
“ሐምሌ 22 ቀን 1928 አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ወደ ግራዚያኒ ቀረቡ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም ፊታቸውም ዘለግ ያለ መልካቸው ጠየም ያለ አዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብስ የጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚሕ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድም የተሰየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንት ናቸው፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም አምጽዋል፣ ሌሎችንም እንዲያምፁ አድርገዋል የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም ካህናቱም ኾኑ የቤተክህነት ባለስልጣኖች አቡነ ቄርሎስም የኢጣሊያን መንግሥት ገዢነት አምነው ሲቀበሉ እርሰዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎትን አፈንጋጭ ኾኑ? ሲል ጠየቃቸውʺ አቡነ ጴጥሮስም ተናገሩ፡፡ እንዲሕም አሉ፡፡ʺአቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚሕ ስለ ሀገሬና እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚሕ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣሪየ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደ ወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ” አሉ፡፡ (ዲያቆን መርሻ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን)
ʺጳጳሱ ላይ የተቋቋመው ችሎት ሕዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ እንዲገደሉ ፈረደ፡፡ ይሕ ሲሰማ በከተማው ሕዝብ ዘንድ ሽብር ፈጠረ፡፡ ጉዳዩም በጋዜጣ እንዳይወጣ ፋሽሽቶች ታላቅ ቁጥጥር አደረጉ፡፡ መስቀል የያዙት ጳጳስ የሞቱን ፍርድ በዝምታ አዳመጡ፡፡ ወደ መገደያ ቦታውም ወሰዷቸው፡፡ ጳጳሱም መገደያቸው ቦታ ሲደርሱ ፊታቸውን አሟሟታቸውን ሊያይ ወደ ተሰበሰበው ሕዝብ አዙረው ቆሙ፡፡ እርሳቸው ሞት ይፈሩ ይመስል ሊገድሏቸው እያዘጋጇቸው ዓይንዎን እንዲሸፈኑ ይፈልጋሉን? ብለው ጠየቋቸው፡፡ እሳቸው ግን እንደፈለጋችሁ አድርጉ ለእኔ ማንኛውም ስሜት አይሰጠኝም አሉ፡፡”
ʺከሚገደሉበት ሥፍራ ሲደርሱ አራቱንም አቅጣጫ በመስቀላቸው ባረኩ፡፡ በሕዝቡም ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፡፡ ፋሽሽቶች የሀገራችንን አርበኛ ሽፍቶች ቢሏቸው እውነት አይምሰላችሁ፡፡ ሽፍታ ማለት ያለ ሀገሩ መጥቶ የሰውን ሀገር የሚወር ይህ በመካከላችሁ የቆመ አረመኔው የኢጣሊያ ፋሽሽት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእርሱ እንዳይገዛ ውጉዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት እንዳትቀበለው የተገዘተች ትሁን” አሉ፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት)
የመከራዋ ሰዓት ደረሰች፡፡ አቡነ ጴጥሮስ በጣሊያን ጀነራሎች ትዕዛዝ አስካሪና ባንዳ ተብለው በሚጠሩ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከዳተኛ ወታደሮች በበርካታ ጥይቶች ተደብድበው ሠመዓት ሆኑ።