንፍፊቶች ይሰራጫል።

የደም ናሙና የያዙ ብልቃጦች

ለመከላከል ምን ማድረግ ይቻላል?

የፕሮስቴት ካንሰርን ለመከላከል አመጋገብን ማስተካከል ዋነኛው መፍትሄ ነው። አትክልት እና ፍራፍሬ የበዛበት፣ ዓሳ፣ የዓሳ ዘይት፣ ኦሊቭ ኦይል ያለው ምግብ መመገብ ለመከላከል ይረዳል።

ከእነዚህ በተጨማሪ አረንጓዴ ሻይ እነዲሁም ቫይታሚን ዲ መጠቀም የመከላከል አቅምን ያጎለብታል።

የፕሮስቴት ካንሰር ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ቅድመ መከላከል

የፕሮስቴት ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ቀስ ብሎ የሚያድግ በመሆኑ፣ ከጀመረበት አንስቶ ለመሰራጨት እና ሕይወትን አደጋ ላይ ለመጣል ረዥም ጊዜ ይወስድበታል።

ስለዚህም ቢያንስ በዓመት ወይንም በሁለት ዓመት አንዴ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ጠቃሚ ነው።

በተለይ ለካንሰሩ የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ የቤተሰብ ታሪክ ያላቸው፤ ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራሉ።

ቅድመ ምርመራ ለመጀመር የተለያዩ አገራት፣ የተለያዩ መመርያዎች እንዳላቸው የሚናገሩት ዶ/ር ፍፁም፣ አንድ ሰው እድሜው ከ50 አስከ 55 ዓመት ሲሆን ቅድመ ምርመራ እንዲያደርግ ይመከራል።

ተመሳሳይ የቤተሰብ ታሪክ ያለው ግለሰብ ደግሞ እድሜው ከ40 አስከ 45 ላይ እያለ ምርመራውን ቢጀመር መልካም መሆኑን ገልፀዋል።

“ቢያንስ ቢያንስ በየሁለት ዓመቱ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ይመከራል” ሲሉ ያክላሉ።

የፕሮስቴት ካንሰር ሕክምና

ከሁሉ በፊት በቤተሰብ ውስጥ ያለን የፕሮስቴት ካንሰር ታሪክን ማወቅ እንዲሁም ወደ አርባዎቹ የእድሜ ክልል ሲገባም በተወሰ ጊዜው ውስጥ ምርመራ ማድረግ ችግሩ ካለ ስር ሳይሰድ ለማከም ይረዳል።

ምርመራው ተደርጎ የፕሮስቴት ካንሰር መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ የተለያዩ ዓይነት ሕክምናዎች እንዳሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከእነዚህም ውስጥ በቀዶ ሕክምና ካንሰሩን ማውጣት፣ የጨረር ሕክምና ወይንም ደግሞ የወንድ ልጅ ቴስቴስትሮን ካንሰሩን በዋነኛነት ስለሚመግብ በሰውነት ውስጥ ያለውን የቴስቴስትሮን መጠንን ለመቀነስ ሕክምና ይሰጣል።