የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት
የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት

ፖለቲካ

15 June 2022

አማኑኤል ይልቃል

የጋምቤላ ክልል በክልሉ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎቹ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የክልሉን ዋና ከተማ ለመቆጣጠር የከፈቱትን ጥቃት በመመከት ከተማውን ‹‹ነፃ›› ማድረጉን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፕረስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጌቱ አዲንግ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሁለቱ ታጣቂ ኃይሎች በጋራ በመሆን በጋምቤላ ከተማ ላይ ጥቃት የከፈቱት ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ከማለዳ 12 ሰዓት አንስቶ ነው፡፡

ታጣቂዎቹ ጋምቤላ ከተማን ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ኡጌቱ የክልሉ መንግሥት ታጣቂዎቹ ጥቃት በከተማዋ ለመክፈት ዝግጅት እያደረጉ ስለመሆኑ መረጃ እንደነበረው አስረድተዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት ይሄንን በማስመልከት ሰኞ ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ግምገማ ማድረጉንና የክልሉ መንግሥት በመረጃው ላይ ተመሥርቶ ጥቃቱን ለመመከት ‹‹የተቀናጀ የፀጥታ ኦፕሬሽን››  ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

አክለውም፣ ‹‹ጥቃት ለመፈጸም እንደተዘጋጁ መረጃ ነበረን፡፡ በዚህ መረጃ ነው ወደ ኦፕሬሽን የተገባው፡፡ ዞሮ ዞሮ [ወደ ከተማው] ገብቷል ግን ቢገባም መመለሻ እንደሌለው ነው የነበረን ውይይት፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹ጋምቤላ ከተማን በሙሉ ለመቆጣጠር ሙከራ ቢያደርጉም በተደረገው ትግል ከተማው ነፃ ሆኗል፤›› ያሉት ኃላፊው ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ በደረሰባቸው ጥቃት ‹‹በአንዳንድ ቦታዎች ተደብደቀው ወደ ቤቶች የገቡ፤›› ታጣቂዎች በመኖራቸው የፀጥታ ኃይሉ ‹‹ለቀማ›› ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ‹‹መደምሰሳቸውን›› እና ኪሳራ እንደደረሰባቸው ተናግረው ‹‹የሰው ሕይወት አልፏል ግን ብዙም የደረሰ ጉዳት አልነበረም፤›› ብለዋል፡፡

ኃላፊው በንፁኃን ላይ ስለ ደረሰ ጉዳት ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ጦርነት ባለበት ሁሉ ሰው መሞቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በወታደርም በሲቪሊያን ላይም ችግር ደርሷል፡፡ ቁጥሩን ገና አላጣራንም ስናጣራ እናሳውቃለን፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጋምቤላ ሕዝቦች ፍትሕ ለሰላምና ልማት ዴሞክራቲክ ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ሳይመን ቱት ፓል በበኩላቸው፣ ከሌሊት 11 ሰዓት አንስቶ በሦስት አቅጣጫ የተኩስ ድምፅ መሰማቱን ገልጸዋል፡፡ ጥቃቱ የተከፈተባቸው አካባቢዎችም ወደ ደምቢ ዶሎ ከተማ የሚወስደው መንገድ ያለበት ብሔር ብሔረሰብ የተባለ አካባቢና እንዲሁም ኒው ላንድና ጀርጀቤ ተራራ የሚባሉ አካባቢዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሳይመን እስከ ትናንት ምሽት 11 ሰዓት ድረስም በከተማዋ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበርና ኒው ላንድ በተባለው አካባቢ አንዲት ሕፃን ልጅና አንድ ዕድሜያቸው ከፍ ያለ ሴት ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

ጀብጀቤ ተራራ የተባለው አካባቢ የክልሉ ልዩ ኃይሎች ካምፕ ያለበት መሆኑን የገለጹት አቶ ሳይመን፣ በዚህ አከባቢ ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ጀብጀቤ ተራራ ላይ የነበረው የከፍተኛ ተኩስ የተሰማው የክልሉን የፀጥታ ኃይል ለማገዝ ከኑዌር ዞን የመጡ ኃይሎች ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ከታጣቂዎቹ ጋር ሲገጥም የትኛዎቹ የፀጥታ ኃይሎች እንደተሳተፉ ጥያቄ የቀረበላቸው የፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ኡጌቱ ‹‹የተቀናጀ የፀጥታ ኦፕሬሽን ነው አንድ አካል ብቻ አይደለም፤›› በማለት የፀጥታ ኃይሎቹን ከመዘርዘር ተቆጥበዋል፡፡

አቶ ኡጌቱ፣ ታጣቂዎቹ በክልሉ ከከተማው ውጭ ያሉ ቦታዎች ላይ ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሰው ‹‹የት ቦታ ነው ያሉት የሚለውን ለማወቅ ጥናት እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡