
ከ 5 ሰአት በፊት
የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ስድስት ቀናት የፈጀ ጉብኝት በተለያዩ የአፍሪካ አገራት አድርዋል።
ሚኒስትሩ የመጨረሻ መዳረሻቸው በሆነችው አዲስ አበባ ተገኝተው “ለዓለም የምግብና ነዳጅ ዋጋ ቀውስ ምዕራባዊያን አገራት ተጠያቂዎች ናቸው” ብለዋል።
ሰርጌይ፤ ከኢትዮጵያ አቻቸው ደመቀ መኮንን እና ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው መክረዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን “ውይይታችን በጣም ፍሬያማ ነበር። ሩሲያ እንደከዚህ ቀደሙ በመርኅና በእውነታ ላይ የተመሠረተ ድጋፍ ለኢትዮጵያ ማድረጓ የሚደነቅ ነው። ይህን ማጠናከር እንደሚገባ ተወያይተናል” ብለዋል።
የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደግሞ “በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር እንዲሻሻል እንሠራለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
የሩሲያው ከፍተኛ ልዑክ የጉብኝት ዓላማ አገራቸው ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደሆነ ገልጠዋል።
ለመሆኑ ሩሲያ ወደ አፍሪካ ፊቷን ማዞር ለምን ሻተች? ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገራትስ ከሩሲያ ምን ያገኛሉ?
ታሪካዊ ዳራ
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ይፋዊ ግንኙነት ከጀመሩ 124 ዓመታት ተቆጥረዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ግንኙነት የጀመሩት አጤ ምኒልክ እና የሩሲያው ንጉስ ኒኮላ አሌክሳንድሮቪች ሮማኖቭ እንደሆኑ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ሶቪዬት ኅብረት በመባል ትታወቅ ወደነበረችው ሰፊ ግዛት በመሄድ ትምህርት ቀስመዋል።
አሁንም በትምህርት እና ሥራ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች መኖሪያቸውን ሞስኮው ያደረጉ ኢትዮጵያውያን አሊያም አዲስ አበባ የከተሙ ሩሲያውያን ማግኘት የተለመደ ነው።
ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ያሉት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ መንግሥታት ከሩሲያ ጋር ያላቸው ግንኙነት የጠበቀ ይመስላል።
በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወታደራዊው አገዛዝ [ደርግ] ከሶቪዬት ኅብረት ጋር ጥብቅ የሚባል ግንኙነት ነበረው።
በወቅቱ ኢትዮጵያ በካፒታሊዝም ከሚመራው የምዕራባዊያን ካምፕ ጋር የነበራት ግንኙነት ጠንካራ ባይባልም በሯ ግን ሙሉ በሙሉ ዝግ አልነበረም።
ደርግ ከወደቀ በኋላም ቢሆን ኢትዮጵያና ሩሲያ ግንኙነታቸው እንደቀድሞ ባይሆንም የሻከረ ግንኙነት አልነበራቸውም።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፊት የነበረው አገዛዝ ከአሜሪካ፣ ከቻይና እንዲሁም ከሩሲያ ጋር የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ትስስር መልካም ነበር ይላሉ የዘርፉ ተንታኞች።
ነገር ግን ኢትዮጵያና ሩሲያ፤ ልክ ከቻይና ጋር እንዳለው ምጣኔ ሀብታዊ ትብብር ጥብቅ ግንኙነት አሊያም ከአሜሪካ ጋር እንዳለው የፀረ-ሽብር ትብብር ዓይነት ግንኙነት አልነበራትም።
- አዲስ አበባን የጎበኙት ላቭሮቭ ለዓለም የምግብ ገበያ ቀውስ ምዕራባውያንን ተጠያቂ አደረጉ27 ሀምሌ 2022
- በግብፅ የተገኙት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ ሊጓዙ ነው25 ሀምሌ 2022
- ዩክሬን እና ሩሲያ እህል ወደ ውጭ እንዲላክ ምን ለማድረግ ተስማሙ?23 ሀምሌ 2022

የሩሲያ ፍላጎት ምንድነው?
ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በሚል የሩሲያ አፍሪካ ስብሰባን ከጀመረች እንሆ ሦስት ዓመታት ተቆጠሩ።
ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት ከትግራይ ጦርነት በኋላ እየሻከረ መጥቷል።
ከእርስ በርስ ጦርነቱ ጋር ተያይዞ ከተባበሩት መንግሥታት ጀምሮ ምዕራባውያን ለጦርነቱ የኢትዮጵያ መንግሥትን ተወቃሽ ሲያደርጉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።
አሜሪካ ይህንን ጦርነት ተከትሎ ለምርቶች ዕድል ይፈጥራል ከሚባለው አጎዋ ኢትዮጵያን ማገዷ አይዘነጋም።
ዓለም አቀፍ ተቋማት የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል።
መሰል ሐሳቦች ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት መጥተው ድምፅ ተሰጥቶባቸዋል።
ነገር ግን ሩሲያ እና ቻይና በአዳራሹ ያላቸውን ድምፅ ተጠቅመው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ወግነዋል።
ሩሲያ ወደ አፍሪካ ፊቷን ያዞረችው እየደረሰባትን ያለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ነው ይላሉ የምሥራቅ አፍሪካና ኦሬንታል ጥናት ዘርፍ ተመራማሪ ነአምን አሸናፊ።
“ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በገባችው ጦርነት ምክንያት ከምዕራባዊያን ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና እየደረሰባት ነው ያለው።”
ተመራማሪው የሰርጌይ ላቭሮቭ ወደ አፍሪካ መምጣት ይህን ጫና ለመቋቋምና አጋር የመሰብሰብ ዓላማ ያለው ነው ብለው ያምናሉ።
“ሩሲያ ከዩክሬን ጦርነት በኋላ ከአውሮፓውያን ጋር ያላት ግንኙነት በተለይ ደግሞ የኃይል ምርት ንግድ ተስተጓጉሏል።
“ሞስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ቦታ ከፍ ለማድረግ አሊያም ባለበት አስጠብቆ ለማስኬድ በማለም ነው ወደ አፍሪካ የመጣችው” ይላሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የምዕራባውያንን ተፅዕኖ የመቋቋም አቅም አለን የሚል መልዕክት ያዘለ ነው ሲሉም ያክላሉ ነአምን።
ተመራማሪው ሩሲያ ከምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን በመጥቀስ “በምሥራቅ አፍሪካ የጦር ኃይል እንዲኖራት ከፍተኛ ሥራ እየሠራች ነው።
ከሱዳን መንግሥት ጋር የገባችውን ስምምነት ማስታወስ እንችላለን። ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ግብፅና ሌሎች አገራትንም ጎብኝተዋል።”
ሩሲያና ቻይና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ሲሞክር የተቃውሞ ድምፅ ማሰማታቸውን የሚያወሱት ተመራማሪው፣ እኚህ ውሳኔዎች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለሙ ናቸው የሚል ግምት አላቸው።
ሰርጌይ ላቭሮቭ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ምናልባት በትግራዩ ጦርነት ድርድር አገራቸው ሚና እንዲኖራት ለማድረግም ሊሆን ይችላል ባይ ናቸው ተመራማሪው።
የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ጦርነቱን በድርድር ለመፍታት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ በደተጋጋሚ ተዘግቧል።
“በአጠቃላይ ጉዞው አሜሪካና ቻይና በቀጣናው ያላቸውን ተፅዕኖ ለመገዳደር፣ አሊያም ከእነሱ የተሻለ ለማድረግ ያለመም ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
በዋናነት ግን ይላሉ ተንታኙ… “ሩሲያ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ሲታይ እንዲሁም የጎበኟቸውን የአፍሪካ አገራት ስንመለከት የደረሰባቸውን ዲፕሎማሲያዊ መገለል የመቀልበስ ትግል አካል ነው።”
ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ከምዕራባዊያን ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ የመጣ ቢመስልም መንግሥት ግን ይህ ትክክል አይደለም ይላል።


የኢትዮጵያ እና ሩሲያ
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “በታሪክ ኢትዮጵያ ከካፒታሊዝምና ከሶሻሊዝም በግድ አንዱን እንድትመርጥ የተደረገበት ጊዜ ነበር። አሁን ያለው ሁኔታ ግን እንደዚያ አይደለም። ከዚህ አገር እንጂ ከዚያ አገር ጋር አንፈልግም የሚባል ነገር የለም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ከምዕራባውን ጋር ያለው ፍጥጫ ተባብሶ ከሩሲያና ከቻይና ጋር ያለው ግንኙነት እየሞቀ መሄዱን አስመልክቶ አምባሳደሩ “ጊዜያዊ ጉዳይ ነው። የአገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይህን መሰል ውጣ ውረድ አለው፤ የሚስተካከለል ነው” ሲሉ ገልጠው ነበር።
የምዕራቡ ዓለም አገራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ተፅዕኖ ፈጣሪ ድርጅቶች ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯ ትክክል አይደለም የሚል አቋም ሲያሰሙ፣ ኢትዮጵያ ከወቀሳ ተቆጥባ ጦርነቱ በሰላም ሊፈታ ይገባል የሚል መግለጫ ማውጣቷ ይታወሳል።
አልፎም የተባበሩት መንግሥታት ሩሲያ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ አገራትን ድምፅ ሲጠይቅ ኢትዮጵያ በስብሰባ ሳትገኝ ቀርታለች።
በትግራይ ጦርነት ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች “የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ይቁም” የሚሉ ሰልፎች ታይተዋል።
በአድዋ ድል መታሰቢያ ወቅት ደግሞ የኢትዮጵያ ባንዲራ እና የሩሲያ ባንዲራ እኩል ሲውለበለቡ ተስተውለዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጎን ለመሰለፍ አዲስ አበባ በሚገኘው የሞስኮ ኤምባሲ ተሰልፈው መታየታቸውም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ከምዕራባዊያን ወይስ ከሩሲያና ቻይና የምታደርገው ግንኙነት ነው አዋጭ? የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል።
ነአምን ይህን ጥያቄ ለመመለስ መጀመሪያ የውስጥ ሰላማችን ሊከበር ይገባል ይላሉ።
“ማንኛውም ውጫዊ ተፅዕኖ አንድን አገር ሊያንበረክክ የሚችለው ውስጣዊ ሰላም ከሌለ ነው። ፀጥታን፣ ሰላምን እንዲሁም የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ ከምዕራባዊያኑም ሆነ ከሩሲያና ከቻይና ሊመጣ የሚችልን ተፅዕኖ ለመቋቋም ይጠቅማል።”
ተንታኙ አክለው የኢትዮጵያን ጥቅም እንዴት ማስጠበቅ እንደሚቻል የሚጠቁም ግልፅ የሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊኖር ያስፈልጋል ይላሉ።
አክለው በአካባቢው ካሉ አጎራባች አገራት ጋር ሰላም ሊኖር እንደሚያስፈልግ ያሰምራሉ።
“ስለምሥራቅ አፍሪካ ስናወራ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም ዋነኛ ተዋናይ። ኤርትራንም ሶማሊያንም መጥቀስ ይቻላል። ከአጎራባች አገራት ጋር ያለ ሰላማዊ ግንኙነት ጥቅምን አስጠብቆ ለመሄድ የሚደረገውን ጉዞ ያጠናክራል።”
ነአምን ከሁሉም በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ከሌሎች አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በልኩ ማድረግ እንደሆነ ይናገራሉ።
“ግንኙነትን በልኩ ማድረግ። ከምዕራባውያንም ጋር ይሁን፣ ከቻይና አሊያም ከሩሲያ የራስን ጥቅም ባስቀደመ መልኩ እንጂ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም አሊያም የጦር መሣሪያ ለማግኘት ሲባል የሚቀየር የፖሊሲ አሊያም የማንነት ቀለም ሊኖር አይገባም።”

ሩሲያ እና አፍሪካ በንግዱ ዘርፍ
ኢትዮጵየያ 40 በመቶ የእህል ፍላጎትዋን የምትሟላው ከዩክሬይን እና ከሩሲያ በሚመጣ ምርት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ዓለም አቀፍ ንግድን የሚከታተለው ኦብዘርቫቶሪ ኦፍ ኢኮኖሚክ [ኦኢሲ] በፈረንጆቹ 2020 ሩሲያ ስንዴን ጨምሮ 44.2 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት ወደ ኢትዮጵያ መላኳን ይገልጣል።
ኢትዮጵያ በበኩላ በተመሳሳይ ዓመት ወደ ሩሲያ ከላከችው ምርቶች በብዛት የቡና የሚገኝበት ሲሆን 17 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ መሆኑን ተቋሙ ያመለክታል።
በርካታ የአፍሪካ አገራት ስንዴ የሚያስመጡት ከሩሲያን እና ከዩክሬይን ነው።
የአፍሪካ አገራት በዩክሬን ባለው ጦርነት ምክንያት የተስተጓጎለው የእህል አቅርቦት ተመልሶ እንዲቀጥል ሩሲያ ማረጋገጫ እንድትሰጣቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር።
ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ ከ2015 ጀምሮ በሁለት እጥፍ አድጓል። በሩሲያና በአፍሪካ መካከል ያለው ንግድ በገንዘብ ሲተመን 20 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ መሆኑ ይነገራል።
ከ2015 ጀምሮ ባለው ጊዜ ሩሲያ 14 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ምርት ስትልክ 5 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ምርት ደግሞ ከአፍሪካ አገራት አስገብታለች።
ሩሲያ አፍሪካ ይልቅ ከአውሮፓ እና ኤዥያ አገራት ጋር ሰፊ የሚባል የንግድ ትስስር አላት።
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት ከሩሲያ ይልቅ ከሕንድ፣ ከቻይና እና ከአሜሪካ ጋር የጠበቀ የንግድ ግንኙነት አላቸው። አሜሪካ፣ ቻይና እና የአውሮፓ ኅብረት ለአፍሪካ አገራት የልማት ድጋፍ እና ኢንቨስትመንት በመስጠትም ይታወቃሉ።

ሩሲያ በአፍሪካ ያላት ተሳትፎ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመካከለኛው ምሥራቅ የነበራቸውን ጉብኝት ባገባደዱ በሳምንቱ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉብኝታቸውን ጀምረዋል።
ይሁን እንጂ በርካታ የአረብ እና የአፍሪካ አገራት ከሁለቱም ኃያል ከሚባሉ አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጎራ በመያዝ ማበላሸት የሻቱ አይመስሉም።
ሩሲያ ዩክሬንን በወረረች ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ጎራ የለየ ሐሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቢሆንም የአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ዜጎች የሩሲያን ባንዲራ ከፍ አድርገው አውለብለዋል።
ባለፈው ጥር በቡርኪናፋሶ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ ደግሞ ሰልፍ የወጡ የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ዜጎች የሩሲያን ባንዲራ ይዘው ታይተዋል።
አልፎም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ያወጀችውን ጦርነት የሚያወግዝ የውሳኔ ሐሳብ ባቀረበበት ወቅት ከ54 የአፍሪካ አገራት 28ቱ ብቻ ናቸው ሐሳቡን የደገፉት። በዚህ ጉባኤ ኢትዮጵያ ባለመገኘቷ ድምፅ ሳትሰጥ ቀርታለች።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በ2020 ሩሲያ በውጭ ፖሊሲዋ ለአፍሪካ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልጠው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ አገራቸው ከአፍሪካ አገራት ጋር ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምታጠናክር አልፎም የመከላከያ እና የደኅንነት እንዲሁም ኢኮኖሚ ድጋፍ እንደምትሰጥ ተናግረው ነበር።
አፍሪካ፤ ትልቋ የሩሲያ የጦር መሳርያ ገበያ ባትሆንም ሞስኮው ለበርካታ አገራት የጦር መሣሪያ በብዛት ታቀርባለች።
በፈረንጆቹ ከ2014 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ግብፅን ሳይጨምር ከሩሲያ የጦር መሣሪያ 16 በመቶው የተላከው ወደ አፍሪካ አገራት ነው፣ የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም እናዳለው።
ሩሲያ በ25 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለግብፅ የገነባችው የመጀመርያው የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ የሚጠቀስ ነው።
ከዚህ መካከል 80 በመቶው ወደ አልጄርያ የተላከ ሲሆን ከሰሃራ በታች አገራት የተላከው የጦር መሣሪያ ብዛት ግን ይህን ያህል አይደለም።
ቢሆንም ከ2015 ጀምሮ ባለው ጊዜ ከ20 በላይ የአፍሪካ አገራት ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ የስምምነት ፊርማ አኑረዋል።
ከ2017 ብቻ ሩሲያ ከአንጎላ፣ ከናይጄሪያ፣ ከሱዳን፣ ከማሊ፣ ከቡርኪናፋሶ እና ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር የጦር መሳርያ ስምምነት አድርጋለች።
የውጊያ ጀቶች፣ የትራንስፖርት ሄሊኮፕተሮች፣ ፀረ-ሚሳይል ታንኮች እና የተዋጊ አውሮፕላን ሞተሮች ወደ አፍሪካ ከተላኩ የሩሲያ የጦር መሣሪያዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሩሲያ እንደ ማግኒዥየም፣ ቦክሳይት፣ ክሮሚንየም ያሉ ለኢንዳስትሪ አስፈላጊ የሆኑ ማዕድናት እጥረት ስላለባት በአፍሪካ ግልጽ የኢኮኖሚ ፍላጎት አላት።
የሩሲያ መንግሥት ኩባንያዎች በጊኒ የቦክሳይት ማዕድን ቁፋሮ ላይ የተሰማሩ ሲሆን፤ በአንጎላ ደግሞ አልማዝ ለመቁረጥ ስምምነት አላቸው።
ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በማለም ‘ሩሲያ-አፍሪካ ሰሚት’ የተሰኘ ጉባዔ ከ2019 አንስቶ ማካሄድ ጀምራለች።
የመጀመሪያው የሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ በሩሲያዋ ሶቺ ከተማ ሲካሄድ ኢትዮጵያን ጨምሮ 43 የአፍሪካ አገራት ተሳትፈዋል።
በወቅቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ አፍሪካን ለመከፋፈል ሳይሆን ከአፍሪካ ጋር ለመሥራት ነው ዓላማችን የሚል ይዘት ያለው ንግግር አሰምው ነበር።
በዚህ ጉባኤ የሩሲያ መንግሥት እና የአፍሪካ መሪዎች በፖለቲካ፣ በደኅንነት፣ በንግድ እና በኢኮኖሚ፣ በሳይንስ እና በትምህርት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በሌሎችም መስኮች አብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጠዋል።
ሁለተኛው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ በሚቀጥለው ዓመት አዲስ አበባ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።