ናንሲ ፔሎሲ
የምስሉ መግለጫ,የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ

ከ 4 ሰአት በፊት

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ታይዋን ቢያቀኑ መዘዙ ከባድ ነው ስትል ቻይና አስጠነቀቀች።

አፈ ጉባኤዋ ታይዋንን ሊጉበኙ ነው የሚል መረጃ መውጣቱ ቻይናን እጅጉን አበሳጭቷል ተብሏል።

ለአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ መንበር ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፔሎሲ፤ የራስ ገዝ ግዛት ወደሆነችው ታይዋን ጉዞ ቢያደርጉ ከእአአ 1997 ወዲህ ታይዋንን የጎበኙ ከፍተኛ ባለስልጣን ያደርጋቸዋል።

ታይዋን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ግዛት ብትቆጥርም ቻይና ግን እንደ ተገነጠለች ግዛቷ ነው የምትመለከታት። ቻይና አስፈላጊ ከሆነም በኃይል ታይዋንን መልሳ የግዛቷ አካል ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማትል ከዚህ ቀደም ገልጻለች።

ይህ የፔሎሲ ጉዞ ቤጂንግን ማበሳጨት ብቻ ሳይሆን፤ የባይደን አስተዳደርም የጂኦፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ከትቷል። ዋይት ሃውስ ፔሎሲ ወደ ታይዋን እንዳይጓዙ ጫና እያሳደረ መሆኑም ተገልጿል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ፕሬዝዳንት ባይደን የፔሎሲን ጉዞ በተመለከተ፤ “ጦሩ ጥሩ ሃሳብ አይደለም ብሎ ያስባል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።

ዋይት ሃውስ ደግሞ የቻይናን ማስጠንቀቂያ “ጠቃሚ ያልሆነ” ሲል ገልጾታል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በበኩሉ ፔሎሲ ወደ ታይዋን ለመሄድ በይፋ አለማሳወቃቸውን እና አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ ያላት አቋምም እንዳልተቀየረ ገልጿል።

አሜሪካ ታይዋን ራሷን እንድትከላከል ለመርዳት የሚያስገድድ ሕግ አላት። ይህ ሕግ ግን ሆነ ተብሎ ግልጽ እንዳይሆን ተደርጓል። በዚህም ቻይና ታይዋንን ብታጠቃ የአሜሪካ ምላሽ በትክክል ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይደለም።

ይሁን እንጂ አሜሪካ ለታይዋን የጦር መሳሪያዎችን ስትሸጥ ቆይታለች።

ታይዋን የምትመራበት የራሷ የሆነ ሕገ-መንግሥት አላት። በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡ መሪዎችም አሏት። ከ300 ሺህ ያላነሰ የጦር ሠራዊት አባላትም ባለቤት ነች።

ፔሎሲ ወደ ታይዋን መጓዝ ለምን አስፈለጋቸው?

የአሜሪካ ኮንግረስ ለታይዋን ጠንካራ ድጋፍ ይሰጣል። በምክር ቤት አባልነት ከ35 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው ፔሎሲ ቻይናን አጥብቀው በመተቸት ይታወቃሉ።

የቻይናን የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ደጋፊዎች ላይ የሚደርሰውን ጫና በማንሳት ቻይናን ይተቻሉ።

ፔሎሲ የታይዋን ጉዟቸውን በተመለከተ በዝርዝር ያሉት ነገር ባይኖርም፤ ከአንድ ሳምንት በፊት “ለታይዋን ድጋፍ ማሳየታችን ለእኛ አስፈላጊ ነው” ብለው ነበር።

ቻይና የፔሎሲን ጉብኝት ለምን ትቃወማለች?

ቻይና እንደ አንድ የራሷ ግዛት አድርጋ የምታየት ታይዋን ከዋሽንግተን ዲሲ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግነኙነት ማጠናከሯ እረፍት ይነሳታል።

ሚያዚያ 2014 ዓ.ም. አራት የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ታይዋንን መጎብኘታቸው ቻይናን አበሳጭቶ ነበር።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛሆ ሊጂአን ፔሎሲ ወደ ታይዋን የሚጓዙ ከሆነ፤ አገራቸው “ጠንካራ እርምጃ” ትወስዳለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ደግሞ ቤጂንግ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችልም ጠቁመዋል።

“የአሜሪካ ወገን በዕቅዱ የሚቀጥል ከሆነ፤ የቻይና ጦር ዝም ብሎ አይመለከትም። የውጪ ጣልቃ ገብነትን ለማስቆም እና ተገንጣይ ኃይሎች ‘ነጻ ታይዋንን’ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀልበስ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል” ሲሉ ኮሎኔል ታን ኬፊ ለቻይና ዴይሊ ተናግረዋል።

ታይዋን እንዴት ከቻይና ተለየች?

ቻይና እና ታይዋን የተለያዩት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሲሆን በጊዜው ቻይና ራሷ በአንድነት መንግሥት እና በኮሚዩኒስት ፓርቲ መካከል ለሁለት ተከፍላ ጦርነት ላይ ነበረች።

በአውሮፓውያኑ 1949 ኮሚዩኒስት ፓርቲ ድል ሲቀዳጅ የወቅቱ መሪ ማኦ ዜዱንግ ቤይጂንግን መቆጣጠር ቻሉ።

ሽንፈትን ያስተናገዱት የብሔራዊ ፓርቲው ደጋፊዎችና መሪዎች ታይዋን ሸሽተው ገቡ። የፓርቲው መሪ ቻንግ ካይ ሼክም ታይዋንን መደበቂያቸው አደረጓት።

ትንሽ ቆይተውም ኩሚ ታንግ የተባለውን ፓርቲ እዚያው ታይዋን ውስጥ መሠረቱ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ታዲያ ይህ ፓርቲ ታይዋን ውስጥ ወሳኝ የሚባል የፖለቲካ ክንፍ ሆኖ ቆይቷል።