መንግሥት ለኮሚሽኑ 40 ሚሊዮን ብር በጀት ይዟል
የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጣዩ ዓመት ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀውን አገራዊ ምክክር ለሚመራው አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሚደረጉ ድጋፎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ትረስት ፈንድ እንዲያቋቁም ውክልና ሰጠ፡፡
ፕሮግራሙ ለኮሚሽኑ የሚደረጉ ድጋፎችን የማስተባበርና በሚያዘጋጀው የትረስት ፈንድ ቋት የማሰባሰብ ኃላፊነት እንደሚኖረው የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ኮሚሽኑ ለሥራው ማስፈጸሚያ የሚሆን በጀት ከመንግሥት እንደሚመደብለት ያስቀመጠ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ ከሌሎች ሕጋዊ ምንጮችም በጀት ማግኘት እንደሚችል ተደንግጓል፡፡
ኮሚሽኑ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር አመቻችነት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር ምክክር ማድረጉን የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማ ከበደ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ውይይቱ የተካሄደው ገንዘብ ሚኒስቴር ባለው ግንኙነት የልማት አጋሮች ለኮሚሽኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ የማመቻቸት ሥራ ለመሥራት መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ፣ ባለፈው ሳምንት የተካሄደው ቅድመ ውይይት መሆኑንና ሌሎች ውይይቶች እንደሚከተሉ አስረድተዋል፡፡ ብዙ የልማት አጋሮች ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በውይይቱ ላይ መነሳቱን አስታውሰው ነገር ግን ድጋፉ ምን ያህል ይሆናል የሚለው አሁን ላይ የማይወሰን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከተለያዩ አካላት ይመጣል ተብሎ የሚታሰበው ድጋፍን የማስተባበርና በአንድ ትረስት ፈንድ የማሰባሰብ ሥራ ለልማት ፕሮግራሙ ተሰጥቷል፡፡
‹‹የፈንድ ቋት ይቋቋምና የልማት አጋሮች አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ሁሉ አንድ ቋት ውስጥ ያስገባሉ፤›› ያሉት አቶ ግርማ ይህም የሆነው ከተለያዩ አካላት የሚመጣ ድጋፍ በአንድ ተቋም መተዳደር ስላለበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አጋር አካላቱ የሚያስገቡትን ድጋፍ በአንድ ላይ ሆነው እንደሚገመግሙና አፈጻጸሙን እንደሚመለከቱም አክለዋል፡፡
ከአጋር አካላቱ የሚደረገው ድጋፍ የገንዘብ ብቻ ላይሆን እንደሚችል ያነሱት ዳይሬክተሩ ‹‹የቴክኒካል፣ የሥልጠና የልምድ ልውውጥ ድጋፍም ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ አሁን የተደረገው ውይይት ግን ድጋፍ ለማድረግ ውይይት መጀመሩን እንጂ ድጋፍ ማድረግን እንደማያረጋግጥ ተናግረዋል፡፡
የአገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያም (ፕሮፌሰር) ይህንን ሐሳብ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ወደፊት የሚያስቡት ነገር ነው እንጂ እስካሁን እንዲህ እናደርጋለን የተባለ ነገር የለም፤›› ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ አጋር አካላቱ ድጋፉን የሚደርጉት የኮሚሽኑን በቀጣይ ሥራዎች እያዩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአጋር አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ በቀጣይ የሚታይ ቢሆንም ኮሚሽኑ በዋነኛነት በጀቱን የሚጠብቀው ከመንግሥት መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጀት ዝርዝር እንደሚያሳየው ኮሚሽኑ ለ2015 በጀት ዓመት 40 ሚሊዮን ብር ተመደቦለታል፡፡
ኮሚሽኑ ሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በተገኙበት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ ኮሚሽኑ ያከናወናቸውን ሥራዎች ያቀረቡት ዋና ኮሚሽነሩ መስፍን (ፕሮፌሰር) በተለያዩ ዘርፎች የተከፈሉ ሥራዎች እንዳሉ ገልጸው የመጀመርያው አጋርነትና ሀብት ማሰባሰብ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የሚድያና ኮሙዩኒኬሽንን የሚከታተል፣ የምክክር ሒደት የተመለከተ፣ ዋነኛው ምክክርንና ትግበራውን የሚከታተል እንዲሁም የሚያስፈልጉ ድንጋጌዎች የሚያወጡ ዘርፎች እንደተዋቀሩ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ ዋና ኮሚሽነሩ በምርጫ ቦርድ ከተመዘገቡ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከ40 ያህሉ ጋር አብሮ ለመሥራት መነጋገሩን አስታውቋል፡፡ ከቀሪዎቹ 13 ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር ደግሞ የተናጠልና የጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡