
7 ነሐሴ 2022, 08:22 EAT
ተሻሽሏል ከ 8 ሰአት በፊት
ይህ ድርጊት የሆነው የዛሬ 60 ዓመት ነው። ወቅቱ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ የነበሩበትና ነጻነታቸውንም ለማግኘት መራር ትግል የሚያካሄዱበት ጊዜ ነበር።
ኢትዮጵያ ደግሞ በአድዋ ጦርነት ጣልያንን ድል አድርጋ፣ ጥቁሮች ነጮችን ማሸነፍ ይችላሉ በሚል ብዙ የአፍሪካ አገራት ምሳሌያቸው አድርገው ወስደዋታል።
በደቡብ አፍሪካም የቅኝ ግዛትን ተቃውመው ትግል ከጀመሩት መካከል አንዱ የሆነው የፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴ ይጠቀሳል።
በዚህ ውስጥ ደግሞ የኔልሰን ማንዴላ ድርሻ ትልቅ ነው።
በ1954 ዓ.ም ማንዴላ ስማቸውን ዴቪት ማትሶማይ በሚል ፓስፖርት ተዘጋጅቶላቸው፣ ፣ ስራቸው ጋዜጠኛ በሚል ተጠቅሶ ወደ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ መጡ።
ስልጠናውን ከመውሰዳቸው በፊት ግን ኢትዮጵያ አሰልጣኝ እና ጠባቂ ለመመደብ ሽር ጉድ ብላለች።
በዚህ መካከል ለው የወቅቱ ሻምበል ጉቱ ዲንቃን ታሪክ የሚያነሳቸው።
- በባርነት ከመሸጥ የተረፉት 64 ኢትዮጵያዊያን26 ሀምሌ 2019
- ከ43 ዓመት በኋላ የተገናኙት ኢትዮጵያዊ እናትና ስዊድናዊ ልጅ20 ሀምሌ 2019
- ለኔልሰን ማንዴላ የተበረከተ ዝነኛ የቦክስ ቀበቶ ተሰረቀ13 ሀምሌ 2022
ጉታ ዲንቃ ደብሱ በ1928 በምዕራብ ሸዋ ቶኬ ሌንጫ ጊዮርጊስ አካባቢ ተወለዱ።
ከ20 ዓመት በኋላ በ1948 ዓ.ም በጉደር ከተማ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ከስድስተኛ ክፍል ለፖሊስ አባልነት ስልጠና ወደ ወሎ ክፍለ አገር አመሩ።
ከስድስት ወር የፖሊስ ስልጠና በኋላ ተመርቀው ወደ ስራ ተሰማሩ።
በ1953ዓ.ም ግን ሻምበል ጉታ የተለየ እድል ገጠማቸው።
ይሰሩበት ከነበረው የፖሊስ ማርሽ ባንድ ብቁ ሆነው ስላልተገኙ ለኮማንዶ ስልጠና ለሶስት ወር ተላኩ።
ያኔ የኮማንዶ ስልጠናውን የሚሰጡት እስራኤላውያን ነበሩ።
ይህ ስልጠና አቶ ጉታን ለመልካም እድልም ለፈተናም ጋበዛቸው።

ኔልሰን ማንዴላ ለመጠበቅ ኃላፊነት መረከብ
ኔልሰን ማንዴላ በጃንሆይ ዘመነ መንግሥት ከዛሬ ስድሳ ዓመት ገደማ በፊት ለወታደራዊ ስልጠና ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር የሕይወት ታሪካቸውን በሰነዱበት ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ላይ አስፍረዋል።
በወቅቱ ለኔልሰን ማንዴላ የተዘጋጀው ፓስፖርት ላይ ማንዴላ የጓደኛቸዉን ስም ይዘው ጋዜጠኛ እንደሆኑም ነበር የተነገረው።
ማንዴላ የኢትዮጵያ አድማ በታኝ ፖሊስ በሚሰለጥንበት አዲስ አበባ ኮልፌ የሚባለው ሰፈር ነው ስልጠናውን የወሰዱት።
ኔልሰን ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ ለስልጠና ከመምጣታቸው በፊት ፓርቲያቸው ኤኤንሲ ከፖለቲካ ተሳትፎ በተጨማሪ የወታደራዊ ክንፍ አቋቁሞ ነበር።
“አፄ ኃይለ ሥላሴ ከእንግሊዟ ንግስት ኤልሳቤጥ ጋር ጥሩ ወዳጅ ስለነበሩ፣ በከፍተኛ ሚስጥር ኔልሰን ማንዴላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስልጠና እንዲወስዱ ለጄነራል ታደሰ ብሩ ትዕዛዝ ተላለፈ። ለዚህም ደግሞ ሁለት አሰልጣኞች እና ሁለት ጠባቂዎች በሚስጥር እንዲመደብላቸው ታዘዙ” ይላሉ ሻምበል ጉታ።
አንድ ቀን ለሻምበል ጉታ አዛዣቸው እንደሚፈልጋቸው ይነገራቸዋል።
እርሳቸውም ወደተጠሩበት ቢሮ ሲደርሱ መቶ አለቃ ፈቃዱ ወንድሙ እና 50 አለቃ ደበበ እሸቴ ቢሮ ተቀምጠው እየጠበቃቸው ነበሩ።
እርሳቸወም በወታደራዊ ስረዓት ሰላምታ ሰጥተው የሚቀጥለውን ትዕዛዝ ሲጠብቁ ጄነራል ታደሰ መጡ።
“ጄነራል ታደሰ ‘ከእዚህ በኋላ ከፍተኛ ምስጢር የሚፈልግ፣ ኃላፊነት ይሰጣችኋል። አንድ ትልቅ እንግዳ ወደ አገራችን መጥቷል። በዚህ ካምፕ ውስጥ ሚስጥራዊ ቦታ ተዘጋጅቶለታል። ስለዚህ ለእናንተ የተሰጠው ይህንን ትልቅ ሰው የመጠበቅ ኃላፊነት ነው ‘አሉን።”
በዚህ መልክ ኮሎኔል ፈቃዱ ዋኬኔ፣ የማንዴላ አሰልጣኝ፣ መቶ አለቃ ፈቃዱ ወንድሙ ረዳት አሰልጣኝ፣ ሹፌር እና የማንዴላ አስተርጓሚ ሆነው ይመደባሉ።
ሻምበል ጉታ ዲንቃ እና 50 አለቃ ደበበ እሸቴ፣ በፈረቃ ማንዴላን እንዲጠብቁ ከጄነራል ታደሰ ብሩ ኃላፊነት ተሰጣቸው።
በነጋታው ጄነራል ታደሰ ብሩ በራሳቸው መኪና፣ ማንዴላን ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ወደሚገኘው ወደ መኮንኖች ክበብ ማምጣታቸውን አቶ ጉታ ያስታውሳሉ።
ኔልሰን ማንዴላን የመግደል ሴራ
ማንዴላ ማንነታቸውን ለመሰወር ስማቸውን እና ሙያቸውን በመቀየር ጥረት ቢያደርጉም የአፓርታይድ ስርዓት መሪዎች ግን ዱካቸውን አነፍንፈው ደርሰውበታል።
እናም የማንዴላ እቅድ ከመንገድ ለማስቀረት በሚል እቅድ አውጥተው፣ በጀት በጅተው ተወካዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ላኩ።
ተወካዮቻቸው ደግሞ ማንዴላን የመግደል እቅድ አውጥተዋል። እቅዳቸውም ማንዴላ በሚተኛበት ቦታ፣ በገመድ አንቆ የሚገድል ሰው በብር መግዛት ነበር።
ለዚህ ደግሞ አይናቸውን ሻምበል ጉታ ዲንቃ ላይ ነው የጣሉት።
እርሳቸውን ለማባበል ከፍተኛ ገንዘብ ማቅረብ ሌላም መደለያ ማመቻቸት ጀመሩ።
“ያኔ ለሶስት ወር ኮማንዶ በእስራኤላውያን ስንሰለጥን፣ አብርሃም የሚባል ሰው ከኤርትራ የመጣ ጓደኛዬ ነበር። አብረም እንሰለጥን ስለነበር በጣም እንዋደዳለን። ለካ እርሱ ይሰልለን ነበር። ማንዴላ እዚህ መኖሩ እና የእርሱ ጠባቂ መሆኔን በሆነ መልኩ አቀውቋል። አንድ ቀን ፒያሳ ጠርቶ ምሳ ልጋብዝህ አለኝ። ያን ቀን የኔ ተራ እንዳልሆነ ያውቃል። ስለዚህ ጣይቱ ሆቴል ተገናኝተን ምሳ ከበላን በኋላ ከሁለት ሰዎች ጋር አስተዋወቀን፤ አንድ ነጭ እና አንድ ጥቁር።”
በልተው ጠጥተው ካበቁ በኋላ አብርሃም ለሻምበል ጉታ ያስደነገጣቸውን ነገር ይነግራቸዋል።
“እንደግዲህ ጉታ እኔና አንተ ጓደኛሞች ነን። ከዚህ የወታደር ስራ የሚገላግለን አንድ ነገር ተገኝቷል። ትቀበላለህ ወይ ብሎ ጠየቀኝ፤ እኔም ሎተሪ ደረሰህ ወይ ብዬ ጠየቅኩት፤ ከዚያ አብርሃም ጉዳዩ በአንተ እጅ ነው። ካወቅንበት ማድረግ እንችላለን ስለዚህ ቃል ግባልኝ አለ፤ እኔም የምችለው ከሆነ እሺ አልኩት። ‘እንደዚያ ከሆነ የምትጠብቀውን ሰው በመስኮት ገብተህ በተማርከው የኮማንዶ ስልት አንቀህ ትገድለዋለህ፤ ከሞተ በኋላ ሬሳውን ሁለት ጊዜ ፎቶ ታነሳዋለህ፤ ለዚህ ደግሞ ካሜራ ይሰጥሃል።ከዚያ በኋለ ከጦር ካምፕ ውጪ አንድ ቦታ በተዘጋጀ መኪና ያንኑ ለሊት በሞያሌ በኩል እንወጣለን’ ብሎ እጅግ የሚያስደነግጥ ነገር ነገረኝ”
ሻምበል ጉታ ግድያውን ፈጽመው ወደ ፈለጉበት የአውሮጳ አገር ሄደው እንዲኖሩ፣ በተጨማሪ ደግሞ የ2000 ፓውንድ የገንዘብ ስጦታ ተዘጋጅቶላቸዋል።
የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው በእቅዱ ተስማምተው 2000 ፓውንዱን እና ካሜራውን ተቀብለው ቀጥታ ወደ ጄነራል ታደሰ ብሩ ቤት አመሩ።

የግድያው ሴራ መክሸፍ
“ያኔ ከፒያሳ እስከ መርካቶ ጋሪ ስለነበር ጋሪ ይዤ፣ ከዚያ በእግሬ በፍጥነት ወደ ጄነራል ታደሰ ቤት ነው ያመራሁት። ከዚያ ለኔልሰን ማንዴላ የግድያ ሴራ እንደተዘጋጀ እና እኔም ተስማምቼ እንደመጣሁ ነገርኳቸው። ጄነራል ታደሰ ሊያምኑኝ አልቻሉም። ኔልሰን ማንዴላ እዚህ መኖሩን በምን አወቁ የሚለው ጥያቄ ሆኖባቸዋል መሰለኝ። ነገ ማታ እርሱን ገድዬ በተዘጋጀው መኪና በሞያሌ በኩል ለመውጣት እቅድ እደያዝን እና የምንገናኝበት ቦታ ደግሞ ከጦር ካምፑ 500 ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ጫካ ውስጥ መሆኑን ነገርኳቸው።”
ይህንን ለመቀልበስ ጄነራል ታደሰ ጊዜ አልፈጀባቸውም።
ስለዚህ ሚስጢራዊ ኦፕሬሽን ለማካሄድ ሁለቱ የማንዴላ አሰልጣኞች እና ጠባቂዎች ሰበሰቡ። ከዚያም እቅድ አወጡ። እቅዳቸውም ፈቃደ ወንድሙ እና ደበበ እሸቴ በተባለው ቦታ ቀድመው በመገኘት በደፈጣ ይጠብቃሉ።
ሌሎች ሁለት ወታደሮች ደግሞ ሻምበል ጉታ ዲንቃ የተያዙ አስመስለው እጃቸውን በካቴና በማሰር ቀጥታ ሰዎቹ ወደ ሚጠብቁበት ቦታ ይወስዷቸዋል
በሻምበል ጉታ እና አብርሃም ስምምነት መሰረት ኔልሰን ማንዴላ ነገ ለሊት ተገድለው በዚያው ለሊት በሞያሌ በኩል ወደ ውጪ ይጠፋሉ።
ሻምበል ጉታ ሃሳባቸውን እንዳይቀይሩ ቤተክርስትያን ሄደው እነዲምሉላቸው አብርሃም መጠየቁን ያስታውሳሉ።
ሻምበል ጉታ ከጄነራል ታደሰ ብሩ ቤት ከተመለሱ በኋላ 12 ሰዓት ላይ በቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስትያሰን ተገኝተው ለአብርሃም ማሉለት።
ወዲያው ግን ፈጣሪያቸውን በሐሰት ስለማሉ ይቅር እንዲላቸው ተማጽኗቸውን ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።
ጄነራል ታደሰ ብሩ እንደመከሯቸው ማንዴላን ገድለው ከሰዎቹ ጋር የሚገናኙበት ሰዓት ሲደርስ ሁለቱ ወታደሮች ሻምበል ጉታን ይዘው ከእነዚያ ሰዎች ጋር የሚገናኙበት ቦታ ወሰዷቸው።
በተመሳሳይ ሰዓት በቦታው የነበሩ ወታደሮች ሁለቱ የውጪ ዜጎች እና አብርሃምን በቁጥጥር ስር አዋሉ።
ሰዎቹ ሻምበል ጉታ ነው ያስያዘን እንዳይሉ ሻምበል ጉታም ያን ለሊት አብረዋቸው እስር ቤት አደሩ።
“ጄነራል ታደሰ ያዘጋጁት ሚስጥራዊ ኦፕሬሽን በዚህ መልኩ ተጠናቀቀ ማንዴላም ከሞት ተረፈ።”
የማንዴላ የግድያ ሙከራ አፄ ኃይለስላሴ ጋር መድረሱ
ሻምበል ጉታ እንዳሉት ማንዴላ ላይ የግድያ ሙከራ ሴራ መክሸፉን በጄነራል ታደሰ ብሩ በኩል ለአፄ ኃይለስላሴ ደረሳቸው።
ይህንን ሙከራ ያከሸፈው ጉታ ዲንቃ የተባለ ወታደር መሆኑንም ጃንሆይ ሰሙ።
ይህ ሚስጥር እንዳይወጣ አፄ ኃይለስላሴ እና ጄነራል ታደሰ ዝምታን መረጡ።
ሁለቱ የውጪ አገር ዜጎች በ24 ሰዓት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ተደረገ።
አብርሃም ደግሞ በወታደራዊ ሕግ መሰረት ከደረጃው ወርዶ ወደ ጠረፍ ተላከ።
ሻምበል ጉታ ዲንቁም ለዋሉት ውለታ፣ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የማዕረግ እድገት ቢሰጣቸው የግድያ ሴራው ወሬ ሌሎች ጆሮ ይደርሳል፣ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ በሚል ታለፉ።
ሻምበል ጉታ “ያኔ ብሩን ወስጄ የፈለግኩት አገር ሄጄ መማር እችል ነበር። ግን ማንዴላን በጣም እወደዋለሁ፤ ማንዴላ ለነጻነት ስለሚታገል እኛም ያኔ ሜጫ እና ቱለማ ውስጥ ስለ ነጻነት አንዳንድ ነገር እንፈልግ ነበር። ሌላ ደግሞ አዛዤ በጣም ይወደኛል። አምኖኝ ይህንን ስራ ሰጠኝ፤ ጄነራል ታደሰ ደግሞ መጀመርያ ለዚህ ስራ ሲመድቡኝ የመከሩኝ ነገር ልቤን አሸነፈ” በማለት ማባበያውን ያልተቀበሉበትን ምክንየዓት ያስረዳሉ።
አክለውም “ ያኔ. . .ዛሬ የምትጠብቁት ሰው ትልቅ ሰው ነው። አንድ ቀን ስለ እርሱ አውቃችሁ እርሱን በመጠበቃችሁ ትኮራላችሁ አሉን። እኔም ማንዴላን ገድዬ የአገሬን ስም ማሰጠፋት አልፈለግኩም” በማለት ለምን ማንዴላን መግደል እንዳልመረጡ ይናገራሉ።
‘ጄነራል ታደሰ 250 ብር ሸለሙኝ’
ሻምበል ጉታ ማንዴላን ከሞት በማትረፋቸው ጄነራል ታደሰ ሸለሟቸው።
“ጠርተውኝ አንተ ታሪክ ነው የሰራሀው አሉኝ። ድሮም አንተ አውቅሃለሁ አንተ ጀግና ነህ። አሁን ደግሞ ከልጆቼ መካከል እንደ አንዱ ነው የማይህ በማለት ከኪሳቸው ወስጥ 250 ብር አውጥተው ሸለሙኝ።”
ሻምበል ጉታ አክለውም ጄነራል ታደሰ ከግለሰቦቹ የተገኘውን 2000 ፓውንድ ለበጎ አድራጎት ድርጅት መስጠታቸውን ያስታውሳሉ።
“ያኔ ጄነራል ታደሰ ብሩ አባታቸው በጦር ሜዳ የሞቱ ልጆ ችን የሚያሳድግ ድርጅት ኃላፊ ነበሩ። ወ/ሮ ውዴ የምትባል ስራ አስኪያጅ ነበረች። ጄነራል ታደሰ 2000 ፓውንዱን መንዝረው አንድ ሳያስቀሩ ለድርጅቱ እነዲውል በማለት ለእርሷ ነው ያስረከቡት፤ ካሜራውን ግን የት እዳስቀመጡት አላውቁም” ይላሉ።
ሻምበል ጉታ በ1981 ጡረታ እስኪወጡ ድረስ በተለያዩ የጦር ግንባር ተሰልፈው አገራቸውን አገልግለዋል።
የስምንት ልጆች አባት የሆኑት የ87 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት ሻምበል ጉታ በትዳር 60 ዓመት ቆይታዋል።