
ከ 5 ሰአት በፊት
ከስምንት ወራት በፊት ቻናል ፎር የተሰኘው የዩናይትድ ኪንግደም ቴሌቪዥን በሰራው ዘገባ ላይ ኮሎኔል ዴቅ አብዱላሂ የተሰኙ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ከፍተኛ አዛዥ፣ አልሸባብ ከኢትዮጵያ ድንበር ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
”ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት አለ። በተለይም አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቀውስ ተከትሎ አዲስ ኃይልም እየመለመሉ ይገኛሉ” ሲሉ አዛዡ በዘገባው ላይ ሲናገሩ ይሰማሉ።
ከወራት በፊትም በኤልከሬ ወረዳ ውስጥ፤ ሂሎ ማዶው በተባለ መንደር ውስጥ ባካሄደው አሰሳ በጉድጓድ ውስጥ ተቀብረው የነበሩ የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎችን ማግኘቱን ገልጾም ነበር።
እስካሁን ስለጥቃቱ የምናውቀው
እነዚህ የማስጠንቀቂያ ደወሎች ከተሰሙ ከወራት በኋላ አልሸባብ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ በመግባት ጥቃት ከፍቷል።
የመጀመሪያው ጥቃት ባኩል በተሰኘው ሶማሊያ ክፍለ አገር የጀመረ ነው። ባኩል ሶማሊያ ካሏት 18 ግዛቶች መካከል አንዱ ነው።
በባኩል በኩል የተሰነዘረው ጥቃት ሦስት የድንበር ከተሞችን ያካለለ ነው። ዬድ፣ ወሻኮ እና አቶ ናቸው። እነዚህ የድንበር ከተሞች በሶማሊያ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ለኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ የሚገኙ ናቸው።
ስለዚህም አልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ ከማለፉ በፊት ጥቃቱን በሶማሊያ ጀምሮ ማለፉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሳምንት በፊት ረቡዕ በተከፈተው በዚህ ጥቃት አልሸባብ ሁለት ቡድኖችን ማሳተፉን እና ከሶማሊያ የሚያሻግር አንድ ቡድን እንዲሁም፣ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ የሚገባ ሌላ ቡድኖች እንደነበሩም ታውቋል።
በመቀጠልም ሁለተኛው ዙር ጥቃት ሰኞ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በሶማሊያ ፊር ሸበሌ ክልል በኩል የተከፈተ ነው። ይህንን አካባቢ ተከትላ ፌር ፌር የተሰኘችው የኢትዮጵያ የድንበር ከተማ ትገኛለች። ከፌር ፌር አካባቢ ላስቁሩን የተሰኘች ከተማ ላይ ውጊያ ተካሂዷል።
ከፍተኛ ውጊያን ያስተናገደው እና የኢትዮጵያ መንግሥት ከ80 በላይ የአልሸባብ ታጣቂዎች መገደላቸውን የገለጸው በዚሁ በፌር ፌር በኩል ነው።
በአካባቢው በልዩ ኃይል ኃይሎች እና በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ አባላት መካከል የተካሄዱ ውጊያዎችን የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንኑ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አምስተኛዋ እና አነስተኛ ውጊያን ያስተናገደችው በሪስማን የተሰኘች ሌላኛዋ ፌርፌር አካባቢ ያለች ቦታ ነች።
በአጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ ከገባው ከአልሻባብ ታጣቂዎች ጋር ለሦስት ቀናት በተደረገው ውጊያ 209 ታጣቂዎችን መገደላቸውን፣ 13 ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን እንዲሁም በርካታ የጦር መሳሪያዎች መማረካቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ጋር ተሰማርቶ ተበታትነዋል የተባሉትን የአልሻባብ ታጣቂዎችን በማደን ላይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ከማክሰኞ ወዲህ የተዘገበ አዲስ ጥቃት የለም።
ታዲያ ይህ ለአምስት ቀናት የቀጠለው የአልሸባብ እና የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጥቃት ምን ያህል ለአገሪቱና ለአካባቢው ሰላም አሳሳቢ ነው?
- “አልሸባብን ብንመክተውም ከዚህ በኋላ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል” ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ 26 ሀምሌ 2022
- የአልሻባብ ታጣቂዎች ድንበር አልፈው የፈፀሙት ጥቃት ዓላማ ምን ነበር?25 ሀምሌ 2022
- አልሸባብ በሶማሌ ክልል ስለፈፀማቸው ጥቃቶች የምናውቃቸው አምስት ነጥቦች26 ሀምሌ 2022
አልሸባብ ባለፉት ዓመታት ጠነከረ ወይስ ተዳከመ?
በሶማሊያ አልሸባብን ለመመከት በአፍሪካ ኅብረት የተሰማራው አሚሶም ከአገሪቱ ለመውጣት የመውጫ ዕቅዱን እየተገበረ እንደሚገኝ ይነገራል። በዚህም ወታደራዊ ተልዕኮው ስያሜውን ብሎም የተወሰኑ ኃላፊነቶቹን እስከማሻሻል የደረሰ ነው።
የኢትዮጵያን ጨምሮ የአምስት የአፍሪካ አገራትን ሠራዊት የያዘው አሚሶም፣ አሁን ላይ ውጊያ ማድረግ መቀነሱን ሶማሊያን እና ኢትዮጵያን ጨምሮ የቀጠናውን የፖለቲካ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ የተከታተሉት እና ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ፋይሰል ሮብሌ ይናገራሉ።
አክለውም አልሸባብ ባለፉት ዓመታት በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች አቅሙን ማጠንከሩን መገመት እንደማያስቸግር ይጠቅሳሉ።
ፋርማጆ በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ በተለይ ከአል ኢትሃድ ጋር ስማቸው ተደጋግሞ የሚነሳ ባለሥልጣናት ነበሯቸው ሲሉ ይወቅሳሉ።
አል ኢትሃድ በአውሮፓውያን 1990ዎቹ አልሸባብ ከመፈጠሩ በፊት ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ይፈጽም የነበረ ታጣቂ ቡድን ነበር።
ፋርማጆ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በርካታ የአልሸባብ ኃይሎች አስተዳደራቸውን ተቀላቅለው እንደነበረም ይናገራሉ።
አልሸባብ ባለፉት አራት ዓመታት በታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊ መመልመሉን የሚናገሩት ፋይሰል ከዚህ ቀደም 10 ሺህ የማይሞላ ታጣቂ እንዳለው ቢገመትም አሁን ከ30 ሺህ ሳይሻገር አይቀርም ይላሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ በቅድሚያ ኦብነግን ቀጥሎም አልሸባብን ለመዋጋት የተዋቀረው የክልሉ ልዩ ፖሊስ ባለፈው ሦስት ዓመታት በክልሉ የክርክር ርዕስ ነበር።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሱ ግጭቶችን አስመልከቶ በርካቶች ከመደበኛ ሠራዊት ጋር የሚስተካከል ትጥቅና አደረጃጀት ያላቸው የክልል ልዩ ኃይሎች ይፍረሱ ሲሉ ተደምጠዋል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ልዩ ፖሊስ የሚል ጽንሰ ሃሳብ የተተገበረበት የሶማሌ ክልልም እነዚህ ሃሳቦችን አስተናግዷል።
ፋይሰል በልዩ ኃይሎች ላይ ከሚነሳው ክርክር ጋር ተያይዞ ች ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ ልዩ ፖሊስን በሚመለከት የሚሰጧቸው አስተያየቶች የልዩ ኃይሉን እምነት እንዲያጡ ያደረጉ ነበሩ ይላሉ።
እንዲሁም በሶማሌ ክልል ድንበር ላይ ያለው የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ኃይል መቀነሱ ተጨምሮበት አልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ደፍሮ እንዲገባ ምቹ ሜዳ ፈጥሯል ሲሉም ያክላሉ።
ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ የልዩ ኃይሉ አስፈላጊነት ላይ ለመወያየት አሁን ጊዜው አይደለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በኢትዮጵያ የፀጥታ አደረጃጀት ላይ ሌላ ጊዜ ብንነጋገር ጥሩ ነው። ነገር ግን አሁን ላይ ድንበር እየጠበቀ እና አገር ሊያጠፋ የመጣውን ኃይል እየመከተ ያለው በዋናነት ልዩ ኃይሉ ነው” ተናግረዋል።

መንግሥት ጥቃቱን ቀድሞ መተንበይ አልቻለም?
የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንዳሉ ሆነው ባለፉት ቀናት በርካቶች አልሸባብ ጥቃት ሊሰነዝር እንደሚችል የሚያሳዩ መረጃዎች ነበሩ ሲሉ ሞግተዋል። ይህንን ስጋት የሚመጥን ዝግጅት ግን ከመንግሥት በኩል አልተደረገም ይላሉ።
ፋይሰል እንደሚሉት አልሸባብ ጥቃት ከመክፈቱ በፊት ቅድመ ዝግጀት የማድረግ ስልት አለው። ይህም ለውጊያ የሚረዱትን መሠረተ ልማቶች ማጥናት እና ማሰናዳትን ይጨምራል።
ታዲያ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ከአራት ወር በፊት አልሸባብ ሊያጠቃ እንደሚችል የሚያሳይ ጥቆማ ቢሰጡም መንግሥት ሳይዘጋጅ ቀርቷል ብለዋል – ፋይሰል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ግን ይህንን ወቀሳ አይቀበሉትም።
“አልሸባብ ባለፉት 4 ዓመታት ሶማሌ ክልል ለመግባት ጥረት ያደርግ ነበር፤ ስንከላከል ስለቆየን ነው ያከሸፍነው” ሲሉ ይናገራሉ።
“ነገር ግን በየትኛውም ዓለም ሙሉ በሙሉ ምንም አይነት መዘናጋት አይኖርም ማለት አይደለም። አሁን ጥቃት የተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሶማሊያ የድንበር ከተሞች ላይ ሲሆን ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ አልገባም” ሲሉም ርዕሰ መስተዳደሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አክለውም አልሸባብ ጥቃቱን ከከፈተባቸው አራት ቦታዎች በሦስቱ ተመትቶ በአንዱ ብቻ ማለፉን ገልጸው፣ ያንንም በመከታተል አንድም ሳይተርፍ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
“እኔ አሁን የማነጋግርሽ ፌርፌር ከተማ ላይ ሆኜ ነው። ይህ መጨረሻው የኢትዮጵያ መሬት ነው” ሲሉ አክለዋል።

የአልሸባብ ጥቃት ለኢትዮጵያ ቀጣይ ስጋት ይሆን?
ታጣቂ ቡድኑ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው። ኢትዮጵያ እኤአ በ2006 ሶማሊያ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ስትወስን አክራሪ እስላማዊ ቡድኖች ለደኅንነቴ ስጋት ሆነዋል በሚል ነበር።
ይህ ውሳኔም በወቅቱ በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በኩል ከፍተኛ ተቃውሞን በመንግሥት ላይ ያስከተለ ሲሆን፥ በርካታ ሶማሊያውያን ጣልቃ ገብነቱን እንደ ወረራ በመመልከት ተቃውመውታል።
ታዲያ ለሁለት ዓመት የቆየው ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊ ዘመቻ በወቅቱ ጠንክሮ በመውጣት ላይ የነበረውን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን በጠላትነት የፈረጀ ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያ “እቅዴን አሳክቻለሁ” ብትልም ይህንን ተከትሎ አደገኛ የተባለው አልሸባብ ተፈጥሯል።
ኢትዮጵያ በአሚሶም ውስጥ ካላት ተሳትፎ ባሻገር በበርካታ ስልቶች አልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ እንዳይገባ መክታለች ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ታዲያ ምዕራባውያን በሌሎች የቤት ሥራዎች ተጠምደው ባሉበት ወቅት የኢትዮጵያን ወሰን ሰርስሮ ለመግባት ጥቃት የሰነዘረው አል ሸባብ ስጋትነቱ ከፍ ወዳለ ደረጃ ላይ ደርሶ ይሆን?
“አልሸባብ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ ዘልቆ መግባት ብሎም በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል ያሉ ተራሮችን ለመያዝ መመከሩ ትንሽ የሚባል ጥቃት አይደለም” ሲሉ ፋይሰል ሮብሌ ይናገራሉ።
“የክልሉ አመራር አልሸባብን ገፍተናል ይበል እንጂ አጥፍተናል ማለት አይችልም። ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የአልሸባብ አጥቂ ነበረች አሁን ተከላካይ ነች” ይላሉ።
አልሸባብ አንድ ቦታ እግሩን ካስገባ በኋላ የሚከተለውን ስልት የሚያብራሩት ፋይሰል፣ በተለይም የአገር ሽማግሌ እና ወጣቶችን በኃይል ብሎም ከመንግሥት ያላገኙትን ግልጋሎት በማሟላት መሆኑንንም ያብራራሉ።
ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ እንደሚሉት ሰልጥኖ ወደ ኢትዮጵያ የተላከው ኃይል “የኢትዮጵያ ሙጃሂዲን” በሚል ስያሜ ኢትዮጵያን ኢላማ ያደረገ የሽብር መረብ ነውም ሲሉ ተናግረዋል።
“ሁኔታው አሳሳቢ ነው”
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በቀድሞው የሥልጣን ዘመናቸው ከአልሸባብ የግድያ ሙከራ ሦስት ጊዜ ተርፈዋል።
ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከኢኮኖሚስት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ቅድሚያ ከሚሰጡት ዕቅዳቸው ውስጥ ታጣቂ ቡድኑን ኢላማ ማድረግ እንደሆነ ገለጸዋል።
ምንም እንኳን ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ከበአለ ሲመታቸው በኋላ ባይገናኙም፣ ታጣቂ ቡድኑ ግን የጋራ ጠላታቸው መሆኑን ፋይሰል ሮብሌ ይናገራሉ።
“ኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል አላት፤ ሶማሊያ ደግሞ አካባቢያዊ እውቀት አላት። ስለዚህ እነዚህ አገራት ተባብረው ከሰሩ ተስፋ አላቸው። ካልሆነ ግን አልሸባብ ከሁለቱ አገራት አልፎ ለቀጠናው ስጋት ሆኖ ይቀጥላል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በጅግጂጋ ከተማ የሚገኙት የኦብነግ ሊቀ መንበር አቶ አብዱራህማን መሀዲ “ሁኔታው አሳሳቢ ነው” ቢሉም፤ የአልሸባብ ፍላጎት ግን በሶማሌ ክልል ይሳካል ብለው አያምኑም።
“የሶማሌ ሕዝብ ድጋፍ እና ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም የሶማሌ ሕዝብ ሃይማኖቱን እና ባህሉን በተመለከተ ጠንካራ ሕዝብ ነው። እንዲህ ባሉ ርዕዮት ዓለሞች እና አዲስ የኢስላም አስተምኅሮዎች አይገዙም” ሲሉ አብዱራህማን ይናገራሉ።
“የክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥታት ብሎም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህንን ክስተት አቅልለው እንዳያዩት እናሳስባለን። ይህ የውስጥ ጉዳይ አይደለም። ከውጭ የመጣ ጥቃት ስለሆነ ሁሉም መተባበር አለበት” ሲሉም አሳስበዋል።
አብዱራህማን አክለውም የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስን በገንዘብ፣ በትጥቅ፣ በሰው ኃይል ብሎም በሥልጠና ማጠናከር ይገባል ይላሉ።