

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሲሠራበት የነበረውን የሥነ ሥርዓት ድንጋጌ የሚተካ፣ ዳኞች ሰዓት አክብረው እንዲሰየሙና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት አርፍደው ከተሰየሙ ባለጉዳዮችን ይቅርታ እንዲጠይቁ የሚያስገድድ ደንብ ፀደቀ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያፀደቀው ይኼው ደንብ፣ ሁሉም የፍርድ ቤት ማኅበረሰብ እንዲያከብረው ያስገድዳል፡፡ መመርያው ሥራ ላይ የሚውለው ከነሐሴ ወር ጀምሮ ነው፡፡
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የችሎት ሥርዓት አከባበር በመመርያ ባልተደገፉ ሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎች ይካሄዱ የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ መመርያ የችሎት ሥርዓት አከባበሩ ወጥነትና ግልጽነት እንዲኖረው ለማድረግ ታቅዶ ተዘጋጅቷል፡፡
መመርያው በዳኞች፣ በባለጉዳዮች፣ በተከራካሪ ወገኖች፣ በፍርድ ቤት አስተዳደር ሠራተኞችና ማኅበረሰቦች፣ እንዲሁም በችሎት ታዳሚዎች የሚጠበቁ ሥነ ምግባሮችንና ኃላፊነቶችን ይዟል፡፡ የሥነ ምግባር ግዴታዎችን ጥሰው በሚገኙ ላይም ተጠያቂነት እንደሚኖርና የተለያዩ ሕጋዊ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ይደነግጋል፡፡
በመመርያው የተለያዩ 11 ድንጋጌዎች ለዳኞች የተዘጋጁ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥም የሥራ ሰዓትን አክብሮ ችሎት መሰየምና መምራት፣ እንዲሁም በበቂ ምክንያት ካረፈዱም ባለጉዳዮችን በማክበር ይቅርታ መጠየቅ ይገኝበታል፡፡ በተጨማሪም ዳኞች ችሎት ላይ ያሉ ባለጉዳዮችን ክብር በሚሰጥና የሙያ ማዕረግ በመጠቀም መጥራት እንደሚኖርባቸው ተደንግጓል፡፡
በቀጠሮው ዕለት ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ካልደረሰ ምክንያቱን በመግለጽ፣ ይህንኑ መዝገብ ላይ በመመዝገብ ጉድለቱ የፍርድ ቤት ወይም የችሎቱ፣ ወይም የዳኛው ከሆነ ይህንኑ ለባለጉዳዮች በመግለጽ፣ በትህትና ይቅርታ መጠየቅ እንዳለባቸውም፣ የዳኞችን የሥነ ሥርዓት ግዴታ መመርያው ያብራራል፡፡
በመመርያው መሠረት የችሎት ሥራ መጀመርያ ጠዋት 3፡30 ሰዓት፣ እንዲሁም ከሰዓት 8፡00 ሰዓት ሲሆን፣ እንደ አካባቢው ነባራዊ ሁኔታና የአየር ፀባይም ሊቀየር ይችላል፡፡ መደበኛ የፍርድ ቤት ሰዓትም እንደ መደበኛው የመንግሥት የሥራ ሰዓት እንደተጠበቀ ይሆናል፡፡
የዳኞች በችሎት በሰዓት አለመሰየም በርካታ ባለጉዳዮችን ሲያማርር የኖረ ጉዳይ እንደሆነ የሚጠቀስ ሲሆን፣ መመርያው ያስተካክለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሕግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ዳንኤል ፈቃዱም ይህንን የሚጋሩ ሲሆን፣ የችሎት በሰዓት አለመጀመርና አለመካሄድ የጉዳዮችን ፍሰት አስተዳደር ዕቅድ አሰጣጥ ተግባራዊ አለመሆን፣ ለሥራቸው አስቸጋሪ ከሆኑባቸው ጉዳዮች ዋነኞቹ ነበሩ ብለዋል፡፡
‹‹ባለጉዳይ ወይም ጠበቃ በሰዓቱ ካልተገኘ መብቱ ይታለፋል፣ ዳኛው ግን በሰዓቱ አብዛኛውን ጊዜ አይሰየምም፡፡ ይህ ደግሞ የጠበቃውን ጊዜ ይበላል፤›› ሲሉ አቶ ዳንኤል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ስለፍርድ ቤት አለባበስ ሥርዓት፣ ስለስያሜ አጠራር ሥርዓት፣ የቀጠሮ አሰጣጥ ሥርዓት፣ ከባለጉዳይ ስለሚጠበቅ ሥነ ምግባር፣ በችሎት ስለተከለከሉ ድርጊቶች፣ የቅድመ ችሎት ሥርዓት፣ እንዲሁም በግልጽ ችሎት መዳኘትን ጨምሮ 32 አንቀጾችን መመርያው ይዟል፡፡
መመርያው ማናቸውም ጉዳዮች በግልጽ ችሎት መታየት እንዳለባቸውና ማንኛውም ሰው እንደ አመጣጡ እየገባ ችሎትን የመከታተል መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ በዝግ ችሎት እንዲታዩ በሕግ የተደነገጉት ጉዳዮች ብቻ በዝግ ችሎት ይካሄዳሉ ይላል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን እጅጉ ግን፣ አንዳንዶችን ተግባራዊ ለማድረግ በመሠረተ ልማት አለመሟላት ምክንያት ሊያስቸግር ይችላል ብለዋል፡፡
‹‹በቂ የሆኑ የችሎት አዳራሾች ባለመኖራቸው ይህንን መመርያ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ችግር ሊገጥመው ይችላል፤›› ሲሉ አቶ ሰለሞን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የችሎት ዳኞች ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ ወዲያው ፍርድ እስከ መስጠትና ቅጣት እስከ መወሰን ድረስ የሆኑ ዕርምጃዎችን የችሎቱን ሥነ ሥርዓት በጣሱ ግለሰቦች ላይ መውሰድ እንዳለባቸው፣ የዚህን መመርያ ተፈጻሚነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንደሚኖርባቸው፣ ማንኛውም ዳኛ የመመርያውን ድንጋጌዎች ጥሶ ከተገኘ ግን በፌዴራል ዳኞች የሥነ ምግባርና የዲሲፕሊን ክስ ሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆን በመመርያው ታይቷል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕግ ምርምር ዋና ዳይሬክተር አቶ አሮን ደጎል፣ መመርያው ወዲያውኑ ተግባራዊ ይሆናል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ ነገር ግን ሌላው ቢቀር ወደ ሥርዓቱ ለማስገባት ትልቅ መንደርደርያ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
መመርያው እንዲያሳካቸው ከታሰበላቸው አምስት ግቦች ውስጥ አንደኛው በከፍተኛ ሥነ ምግባር በመታነፅ ተቋማዊ ባህልን ማስፈን መሆኑን አቶ አሮን ገልጸው፣ የችሎት ሥርዓትን ከዳኞች ጀምሮ በግልጽነት ተፈጻሚ በማድረግ የኅብረተሰቡን አመኔታ ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡