
ከ 4 ሰአት በፊት
የአሜሪካ እና የቻይና መሪዎች በታይዋን ጉዳይ ለሁለት ሰዓታት በዘለቀ የስልክ ንግግራቸው አንዳቸው ሌላኛውን አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ የታይዋንን የህልውና ጥያቄን የሚቀይር የተናጠል እርምጃን አጥብቃ እንደምትቃወም ለቻይናው አቻቸው ዢ ዢንፒንግ ተናግረዋል።
ባይደን አሜሪካ ታይዋንን በተመለከተ ያላት ፖሊስ እንዳልተለወጠም ለቻይናው መሪ ተናግረዋል።
ዢ በበኩላቸው ባይደን ‘የአንድ ቻይናን መርህ’ እንዲያከብሩ ካሳሰቡ በኋላ፤ “ማንኛውም በእሳት የሚጫወት መቃጠሉ አይቀርም” ሲሉ ባይደንን ወርፈዋል።
የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ታይዋን ሊያቀኑ ነው መባሉን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት ነግሷል።
- የአልሸባብ ጥቃት ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ስጋት ይዞ ይመጣ ይሆን?ከ 5 ሰአት በፊት
- የመንግሥትና የህወሓት ድርድር ከኬንያ ምርጫ በኋላ ሊጀመር ይችላል ተባለከ 5 ሰአት በፊት
- መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑ ተገለጸ28 ሀምሌ 2022
ቻይና እንደ አንድ የራሷ ግዛት አድርጋ የምታየት ታይዋን ከዋሽንግተን ዲሲ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከሯ እረፍት ይነሳታል።
ምንም እንኳ እስካሁን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አፈ ጉባኤዋ ወደ ታይዋን እንደሚጓዙ ይፋ አይደለም ቢልም፤ ቻይና ፔሎሲ ወደ ታይዋን ከተጓዙ፤ መዘዙ ከባድ ነው ስትል አስጠንቅቃለች።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛሆ ሊጂአን ፔሎሲ ወደ ታይዋን የሚጓዙ ከሆነ፤ አገራቸው “ጠንካራ እርምጃ” ትወስዳለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ደግሞ ቤጂንግ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችልም ጠቁመዋል።
“የአሜሪካ ወገን በዕቅዱ የሚቀጥል ከሆነ፤ የቻይና ጦር ዝም ብሎ አይመለከትም። የውጪ ጣልቃ ገብነትን ለማስቆም እና ተገንጣይ ኃይሎች ‘ነጻ ታይዋንን’ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀልበስ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል” ሲሉ ኮሎኔል ታን ኬፊ ለቻይና ዴይሊ ተናግረዋል።

ፔሎሲ፤ የራስ ገዝ ግዛት ወደሆነችው ታይዋን ጉዞ ቢያደርጉ ከእአአ 1997 ወዲህ ታይዋንን የጎበኙ ከፍተኛ ባለስልጣን ያደርጋቸዋል።
ታይዋን ራሷን እንደ ሉዓላዊ ግዛት ብትቆጥርም ቻይና ግን እንደ ተገነጠለች ግዛቷ ነው የምትመለከታት። ቻይና አስፈላጊ ከሆነም በኃይል ታይዋንን መልሳ የግዛቷ አካል ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማትል ከዚህ ቀደም ገልጻለች።
ምንም እንኳ አሜሪካ ታይዋንን እንደ ሉዓላዊት አገር ባትቆጥራትም፤ በዲሞክራሲያዊ መንግድ የተመረጠው መንግሥት እራሱን መከላከል እንዲችል በሚል የጦር መሳሪያዎችን በሽያጭ መልክ ታቀርባለች።
ትናንት ሐምሌ 21/2014 ዓ.ም. ሁለቱ ኃያላን መሪዎች በስልክ በነበራቸው ንግግር ፊት ለፊት ተገናኝቶ መነጋገር ስለሚቻልበት ሁኔታ መወያየታቸውን የባይደን አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊ ተናግረዋል።
ይህ መሪ ባይደን እና ዢ ያደረጉትን የስልክ ንግግር “ቀጥተኛ እና ሐቀኛ” ሲሉ ገልጸውታል።
ሁለቱ መሪዎች ከታይዋን በተጨማሪ በከባቢ አየር ለውጥ እና የጤና ደኅንነትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል ተብሏል።
ታይዋን ከቻይና እንዴት ተለየች?
ቻይና እና ታይዋን የተለያዩት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሲሆን በጊዜው ቻይና ራሷ በአንድነት መንግሥት እና በኮሚዩኒስት ፓርቲ መካከል ለሁለት ተከፍላ ጦርነት ላይ ነበረች።
በአውሮፓውያኑ 1949 ኮሚዩኒስት ፓርቲ ድል ሲቀዳጅ የወቅቱ መሪ ማኦ ዜዱንግ ቤይጂንግን መቆጣጠር ቻሉ።
ሽንፈትን ያስተናገዱት የብሔራዊ ፓርቲው ደጋፊዎችና መሪዎች ታይዋን ሸሽተው ገቡ። የፓርቲው መሪ ቻንግ ካይ ሼክም ታይዋንን መደበቂያቸው አደረጓት።
ትንሽ ቆይተውም ኩሚ ታንግ የተባለውን ፓርቲ እዚያው ታይዋን ውስጥ መሠረቱ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ታዲያ ይህ ፓርቲ ታይዋን ውስጥ ወሳኝ የሚባል የፖለቲካ ክንፍ ሆኖ ቆይቷል።