
ከ 2 ሰአት በፊት
የትግራይ ክልልን በበላይነት እየመራ የሚገኘው ህወሓት በትግራይ ክልል ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችን የትግራይ ሕዝብን ትግል “እንዳያደናቅፉ” አስጠነቀቀ።
ህወሓት ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ የክልሉ ቴሌቪዥን እንደዘገበው፣ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች “ሕዝባዊ ትግላችንን የሚያደናቅፉ እንቅስቃሴዎች አድርገዋል” ብሏል።
በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት)፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ (ውናት) እንዲሁም ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) የተባሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጦርነቱን በተመለከተ እና በክልሉ አስተዳደር ላይ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ በክልሉ ሁሉን አቀፍ የሽግግር አስተዳደር እንዲቋቋም መጠየቃቸው ይታወሳል።
ፓርቲዎቹ ክልሉን በማስተዳደር በኩል በህወሓት ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ በማንሳት፣ ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ጦርነት ለማብቃት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ይካሄዳል በተባለው ድርድር ላይ ህወሓት ትግራይን ወክሎ የመደራደርም ሆነ ክልሉን በብቸኝነት ማስተዳደር የለበትም ብለዋል።
በትግራይ ሕዝብ የኮሙኒኬሽን ቢሮ እና መንግሥት አማካይነት ወጣ በተባለው መግለጫ፣ “ቀደምት ታጋዮች ለሕዝቡ ህልውና በተደጋጋሚ መስዋዕትንት እየከፈሉ” መሆኑን ጠቅሶ፣ ነገር ግን ተቃዋሚዎቹ “የሚከፈለውን መስዋዕትነት በሚያሳንስ ሁኔታ በትግራይ መንግሥት ላይ ክሶችን እያቀረቡ ነው” ብሏል።
ጨምሮም ተቃዋሚዎቹ “በትግራይ ሕዝብ እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ ጦርነት ለማደናቀፍ ጥረት እያደረጉ ነው” ሲል ከሷቸዋል።
- የትግራይ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር የሚደራደር ቡድን ማቋቋማቸውን ገለጹ19 ሀምሌ 2022
- አዲሱ የሶማሊያ አስተዳደር ወታደሮቼ በኢትዮጵያ ጦርነት አልተሳተፉም አለከ 4 ሰአት በፊት
- ቆሻሻ መጣያ የነበረን ቦታ ወደ ውብ የመናፈሻ ሥፍራነት የለወጠች ሴት ከ 5 ሰአት በፊት
ተቃዋሚዎቹ ህወሓት ከዚህ በፊት በፌደራል መንግሥቱ ተቀባይነት ያላገኘ ክልላዊ ምርጫዎች በማካሄድ ‘የሕዝብ ተቀባይነት’ አግኝቻለሁ በማለት ሥልጣኑን አጠናክሯል በማለት፣ ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ ከሥልጣኑ መወገዱን ጠቅሰው ሕጋዊ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
ህወሓት በመግለጫው ላይ ተቃዋሚዎቹ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ከዚህ በኋላ እንደማይታገሰው አመልክቷል።
“ምንም እንኳን የትግራይ መንግሥት እራሳቸውን ያርማሉ ብሎ ቢታገሳቸውም፣ ትግላችንን ከማደናቀፍ አልታቀቡም” ብሏል።
ይህንንም በማንሳት በመግለጫው ላይ ተቃዋሚዎቹ በትግራይ ያለው ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ፈርሷል ስለዚህም የሽግግር መንግሥት ወይም የአንድነት መንግሥት እንዲቋቋም ጠይቀዋል ይህም “ትግሉን በሚያደናቅፍ ሁኔታ የትግራይ መንግሥት ሕጋዊ አይደለም አስከ ማለት ደርሰዋል” ብሏል።
ጨምሮም ተቃዋሚ ቡድኖቹ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተቀሰቀሰውን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም ህወሓት ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ለመደራደር ሥልጣን የለውም ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅት ትግላችንን የሚያደናቅፍ ተግባራት ላይ አተኩረዋል፤ የትግራይ ክልል መንግሥት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሰላም ንግግር ማድረግ የሚያስችል ሥልጣን የለውም” ማለታቸውንም ጠቅሷል።
ስለዚህም ተቃዋሚዎቹ “በቃችሁ ሊባሉ ይገባቸዋል። የትግራይ ሕዝብም ሥርዓት ሊያሲዛቸው ይገባል” ብሏል የህወሓት መግለጫ።
ለ20 ወራት የዘለቀውን የኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት ለመቋጨት ተዋጊ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ከተለያዩ ወገኖች ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የሚደራደሩ ሰባት አባላት ያሉት የኮሚቴ ይፋ ካደረገ በኋላ፤ ህወሓትም ከቀናት በፊት ከመንግሥት ጋር ድርድር የሚያደርግ ቡድን ማቋቋሙን ገልጿል።