
July 6, 2022
በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ቁጥራቸው እስካሁን በውል ባልታወቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በኦነግ ሸኔ መገደላቸው በይፋ ከተገለጸ በኋላ፣ ዜጎች ለደኅንነታቸው ጠባቂ ማጣታቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
እናት ፓርቲ ማክሰኞ ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ነገሩ በአማራ ላይ የቀጠለው ዘር ፍጅት (Genocide) ቀጣይ ክፍል እንጂ አዲስ ነገር አይደለም፤›› ብሎ፣ ‹‹በግድያው አዲሱ ነገር የመሰለው ቦታና ጊዜ መቀየሩ ብቻ እንጂ ገዳዩም ሟቹም ያው ነው፤›› ብሏል፡፡
ዜጎች በምርጫ ባልተቀበሉት የ‹‹አማራነት›› ማንነት እየተፈጸመባቸው ባለው መዋቅራዊ ጭፍጨፋ እጅግ እንደሚያዝን፣ ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ የሚሄድ ነገር አለመኖሩን በመግለጽ፣ አገሪቱ ወደ መንግሥት አልባነት እየተሸጋገረች መሆኗን ተገንዝቦ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ራሱን እያደራጀ ከጥቃት እንዲከላከል፣ ለከፋም ጊዜ ራሱን እንዲያዘጋጅ እናት ፓርቲ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ማክሰኞ ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በድንገት መጥቶ ሕዝብን ከሚያጠቃው እኩይ አካል መንግሥት እኩል ዜጋውን የመጠበቅ ግዴታ እያለበት፣ የዜጎችን መብት የማይጠብቅ መንግሥት ተጠያቂ መሆን እንዳለበት አስታውቋል፡፡
ኢዜማ በመግለጫው፣ ‹‹የማያባራ ሥቃይ፣ የማይረጋጋ ነፍስ፣ ፅልመት የዋጠው የሰቆቃ ኑሮ፣ የማያሳርፍ ጭንቀት ተሸክመው እጅግ መራር ሕይወትን እንዲገፉ የተፈረደባቸው ወገኖቻችን ዛሬም የሰው አውሬ ያገኛቸው ጠባቂ ስላጡ ነው፤›› በማለት በተፈጠረው ችግር ማዘኑን አስረድቷል፡፡
ኢዜማ መንግሥት ማንነትን መሠረት አድርገው የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማስቆም ተገቢውን ዕርምጃ በመውሰድ፣ ዜጎችን ከአሰቃቂ ጭፍጨፋ የመጠበቅ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ በተደጋጋሚ ቢያሳስብም፣ ‹‹መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማሳሰቢያዎችንም ሆነ ምክረ ሐሳቦቻችንን ለመቀበል ምንም ዓይነት ፍላጎት አላሳየም፤›› ሲል ወቀሳውን ሰንዝሯል፡፡
በመሆኑም የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱም ከዕለት ወደ ዕለት ጥያቄ ውስጥ እየገባ መምጣቱ ኢዜማን በብርቱ እንዳሠጋው፣ የእኩይ ኃይሉ ተባባሪዎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ መሰግሰጋቸውና የዜጎችን ነፍስ ለመታደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በቁርጠኝነት ባለመተግበሩ መንግሥትን ተጠያቂ እንደሚያደርገው አስታውቋል፡፡
መንግሥት በተለይም በወለጋ አካባቢ በዚህ ደረጃ የፀጥታ ችግሮችን ለምን መቆጣጠር እንደተሳነው ለሕዝብ በግልጽ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት፣ ለችግሩ የመፍትሔ የጊዜ ገደብ ወጥቶለት አካባቢውን ከመሰል ጥቃቶች በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንደሚያወጣ በይፋ በመግለጽ፣ ለዜጎች ደኅንነት መጠበቅ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነና የማስፈጸም አቅም እንዳለው ሊያሳይ እንደሚገባም በመግለጫው ገልጿል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ፣ ‹‹የተቀናጀ፣ ተከታታይና ሥልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸምና በማስፈጸም የአማራን ሕዝብ ማሸማቀቅ፣ አንገቱን ማስደፋትና ፖለቲካዊ ድል ማግኝት አይቻልም፤›› ሲል ማክሰኞ ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የዘር ፍጅት ፖለቲካ አራማጁና ሽብርተኛው የኦነግ ሸኔ ሠራዊት፣ ከይፋዊና ከህቡዕ አጋሮቹ ጋር በመተባበር በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል አጠናክሮ ስለመቀጠሉም አክሏል፡፡
በብዙ ምዕራፍ የተከፈለና የተቀናጀ፣ ተከታታይና ሥልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዕቅድ ቀጣይ ክፍል እንደሆነ በገለጸው ጭፍጨፋ፣ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. በቄሌም ወለጋ ዞን በሃዋ ገላን ወረዳ መንደር 20 እና 21 ተብለው በሚታወቁ ልዩ ቦታዎች፣ እስካሁን በታወቀ መረጃ ከ400 በላይ ሕፃናት፣ ሴቶችና ሌሎች ሰላማዊ የአማራ ተወላጆች መጨፍጨፋቸውን በመግለጫው አትቷል፡፡
በመሆኑም የፌዴራሉ መንግሥትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከታታይና በመደበኛ ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው የዘር ፍጅትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጨባጭ፣ ግልጽና ተገማች አደጋ በመሆኑ የችግሩ ምንጭ የሆኑ የሕግ፣ የመዋቅርና የሥርዓት አቀፍ ችግሮች እስኪፈቱ ድረስና ችግሩ ወደ ለየለትና አጠቃላይ የዘር ፍጅት ከመድረሱ በፊት፣ ዘር ማጥፋትና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል ብሔራዊ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ሕግና አሠራር ሥራ ላይ እንዲያውሉ አብን ጠይቋል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ማክሰኞ ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በወለጋ በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በጥብቅ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና ባልደራስ በመግለጫው፣ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ቤተሰብን ለመጠየቅና ለድርጅታዊ ሥራ በሰሜን አሜሪካ ለሁለት ወራት መቆየቱን አስታውሷል፡፡ በውጭ አገር ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ፓርቲው ቢያምንም፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ አቶ እስክንድር አስቸኳይ ለሆኑ ድርጅታዊ ሥራዎች ስለሚፈልጋቸው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡
ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በአማራ ብሔር ተወላጆች በሚኖሩባቸው መንደሮች በተፈጸመው ተመሳሳይ ጥቃት፣ በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውና ሺዎች ደግሞ አካባቢውን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል፡፡