15 ጥር 2022
ተሻሽሏል 3 ነሐሴ 2022

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ለጉብኝት ወደ ታይዋን መጓዛቸው ቻይናን ክፉኛ አስቆጥቷል።
የአፈ ጉባኤዋ ጉብኝት ከባድ መዘዝን ሊያስከትል እንደሚችል ስታስጠነቅቅ የነበረችው ቻይና፣ ሠራዊቷ አስፈላጊ ለሆነ እርምጃ ሁሉ ዝግጁ እንዲሆን ማዘዟን አሳውቃለች።
ቻይና የግዛቷ አካል አድርጋ ከምትመለከታት ታይዋን ጋር የትኛውም አገር የሚያደርገው ግንኙነት ሉአላዊነቷን ለመጋፋት እንደሚደረግ እርምጃ አድርጋ ነው የምትመለከተው።
በዚህም ሳቢያ የናንሲ ፔሎሲ በአሜሪካ እና በቻይና እንዲሁም በደቡብ ምሥራቅ የኤሺያ ክልል ውስጥ ከባድ ውጥረትን አስከትሏል።
ከወታደራዊ አቅም አንጻር ታይዋን ከቻይና ጋር የምትነጻጸር ባትሆንም፣ ቻይና አንዳች አይነት እርምጃ በታይዋን ላይ ብትወስድ አሜሪካ እና አጋሮቿ እንዲሁ መዝምታ የሚያልፉት አይሆንም።

በቻይና እና በታይዋን መካከል ያለው ፍጥጫ ለረጅም ጊዜ የቆየ ሲሆን፣ ከወራት በፊት ቻይና በርካታ የጦር አውሮፕላኖቿ የታይዋንን የአየር ክልል ጥሰው በመግባታቸው ውዝግብ መከሰቱ ይታወሳል።
በዚህ ሁሉ ፍጥጫ ውስጥ የሚነሳው ዋነኛው ጉዳይ ቻይና ታይዋንን ወደ ግዛቷ ጠቅልሎ የማስገባት ፍላጎት ነው።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢን ፒንግ በአንድ ወቅት ታይዋን ከቻይና ጋር የመዋህዷ ነገር “መሳካት ያለበት ነው” ብለው ነበር። ፕሬዝደንቱ በንግግራቸው ታይዋንን መልሶ የቻይና አካል ለማድረግ ኃይል መጠቀም አማራጭ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ቻይና በራሷ የምትተዳደረው ታይዋንን እንደ ተገንጣይ ግዛቷ የምትቆጥራት ሲሆን የጊዜ ጉዳይ እንጂ ተመልሳ የቻይና አካል እንደምትሆን ቤይጂንግ ታምናለች።
ታይዋን በሌላ በኩል እራሷን እንደ ሉዓላዊ አገር ነው የምትቆጥረው። የራሷ የሆነ ሕገ-መንግሥት ያላት ሲሆን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥትም አላት።

ታይዋን ያለችው የት ነው?
ታይዋን ከደቡብ ምሥራቅ ቻይና ባሕረ ሰላጤ 100 ማይሎች ርቀት ላይ የምትገኝ ደሴት ነች።
በአካባቢው ከሚገኙና አሜሪካ ጥብቅ ወዳጆች መካከል የመጀመሪያው ተረታ ላይ የምትሰለፈው ታይዋን ከፍተኛ የሆነ አካባቢያዊ ጠቀሜታ እንዳላት ይታመናል።
ቻይና ታይዋንን የምትቆጣጠር ከሆነ በምዕራባዊ ፓሲፊክ አካባቢ ትልቅ ውጥረት ሊነግስ እንደሚችል የሚገመት ሲሆን አሜሪካም ብትሆን በጉዋም እና ሃዋይ ያሏት ትልልቅ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ ስጋት ሊፈጥር ይችላል።
- ቻይና ‘ታይዋን ነጻነቷን ካወጀች’ ጦርነት እንደምትከፍት አስጠነቀቀች
- ታይዋን 38 የቻይና ተዋጊ ጀቶች የአየር ክልሏን አልፈው መግባታቸውን ገለጸች
- በአዲሱ ዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ እሽቅድድም ዘመን ሠራዊቷን እያዘመነች ያለችው ቻይና
ታይዋን እንዴት ከቻይና ተለየች?
ቻይና እና ታይዋን የተለያዩት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሲሆን በጊዜው ቻይና እራሷ በአንድነት መንግሥት እና በኮሚዩኒስት ፓርቲ መካከል ለሁለት ተከፍላ ጦርነት ላይ ነበረች።
በአውሮፓውያኑ 1949 ኮሚዩኒስት ፓርቲ ድል ሲቀዳጅ የወቅቱ መሪ ማኦ ዜዱንግ ቤይጂንግን መቆጣጠር ቻሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሽንፈትን ያስተናገዱት የብሔራዊ ፓርቲው ደጋፊዎችና መሪዎች ወደ ታይዋን ሸሽተው ገቡ። የፓርቲው መሪ ቻንግ ካይ ሼክም ቢሆኑ ታይዋንን መደበቂያቸው አደረጓት።
ትንሽ ቆይተውም ኩሚ ታንግ የተባለውን ፓርቲ እዚያው ታይዋን ውስጥ መሰረቱ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ታዲያ ይህ ፓርቲ ታይዋን ውስጥ ወሳኝ የሚባል የፖለቲካ ክንፍ ሆኖ ቆይቷል።

በአሁኑ ጊዜ ቫቲካንን ሳይጨምር 13 አገራት ታይዋንን እንደ ሉዓላዊ አገር የሚቆጥሯት ሲሆን፣ የቻይና ዲፕሎማቶችም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አገራት ይህንን እንዳይቀበሉ ይወተውታሉ። ካልሆነ ደግሞ ሀሳቡን ሳይደግፉም ሳይነቅፉም እንዲቆዩ ሐሳብ ያቀርባሉ።
የታይዋኑ የመከላከያ ሚኒስትር አሁን ላይ ከቻይና ጋር የገቡበት ፍጥጫ ከ40 ዓመታት ወዲህ የጋለ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ቻይና ከታይዋን ጋር ዳግም የመዋሃድ ውጥኗን በተቻለ መጠን ወታደራዊ ባልሆነ መንገድ ለማሳካትና በተለይ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በመፍጠር ነገሮችን ለማሳለጥ ስትሞክር ቆይታለች። ነገር ግን ቻይና ወታደራዊ አማራጭ ለመከተል የምትወስን ከሆነ በምንም አይነት መንገድ ታይዋን እራሷን መከላከል አትችልም።
ቻይና ከአሜሪካ በመቀጠል ትልቁን ወታደራዊ በጀት የምትበጅት አገር ስትሆን በተለያዩ ወታደራዊ መስኮች አስገራሚ የሚባሉ ቴክኖሎጂዎችን ትጠቀማለች።
ከባሕር ኃይል እስከ ሚሳኤል እንዲሁም ከአየር ኃይል እስከ ሳይበር ጥቃቶች ድረስ በሁሉም ዘርፎች አስፈላጊውን ውጤታማ ሥራዎችን መከወን ችላለች።

አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ቻይና ታይዋንን ከወረረች ታይዋን ማድረግ የምትችለው ምናልባት የቻይና ባሕር ኃይልን ለጥቂት ጊዜያት መግታት አልያም የሽምቅ ውጊያ እያካሄደች ሌሎች አገራት እስኪረዷት መጠበቅ ብቻ ነው።
ይህን እርዳታ ደግሞ ከአሜሪካ ውጪ ከየትም እንደማይመጣ ይታመናል። ነገር ግን አሜሪካ አሁንም በጉዳዩ ላይ ግልጽ የሆነ አቋም የላትም።
በሌላ አገላለጽ አሜሪካ ታይዋን ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ በፍጥነት ታይዋንን ለማዳን ወደ ጦርነት ትገባለች ወይስ አትገባም የሚለው በውል አይታወቅም።
በዲፕሎማሲው ረገድ አሜሪካ ‘አንድ ቻይና’ የሚለውን ፖሊሲ የምትከተል ሲሆን፣ ይፋዊ የሆነ ግንኙነት ያላትም ከቤይጂንግ ጋር ብቻ ነው። ነገር ግን አሜሪካ ለታይዋን የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎችን ትሸጣለች።
በአውሮፓውያኑ 2021 ቻይና ታይዋን የግሌ ነው በምትለው የአየር ክልል ውስጥ ተዋጊ ጀቶችን መላኳ የሚታወስ ነው። ታይዋንም የቻይና ድርጊት ሉዓላዊነቴን የሚጥስና ደኅንነቴን አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት ከሳለች።
ታይዋን ለተቀረው ዓለም ምን ትፈይዳለች?
ታይዋን በኤሌክትሮኒክስ ምርት ላይ ትልቅ ሚና ያላት አገር ነች። ከስልኮች እስከ ላፕቶፖች፣ ከእጅ ሰዓት እስከ ጌሞች ድረስ ሁሉም ኤሌክትሮኒክሶች የሚጠቀሟቸው ዋና ዋና የውስጥ አካላት በብዛት የሚመረቱት ታይዋን ውስጥ ነው።
ታይዋን ሰሚኮንዳክተር ማኒፋክቸሪን ካምፓኒ (ቲኤስኤምሲ) የተባለው ኩባንያ ከፍተኛ መጠን ያለው ‘ቺፕስ’ በማምረት የዓለማችንን የኤልክትሮኒክስ ገበያ ግማሹን ይቆጣጠራል።
ይህ ድርጅት በ2021 በተደረገ ሪፖርት መሠረት አጠቃላይ ዋጋው 100 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል።

ቻይና ታይዋንን የምትቆጣጠር ከሆነ ደግሞ ዓለም በእጅጉ የምትፈልጋቸውን ነገሮች በዋነኛነት የሚመረትበትን ቦታ በእጇ አስገባች ማለት ነው።
በሌላ በኩል ምንም እንኳን ቻይና እና ታይዋን ከባድ ፍጥጫ ውስጥ ቢሆኑም በርካታ ታይዋናውያን ጉዳዩ ብዙም አያሳስባቸውም ይላል በቅርቡ የተሰራ አንድ ጥናት።
ከወራት በፊት አንድ ድርጅት ታይዋናውያን ከቻይና ጋር ጦርነት ቢገጥሙ ምን እንደሚሰማቸው ጠይቋቸው ነበር። ታዲያ 64 በመቶ የሚሆኑት ታይዋናውያን ጦርነት ይነሳል ብለው እምብዛም እንደማያስቡ ነው የተናገሩት። እንደውም ጦርነት ይኖራል ብለው አያምኑም።
ነገር ግን አብዛኛው ሕዝብ እራሱን ታይዋናዊ አድርጎ የሚቆጥር ሲሆን ከቻይና በብዙ ነገሮች የተለዩ እንደሆነ ነው የሚያምኑት።