ሞ ፋራህ

12 ሀምሌ 2022, 09:22 EAT

በዓለም ስመ ጥር ከሚባሉት አትሌቶች አንዱ የሆነው ሰር ሞ ፋራህ በህፃንነቱ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዲመጣ መደረጉን እና ለአስገዳጅ የህፃናት የጉልበት ብዝበዛ መጋለጡን ይፋ አደረገ።

በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከፍተኛ የማዕረግ ስም የሆነውን ‘ሰር’ የሚለውን መለያ ያገኘው ሞ ፋራህ ስሙም በወላጆቹ የተሰጠው ሳይሆን ሐሰተኛ ነው ብሏል።

ሞ ፋራህ የተሰኘው ስምም ከጂቡቲ በወሰዱት አዘዋዋሪዎች እንደተሰጠው ለቢቢሲ ተናግሯል። የሞ ፋራህ ትክክለኛ ስም ሁሴን አብዲ ካህን ነው።

በዘጠኝ ዓመቱ በማያውቃት ሴት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የተወሰደው ሞ ፋራህ፣ እንግሊዝም ከደረሰ በኋላ የሌላ ቤተሰብ ልጆችን እንዲጠብቅና እንዲንከባከብም ተገዷል።

“ለዓመታት ያህል ስለዚህ ጉዳይ ማሰብ አልፈለግኩም” ያለው ሞ ፋራህ “ሃሳቡን ከጭንቅላቱ ማስወገድ የሚቻለው ለተወሰነ ጊዜ ነው” ብሏል ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ።

የኦሊምፒክ አሸናፊውና የረጅም ርቀት ሯጩ ሞ ከዚህ ቀደም ስለ ህይወት ታሪኩ ሲናገር ከወላጆቹ ጋር በስደተኝነት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንደመጣ ገልጾ ነበር።

ነገር ግን በቢቢሲ እና ሬድ ቡል ስቱዲዮ ተዘጋጅቶ በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ለዕይታ በሚበቃው ዘጋቢ ፊልም ወላጆቹ የዩናይትድ ኪንግደምን ምድር አልረገጡም። እናቱ እና ሁለት ወንድሞቹ ሶማሊላንድ ውስጥ በግብርና ሥር የሚተዳደሩት መሆባቸውን ተናግሯል።

አባቱ አብዲ በሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት በተባራሪ ጥይት የተገደለ ሲሆን፣ ሞም በወቅቱ የአራት ዓመት ልጅ ነበር።

አገሩ ሶማሊላንድ በአውሮፓውያኑ 1991 ከሶማሊያ ተገንጥያለሁ በማለት እንደ አገር ብትመሰረትም እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገርነት እውቅና አልተሰጣትም።

ሞ ፋራህ መጀመሪያ ጂቡቲ ካሉ ዘመዶቻቸው ጋር እንዲኖር ነበር ከቤተሰቡ የተለከየው፤ በዚያን ወቅትም የስምንት ወይም የዘጠኝ ዓመት ልጅ እንደነበረ ያስታውሳል። ከጂቡቲም እሱ በማያውቃት እና ከቤተሰቡም ጋር ዝምድና በሌላት ሴት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተወሰደ።

ግለሰቧ ከዘመዶቹ ጋር እንዲኖር ወደ አውሮፓ እየወሰደችው መሆኑን የነገረችው ሞ ፋራህ ሁኔታው “በጣም አስደስቶኝ ነበር” ይላል።

የህፃንነት ልቡም የፈነጠዘው በአውሮፕላን በመሳፈሩ ነበር “ከዚህ በፊት በአውሮፕላን ተሳፍሬ አላውቅም ነበር” በማለት ያስታውሳል።

ሴትየዋም ስሙን ከተጠየቀ መሐመድ ነው እንዲል አጥብቃ አሳሳበችው። ሞሐመድ ፋራህ በሚል ስምም የእሱን ፎቶ የያዘ ሐሰተኛ የጉዞ ሰንድ እንደነበራት ተናግሯል። 

ሃሰተኛው የጉዞ ሰነድ

ቃል የተገባለት ዩናይትድ ኪንግደም እንደደረሱ፣ ሴትየዋ በምዕራብ ለንደን ሃውንስሎው ወደሚገኘው አፓርታማዋ ወሰደችው። በመቀጠልም የዘመዶቹን አድራሻ የያዘውን ወረቀት ወሰደችበት።

“ዐይኔ እያየ አድራሻውን የያዘውን ወረቀት ቀድዳ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ከተተችው። በዚያን ወቅት ነበር ችግር ውስጥ እንደገባሁ ያወቅኩት” በማለት ያስታውሳል።

ሞ በጨቅላነት እድሜው ምግብ ማግኘት ከፈለገ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም የሚያገኘው፤ የቤቱን ሥራ ማጠናቀቅ እንዲሁም የግለሰቧን ልጆች መንከባከብ ነበረበት።

ይባስ ብሎም ሴትየዋ ታስፈራራው ነበር “ቤተሰብህን እንደገና ማየት የምትፈልግ ከሆነ ለማንም ምንም መተንፈስ የለብህም” ትለው ነበር።

የጭንቅ ቀኑንም ሲያስታውስ “ብዙውን ጊዜ ራሴን መታጠቢያ ቤት ውስጥ ቆልፌ አለቅሳለሁ” ይላል።

በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት የቤተሰቡን የቤት ሥራ ብቻ እንዲያከናውን እንጂ ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄድ አልፈቀዱለትም። ነገር ግን 12 ዓመት ገደማ ሲሆነው ፌልታ ኮሚዩኒቲ ኮሌጅ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ እንዲመዘገብ ተደረገ።

ለትምህርት ቤቱ ሠራተኞችም ሞ ከሶማሊያ የመጣ ስደተኛ መሆኑ ተነገራቸው።

የቀድሞ መምህሩና አስጠኚው ሳራ ሬኒ ሞ ትምህርት ቤት በሚመጣበት ወቅት “ዝርክርክ” ብሎ ሲሆን ተንከባካቢ እንደሌለው ያስታውቅ ነበር ይላሉ። እንግሊዝኛም የሚናገረው ትንሽ ትንሽ ሲሆን “ከአካባቢው ባህልም ሆነ ከስሜት የተነጠለ ልጅ” ነበር በማለትም የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታ ያስረዳሉ።

ወላጆቹ ነን ብለው ትምህርት ቤት ያስገቡት ግለሰቦችም ምንም አይነት የወላጆች ቀን ላይ ተገኝተው እንደማያውቁም ለቢቢሲ አስረድታለች።

ሌላኛው የሰር ሞ አካላዊ እንቅስቃሴ (ስፖርት) መምህር አለን ዋትኪንሰን ታዳጊው ሞ የሩጫው ሜዳ ላይ ሲወጣ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚለወጥ ማስተዋል ጀመሩ።

“የተረዳው የሚመስለው አካላዊ እንቅስቃሴ ወይም የስፖርት ቋንቋ ብቻ ነበር” ይላሉ።

ስፖርት የሕይወት መስመር ማስቀጠያዬ ነበር የሚለው ሞ “ከነበርኩበት የሕይወት ፈተና ለመዳን ማድረግ የምችለው ብቸኛ ነገር ቢኖር መውጣትና መሮጥ ነበር” በማለት የነበረውን ያስታውሳል።

በመጨረሻም ለስፖርት መምህሩ ዋትኪንሰን ስለእውነተኛ ማንነቱ፣ ስለታሪኩ እና ስለተጋለጠበት ጉልበት ብዝበዛ አስረዳቸው።

‘እውነተኛው ሞ’

ታሪኩን ከሰሙ በኋላ የስፖርት መምህሩ ማኅበራዊ አገልግሎት ለሚሰጠው መሥሪያ ቤት አስታወቁ። ከነበረበት ቤተሰብም እንዲወጣ ተደርጎ ለሌላ የሶማሌ ቤተሰብ በማደጎ እንዲሰጥ በማድረግ ረዱት።

“እውነተኛ ቤተሰቦቼ ይናፍቁኝ ነበር፤ ነገር ግን ወደ እነዚህ ሶማሌ ቤተሰብ ከመጣሁ በኋላ ሁሉም ነገር ተሻሽሏል” ይላል ሰር ሞ።

“ለዓመታት የተሸከምኩት ሸክም ከጀርባዬ ላይ የተነሳ ያህል ተሰማኝ። እኔነትም ይሰማኝ ጀመር። ያኔ ነው ሞ የወጣው- እውነተኛው ሞ” ብሏል።

ሰር ሞ ፋራህ በአትሌትነት ስሙ መጠራት የጀመረው ገና በ14 ዓመቱ ነበር። በላትቪያ የሩጫ ውድድር የዩናይትድ ኪንግደም ትምህርት ቤቶችን ወክሎ እንዲወዳደር ተጋብዞ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ ምንም አይነት የጉዞ ሰነድ አልነበረውም።

ሞ በአውሮፓውያኑ 2012 ለንደን የነበረውን ኦሎምፒክ ውድድር አሸንፎ ደስታውን ሲገልጽ

አለን ዋትኪንሰን ሞሐመድ ፋራህ የዩናይትድ ኪንግደም ዜግነት ለማግኘት እንዲያመለክት ረድቶታል። በአውሮፓውያኑ 2000 ሞ ፋራህ የእንግሊዝ ዜግነቱን አገኘ።

በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ጠበቃ አለን ብሪዶክ ለሰር ሞ ዜግነቱን ቴክኒካል በሆነ መንገድ ሲመለከቱት “በማጭበርበር ወይም በተሳሳተ መረጃ የተገኘ” እንደሆነ ሲነግሩት ይሰማል።

በዩናይትድ ኪንግደም ሕግ መሠረት አንድ ሰው ዜግነቱ በማጭበርበር የተገኘ ከሆነ ሊገፈፍ ይችላል።

ሆኖም አለን ብሪዶክ እንደሚያስረዱት በሞ ጉዳይ ይሄ ስጋት እንደሌለ ያብራራሉ።

“የሕገወጥ ዝውውር ትርጉም ለጉልበት ብዝበዛ ዓላማ ማጓጓዝ” ነው ሲሉ ለሰር ሞ አለን ብሪዶክ ሲነግሩት ይደመጣል።

“የአንተን ሁኔታ ስንመለከተው አንተ ራስህ ታዳጊ ልጅ ሆነህ ትንንሽ ልጆችን እንድትጠብቅ እና የቤት አገልጋይ እንድትሆን ተገደሃል። ከዚያም ለሚመለከተው አካል ‘ይህ ስሜ አይደለም ብለህ ተናግረሃል። እነዚህ ሁሉ ተደምራረው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜግነትህን የመውሰዱ ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሱታል” ብለዋል።

ሩጫ አዳነኝ

ሞ ታሪኩን መንገር የፈለገበት ምክንያት ስለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ባርነት ያለውን አመለካከት ለመገደዳደር እንደሆነ ተናግሯል።

“እኔ ባለፍኩበት መንገድ ተመሳሳይ ሁኔታ እያጋጠማቸው ያሉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ አላውቅም ነበር። አሁን የደረስኩበትን ደረጃ ሳየው ምን ያህል እድለኛ እንደሆንኩ ተረዳሁ” ብሏል ሞ።

“በእውነቱ ከዚህ ሁሉ መከራ ያዳነኝ፤ መሮጥ መቻሌ ነው” በማለት አጠቃልሏል።

ሰር ሞን ወደ ለንደን በሕገወጥ መንገድ ያመጣችው ግለሰብ አስተያየቷን እንድትሰጥ ቢቢሲ ቢጠይቃትም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች።