በሃሚድ አወል
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ዐቃቤ ህግ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት ትዕዛዝ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ፖሊስ በጋዜጠኛ ሰለሞን ሹምዬ እና መዓዛ መሐመድ ላይ ለሚያደርገው ምርመራ ተጨማሪ አምስት ቀናት ፈቅዷል።
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጉዳይ የያዘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራውን አጠናቅቆ ለዐቃቤ ህግ ማስተላለፉን ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 7፤ 2014 ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ አስታውቋል። ከፖሊስ የምርመራ መዝገቡን መረከቡን በጽሁፍ ያረጋገጠው ዐቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ 15 ቀናት እንዲሰጡት ችሎቱን ጠይቋል።
ጋዜጠኛ ተመስገንን ወክለው በችሎት የተገኙት ጠበቃው አቶ ሔኖክ አክሊሉ የዐቃቤ ህግን ጥያቄ ተቃውመው፤ ፍርድ ቤቱ የደንበኛቸውን የዋስትና መብት እንዲያስከብርላቸው ጠይቀዋል። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የጠበቃውን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለዐቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ 15 ቀናትን ፈቅዷል።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጋዜጠኛ ተመስገንን ጉዳይ ዛሬ የተመለከተው፤ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የፈቀደው የ10 ሺህ ብር ዋስትና በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሽሮ መዝገቡ አንዲመለስ በመደረጉ ምክንያት ነው። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስትና ትዕዛዙን የሻረው፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በትዕዛዙ ላይ ያቀረበውን ይግባኝ በመቀበል ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)